ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፤ የቅድስት መንበር ተግባር ግን ዘወትር ይቀጥላል!"
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“እምነት እና ጸሎት ለምግብ ጣዕም እንደሚሰጥ ጨው ናቸው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅዳሜ ግንቦት 16/2017 ዓ. ም. ጠዋት በቫቲካን ለተቀበሏቸው የግዛቲቱ ሠራተኞች ተናግረው፥ እነዚህን ሁለቱን በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ውስጥ በማስገባት ሃላፊነታቸውን ዘወትር በአግባቡ እንዲወጡት አደራ ብለዋል።
ቅዱስ አባታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ከከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ባለሥልጣናት፣ ከቅድስት መንበር ሠራተኞች፣ ከቫቲካን አስተዳደር ጠቅላይ ግዛት እና ከሮም ሀገረ ስብከት ሠራተኞች ጋር ሲገናኙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ነበር ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እያንዳንዱ ተቀጣሪ በሥራው የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተባባሪ እንደሚሆን በማስገንዘብ፥ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ የተሰበሰቡትን በደስታ ተቀብለው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
እያንዳንዱ ሰው የዕለተ ዕለት ተግባሩን በቁርጠኝነት እና በእምነት በመወጣት አስተዋፅኦን እንደሚያደርግ ገልጸው፥ “በተግባሩ ውስጥ ያሉት እምነት እና ጸሎት፥ ለምግብ ጣዕም እንደሚሰጥ ጨው ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል። ዕለቱ ቅዳሜ በመሆኑ በአዳራሹ ውስጥ ብዙ የቤተሰብ አባላት መገኘታቸው እጅግ ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ከቫቲካን ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው እንደሆነ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የዛሬው ንግግሬ የታቀደ ሳይሆን ነገር ግን ለምትሰጡት አገልግሎት ላመሰግናችሁ የሚያስችል አጋጣሚ ነው” ብለው፥ “ይህ ሐዋርያዊ አገልግሎቴ ከቀደሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የወረስኩት ነው” ብለዋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሁለት ዓመት በፊት የብጹዓን ጳጳሳት ጽሕፈት ቤትን እንዲመሩ በሾሟቸው ጊዜ ወደ ቫቲካም መምጣታቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥በወቅቱ ከፔሩ ቺክላዮ ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ተነስተው መምጣታቸውን አስታውሰዋል።
“እንዴት ያለ ለውጥ ነው! ታዲያ አሁን ምን እላለሁ?” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ስምዖን ጴጥሮስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለኢየሱስ ክርስቶስ፥ “ጌታ ሆይ ሁሉንም ነገር ታውቃለህ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” ሲል በተናገረው ላይ አስተንትነዋል።
“ር. ሊ. ጳ. ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፤ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶች ሥራ ግን ይቀጥላል”
“ር. ሊ. ጳ. ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፤ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶች ሥራ ግን ይቀጥላል” በማለት ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ይህ በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን እና በሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረው በሮም ጳጳስ ጽሕፈት ቤቶችም ተግባራዊ እንደሚሆን አስረድተው፥ የቤተ ክርስቲያን ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የአንድ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ ትውስታን፣ የጳጳሳትን አገልግሎት ጠብቆ የሚያቆይ እና የሚያስተላልፍ በመሆኑ አስፈላጊ ተቋም ነው” ብለዋል።
የማስታወስ ችሎታ በሕያዋን ፍጡር ውስጥ አስፈላጊ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ባለፈው ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ባአሁኑ ላይ በማደግ ወደፊት የሚመራ እንደሆነ በማስገንዘብ፥ “ያለ ትዝታ መንገድ ይጠፋና ጉዞውም ትርጉሙን ያጣል” ሲሉ አስረድተዋል።
እግዚአብሔርን ለጥሪው እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ
“በቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ መሥራት ማለት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን አገልግሎት በተቻለ መጠን በተሻለ መንገድ እንዲከናወን ማድረግ እና የሐዋርያዊ መንበር ትውስታ በሕይወት እንዲቆይ መርዳት ማለት ነው” ብለው፥ የቫቲካን ከተማ አስተዳደር አገልግሎቶችን በተመለከተ ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል ብለዋል።
በመቀጠልም፥ የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች እና ከቅዱስ ጴጥሮስ የሐዋርያነት አገልግሎት ጋር የተገናኘ እያንዳንዱ ተቋም ከትዝታ ጋር የተቆራኘ የሚስዮናዊነት አቅጣጫን አጉልተው አሳይተዋል።
“እንደምታውቁት ይህም እንደ ተጠመቁ ክርስቲያኖች የተልዕኮ ሕይወቴ ልምድ አካል እንደሆነ እና ነገር ግን እንደ ቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር አባልነቴ በፔሩ ስለኖርኩ የእኔ ሐዋርያዊ ጥሪ ያደገው በፔሩ ሰዎች መካከል በመሆኑ ለዚህ ስጦታ እግዚአብሔርን እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!” ብለዋል።
እምነት እና ጸሎት አስፈላጊ ናቸው!
በቅድስት መንበር ሥር በሚገኙ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ሆነው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የደረሳቸው ጥሪ አዲስ ተልዕኮ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዚህ ተልዕኮ መሳተፋቸውን ገልጸው፥ እግዚአብሔር እስከፈቀደ ድረስ ወደፊትም እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት በተመረጡበት ሐሙስ ሚያዝያ 30/2017 ዓ. ም. ምሽት ባቀረቡት የመጀመሪያ ሰላምታ ላይ ያደረጉትን ንግግር በመድገም፥ ሁላችንም፥ አንዱን ከአንዱ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ የምትገነባ፣ የእኛን በጎነት፣ ውይይትን እና ፍቅርን የሚፈልጉትን እጆቿን ዘርግታ ለመቀበል ዘወትር ዝግጁ የሆነች ሚሲዮናዊት ቤተ ክርስቲያን አባላት መሆን አለብን” ብለዋል።
እያንዳንዱ ሰው የዕለት ተዕለት ተግባሩን በቁርጠኝነት እና በእምነት እንዲያከናውን አሳስበው፥ እምነት እና ጸሎት በምግብ ውስጥ ጣዕም እንደሚሰጥ ጨው ናቸው” ብለዋል። እግዚአብሔር ይህንን ተግባር ለቅዱስ ጴጥሮስ እና ለተተኪዎቹ በአደራ መስጠቱን በማስታወስ፥ “በዚህ መሠረት ሁላችንም በተለያየ መንገድ በዚህ ታላቅ ሥራ እንተባበር” ሲሉ አሳስበዋል።
የዕለት ተዕለት ሁኔታዎችን
“ሁላችንም በታላቅ የአንድነት እና የፍቅር ተግባር መተባበር ከፈለግን፥ ከሥራ ዘርፋችን ጀምሮ በዕለተ ዕለት ባህሪያችን ሃላፊነታችንን ተግባራዊ ለማድረግ እንትጋ” ብለዋል።
“እያንዳንዳችን ለባልደረቦቻችን ባለን አመለካከት የአንድነት ገንቢ መሆን እንችላለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳስተማሩን፥ ይህም የማይቀሩ አለመግባባቶችን በትዕግሥት እና በትሕትና በማሸነፍ፣ ራሳችንን በሌሎች ጫማ ውስጥ በማስገባት፣ ጭፍን ጥላቻን በማስወገድ እንዲሁም ጥሩ ቀልዶችን በማሳየት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ለሁሉም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቡራኬን ተመኝተዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የቫቲካን ሠራተኞችን ከልባቸው በማመስገን፥ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶችን እና የቫቲካን ግዛት ሠራተኞችን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን እንድትባርክ በግንቦት ወር ውስጥ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን በአንድነት እንዲያቀርቡ በማበረታታት፣ በተለይም ህጻናትን፣ አዛውንትን፣ የታመሙትን እና የሚሰቃዩትን በጸሎታቸው እንዲያስታውሱ በመጋበዝ ንግግራቸውን አጠናቀዋል።