ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለሮም ሀገረ ስብከት የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ግንቦት 17/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን የሮም ጳጳስ ካቴድራል ውስጥ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት፥ ሌሎችን ማዳመጥ፣ ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን ድምፅ ማዳመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ቅዱስነታቸው ወደ ዮሐንስ ዘላቴራን ካቴድራል ከማቅናታቸው በፊት ወደ ከተማው ሲቪል እና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መቀመጫ ወደ ሆነው የሮም ማዘጋጃ ሲደርሱ የከተማው ከንቲባ አቶ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቦታው ተገኝተው አቀባበል ላደረጉላቸው የከተማውን ከንቲባ እና የሲቪል ባለስልጣናትን ካመሰገኑ በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ “ሮም ምን ጊዜም የምትለየው፥ የሰው ልጅ እና ሥልጣኔ ከቅዱስ ወንጌል ከሚመነጭ እሴት ነው” የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው በዮሐንስ ዘላቴራን ካቴድራል ለተገኙት ብፁዓን ካርዲናሎች፣ ጳጳሳት፣ ካህናት እና ምዕመናን ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ ባሰሙት ስብከት፥ “ሮም የታላቅ ታሪክ ወራሽ እንደሆነች፣ በቅዱስ ጴጥሮስ፣ በቅዱስ ጳውሎስ እና ስፍር ቁጥር በሌላቸው ሰማዕታት ምስክርነት ላይ የተመሠረተች ናት” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።
በመቀጠልም፥ ንፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “በቤተ ክርስቲያን የእናትነት ገጽታ ላይ እንድናሰላስል ይገባል” በማለት የጋበዙትን ጠቅሰው፥ ርኅራኄ፣ ለመሥዋዕትነት ዝግጁ እንድንሆን እና ለማዳመጥ የሚረዳን አቅምን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ ከመገለጻቸው በፊት የሚጠበቁ ፍላጎቶችን መገመት ይገባል” ማለታቸውንም አስታውሰዋል።
“እነዚህ እሴቶች በሁሉ ቦታ በሚገኙ የእግዚአብሔር ሰዎች ልብ ውስጥ፣ እዚህ በእኛ ሀገረ ስብከት ምዕመናን፥ በሐዋርያዊ አባቶች መካከል እና ከሁሉም በላይ በእኔ ውስጥም ማደግ እንደሚቀጥሉ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ አረጋግጠዋል።
የእግዚአብሔርን ድምፅ ማዳመጥ
በዕለቱ ከተነበቡት ንባብ በመነሳት ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፥ የመጀመሪያው የክርስቲያን ማኅበረሰብ ለአረማዊያን ወንጌልን ለመስበክ በጀመሩበት ወቅት ያጋጠማቸውን ፈተና እንዴት እንደተጋፈጡ አጽንኦት በመስጠት ሲናገሩ፥ “በሁሉም ሂደት ውስጥ ነገሮች እንዲቻሉ ለማድረግ እጅግ አስፈላጊው የእግዚአብሔርን ድምፅ ማዳመጥ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
እያንዳንዱ ሰው በዚህ ዓይነት ውጥረት ውስጥ ሲገኝ ብቻ ‘አባባ’ ብሎ የሚጮሄውን የመንፈስ ቅዱስ ድምፅ መስማት እንደሚችል እና በዚህም ሌሎችን እንደ ወንድም እና እህት መረዳት እንደሚችል አስረድተዋል።
በመንፈስ ቅዱስ መመራት
ቅዱስ ወንጌል በሕይወታችን ውስጥ በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ብቻችን እንዳልሆንን በመንገር መልዕክቱን እንደሚያጠናክረው ተናግረው፥ ኢየሱስ የተናገረውን ሁሉ በማስተማር እና በማስታወስ መከተል ያለብንን መንገድ መንፈስ ቅዱስ ያሳየናል” ሲሉ አስረድተዋል።
“ከሁሉም በፊት መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በውስጣችን በጥልቅ እንዲገባ በማድረግ ያስተምረናል” ብለው፥ “እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አገላለጽ ሕጉ በድንጋይ ጽላት ላይ የተጻፈ ሳይሆን ነገር ግን በልባችን ውስጥ ተቀምጦ እርስ በርሳችን አንዱ ለሌላው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መልዕክትነት እስክንለወጥ ድረስ የሚያሳድገን ስጦታ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ሁላችንም በእርሱ እንድንሸነፍ እና እንድንለወጥ በፈቀድን መጠን፥ ቅዱስ ወንጌልን ለሌሎች የመስበክ ችሎታ እንደሚኖረን፥ መንፈስ ቅዱስ ውስጣችንን እንዲያነጻው ስንፈቅድ ቃላቶቻችን ቀላል እና ቅን፣ ምኞቶቻችን ንፁህ እና ተግባሮቻችንም ለጋስ ይሆናሉ” ብለዋል።
“ማሳሰብ” የሚለውን ቃል የተመለከቱት ቅዱስነታቸው፥ ይህም የልብን ትኩረት ወደ ሕይወታችን ልምድ በማዞር ትርጉሙ በውስጣችን ዘልቆ ገብቶ ውበቱን ለማጣጣም ያግዛል” ብለዋል።