MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ከእምነት በሚገኝ ደስታ እንመላለስ” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እሑድ ግንቦት 17/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር ሆነው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ዘንድ ጸሎት አድርሰዋል። በዕለቱ ባሰሙት ስብከት ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ልባችን እንዳንታወክ በማለት ያቀረበውን ጥሪ በማስታወስ፥ ምዕመናኑ ከእምነት በሚያገኙት ደስታ እንዲመላለሱ አሳስበው፥ ምእመናኑ ላሳዩላቸው ፍቅርም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ግንቦት 17/2017 ዓ. ም. ከዮሐ. 14:23-29 ተወስዶ በተነበበው ላይ በማስተንተን ያሰሙትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! ሐዋርያዊ አገልግሎቴን በመጀመር ላይ እገኛለሁ። ከሁሉ አስቀድሜ ስለምታሳዩኝ ፍቅር አመሰግናችኋለሁ። ከጎኔ ሆናችሁ በጸሎታችሁ እንድትረዱኝ እጠይቃችኋለሁ።

እግዚአብሔር በሚጠራን የሕይወት እና የእምነት መንገድ አንዳንድ ጊዜ ጠንካሮች እንዳልሆንን ይሰማን ይሆናል። ነገር ግን ከዮሐ. 14:23-29 ተወስዶ የተነበበው የዛሬው ምንባብ፥ የራሳችንን ጥንካሬ ሳይሆን እኛን የመረጠን የእግዚአብሔር ምሕረት መመልከት እንዳለብን፣ መንፈስ ቅዱስ እንደሚመራን እና ሁሉንም ነገር እርሱ እንደሚያስተምረን እርግጠኞች እንድንሆን ያሳስበናል።

በመምህራቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ዋዜማ ላይ በጭንቀት የተረበሹት ሐዋርያት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መመስከር እንዴት መቀጠል እንደሚችሉ ያስቡ ነበር። ኢየሱስም በአስደናቂ ቃል ኪዳኑ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንደሚሰጣቸው እንዲህ ሲል ተናግሯል፥ ‘የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፣ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን፤ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን’ (ዮሐ. 14:23)።

በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከጭንቀት ነጻ አወጣቸው። “ልባችሁ አይታወክ፤ አትፍራም” ሲል አበረታታቸው (ዮሐ. 14:27)። በኢየሱስ ፍቅር ጸንተ ከኖርን እርሱ ራሱ በእኛ ውስጥ ይኖራል። ሕይወታችንም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ይሆናል፤ ፍቅሩም ብርሃናችን ይሆናል። የእርሱ ብርሃን በውስጣችን በመሆን ለአስተሳሰባችን፣ ለመንገዳችን እና ለምርጫችን አልፎ ተርፎ ለሌሎችም ጭምር የህልውና ብርሃን ይሆናቸዋል።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ ይህ የእግዚአብሔር በውስጣችን መኖር የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው። ​​በእጆቹም ደግፎን በዕለት ተዕለት ኑሮአችን የእግዚአብሔርን በውስጣችን መገኘት እንድንለማመድ በማድረግ መኖሪያውም ያደርገናል።

እያንዳንዳችን ጥሪያችንን፣ እውነታዎችን እና በአደራ የተሰጡንን ሰዎች በማየት፣ በምንፈጽማቸው ቃል ኪዳኖች፣ ለቤተ ክርስቲያን በምናበረክተው አገልግሎት ውስጥ በልበ ሙሉነት፥ ‘እግዚአብሔር እኔ ደካማ ብሆንም በእኔ ሳያፍር ወደ እኔ በመምጣት በውስጤም ይኖራል’ ብለን ለመናገር መቻላችን መልካም ነው። በመንፈሱ ይመራኛል፤ ብርሃኔም በመሆን ለሌሎች ሰዎች፣ ለኅብረተሰብ እና ለዓለም የፍቅር መሣሪያው አድርጎኛል።

ወዳጆቼ ሆይ! በዚህ የተስፋ ቃሉ መሠረት፥ የእግዚአብሔር ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን በእምነት ደስታ እንመላለስ። እያንዳንዳችን፥ እህት እና ወንድም የእግዚአብሔር ማደሪያዎች በመሆን፥ የእርሱ መገኘት በሕጻናት፣ በድሆች እና በተቸገሩት ሁሉ ላይ የሚገለጥ መሆኑን በማስታወስ፥ ለሌሎች የምንራራ ክርስቲያኖች መሆናችንን እናረጋግጥ።

ሁላችንም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድታማልደን እንለምን። እርሷ በመንፈስ ቅዱስ ድንቅ ሥራ የእግዚአብሔር ቅዱስ ማደሪያ ሆናለች። ከእርሷ ጋር በመሆን፥ እግዚአብሔርን ከመቀበል የሚመጣ ፍቅር፣ ምልክት እና መሣሪያ የመሆን ደስታን ማግኘት እንችላለን።”

 

26 May 2025, 17:29