MAP

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የአፍሪካ ነጋዲያን የኢዮቤልዩ በዓልን ተካፍለዋል ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የአፍሪካ ነጋዲያን የኢዮቤልዩ በዓልን ተካፍለዋል  

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “የተጠመቀ ክርስቲያን በሙሉ የተስፋ ምልክት እንዲሆን መጠራቱ ሊሰማው ይገባል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ሰኞ ዕለት የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ለተካፈሉት የአፍሪካ አምባሳደሮች፣ ተወካዮች እና ነጋዲያን መልዕክት አስተላልፈዋል። ሰኞ ዕለት በተፈጸመው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ እያንዳንዱ የተጠመቀ ክርስቲያን በዓለማችን ላይ የተስፋ ምልክት ለመሆን መጠራቱ ሊሰማው ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር ለአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች እና የኢዮቤልዩ በዓል ተካፋይ ለሆኑ የአፍሪካ ነጋዲያን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሰኞ ግንቦት 18/2017 ዓ. ም. የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮድዎ አፒያ ታርክሰን ናቸው።     

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የአፍሪካ ቀን” 62ኛ ዓመት በተከበረ ማግሥት በቀረበው መስዋዕተ ቅዳሴ ማጠናቀቂያ ላይ ተገኝተው ለልዑካን ቡድኑ ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “እያንዳንዱ የተጠመቀ ክርስቲያን በዓለም ውስጥ የተስፋ ምልክት እንዲሆን መጠራቱ ሊሰማው ይገባል” ሲሉ አበረታተዋል።

ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ለተገኙት የአፍሪካ ነጋዲያን እና አምባሳደሮች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. በመከበር ላይ የሚገኘው የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት፥ “ሁላችንንም የሚያነቃቃን፣ ተስፋን እንድንፈልግ እና የተስፋ ምልክቶችም እንድንሆንም ጭምር የሚጋብዘን ነው” ብለዋል።

በመሆኑም እያንዳንዱ የተጠመቀ ክርስቲያን ዛሬ በዓለም ላይ የተስፋ ምልክት ለመሆን በእግዚአብሔር የተጠራ መሆኑ ሊሰማው ይገባል ብለዋል።

“እምነት የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃን በሕይወታችን እንድናይ ብርታትን ይሰጣል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥በየእሁዱ፣ በሌሎች ትላልቅ መንፈሳዊ በዓላት ወይም በመንፈሳዊ ንግደት ወቅት ብቻ ሳይሆን በእምነት ጎዳና በምንመላለስበት ወቅት በሙሉ አስፈላጊ መሆኑን ለመረዳት የሚያስችለን እና ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በሚሰጠን ተስፋ እንድንሞላ የሚያደርገን እምነት ነው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፥ ሁላችንም በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት መንፈስ አንድ ሆነን እግዚአብሔርን በማመስገን፣ ያለን እና የሆነው በሙሉ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ተገንዝበን ለሌሎች አገልግሎት እንደምናውለው ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ መስዋዕተ ቅዳሴውን የተካፈሉት በቅድስት መንበር የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች እና የአኅጉሪቱ ነጋዲያን እምነታቸውን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማኖራቸው አመስግነዋቸዋል።

ቡድኑ በብፁዕ ካርዲናል ቱርክሰን፥ በጳጳሳዊ የሥነ-ሕይወት ጥናት የማኅበራዊ ሳይንስ አካዳሚዎች ቻንስለር፣ በብፁዕ ካርዲናል ፍራንሲስ አሪንዜ፣ የመለኮታዊ አምልኮ እና የቅዱሳት ምስጢራት ጉዳይ አስተባባሪ በነበሩት እና በሊቀ ጳጳስ አቡነ ፎርቱናተስ ኑዋቹኩ፥ የወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ በኩል መልካም አቀባበል እንደተደረገለት ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማጠቃለያ መልዕክታቸው፥ መስዋዕተ ቅዳሴውን የተካፈሉት በሙሉ፥ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ተመስገን! ስምህ የተመሰገነ ይሁን!” በማለት ለቡድኑ አባላት ባቀረቡት ጸሎት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

27 May 2025, 11:38