MAP

ር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ፥ “በክርስቶስ ላይ ያለንን ውብ እምነት ለሰዎች መመስከር አለብን” በማለት አሳሰቡ

የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 267ኛው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው የተመረጡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ለብጹዓን ካርዲናሎች፥ “በክርስቶስ ላይ ያለንን አስደሳች እምነት መመስከር አለብን” በማለት አሳስበው፥ “የተጠራነውም በክርስቶስ አዳኝነት ላይ ያለንን አስደሳች እምነት እንድንመሰክር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓርብ ግንቦት 1/2017 ዓ. ም. ማለዳ ከመራጭ ካርዲናሎች እና ሌሎች ካርዲናሎች ጋር በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ባቀረቡበት ወቅት ባሰሙት ስብከት፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን አስደሳች እምነት መመስከር አለብን” በማለት አሳስበው፥ እምነት በሚጎድልበት ቦታ ሁሉ ሕይወት ትርጉም እንደሚያጣ አስጠንቅቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ከምርጫው በኋላ በሲስቲን ጸሎት ቤት የመጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴን ግንቦት 1/2017 ዓ. ም. አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ሐሙስ ሚያዚያ 30/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ለአራተኛ ዙር በተካሄደው የድምጽ መስጫ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከጠቅላላው ሁለት ሦስተኛ ድምጽ በማግኘት የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 267ኛ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ተመርጠዋል።

አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ባሰሙት ስብከት፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነትን ሁል ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ማሳደግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበው፥ ያለ እምነት ሕይወት ትርጉም እንደሌለውም ተናግረዋል።

በአሜሪካ ቺካጎ-ኢሊኖይ የተወለዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ የመረጧቸው ካርዲናሎች ላሳዩት እምነት አመስግነው፥ “በመዝሙረ ዳዊት 98:1 ላይ የተጻፈውን በመድገም፥ “ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር እዘምርለታለሁ፤ ምክንያቱም ተዓምራትን አድርጓልና፤ እርሱ ያደረጋቸው ተዓምራት ለእኔ ጋር ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም ጭምር ነው” ብለዋል።

“ብጹዓን ካርዲናል ወንድሞቼ ሆይ! ዛሬ ጠዋት ይህን መስዋዕተ ቅዳሴን ስናቀርብ እግዚአብሔር በቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያዊ አገልግሎት አማካይነት በሁላችን ላይ እያፈሰሰ ስላለው በረከቶች እና ስላደረጋቸው ተዓምራት እንድታስተነትኑ እጋብዛችኋለሁ” ብለዋል።

“ያንን መስቀል እንድሸከም እና ተልዕኮውንም እንድፈጽም ጠርታችሁኛል፤ እንደ ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጆች እና እንደ አማኞች የወንጌልን መልካም ዜና መስበክን በምንቀጥልበት ወቅት እያንዳንዳችሁ አብራችሁኝ እንደምትጓዙ አምናለሁ” ብለዋል።

ኢየሱስ የሰውን ቅድስና አሳይቶናል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወትን በማሰ ባሰሙት ስብከታቸው፥ በማቴዎስ ወንጌል ላይ፥ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” (ማቴ. 16:16) ብሎ መመለሱን በማስታወስ፥ “ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ላይ ያላትን ጽኑ እምነት ይበልጥ አጠናክራ ሐዋርያዊ የመተካካት ሥርዓቷን ለሁለት ሺህ ዓመታት ያህል ጠብቃ አቆይታዋለች” ብለዋል።

ቅዱስ ጴጥሮስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ያስተነተኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የአባቱን መልክ የሚገልጽ መሆኑን አስታውሰው፥ “በእግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች በሙሉ ቅርብ እና ተደራሽ ለማድረግ፥ በሚታመን ልጅ ዓይን፣ በብሩኅ የወጣት አእምሮ እና በሰው ልጅ በሳል ባህሪ አማካይነት ገለጠልን፤ በመጨረሻም ከትንሳኤ በኋላ በክቡር አካሉ ለደቀ መዛሙርቱ ታያቸው” ሲሉ አስረድተዋል። በዚህም መንገድ ከአቅማችን በላይ የሆነውን የዘላለም ግብ ለመስጠት ከገባልን የቃል ኪዳን ተስፋ ጋር ሁላችንም እርሱን ልንመስል የምንችልበትን የሰው ልጅ የቅድስና አብነት አሳይቶናል” ብለዋል።

ስጦታ እና መንገድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ የሰጣቸው ሁለት ምላሾች፥ “የእግዚአብሔር ስጦታ እና በዚህ ስጦታ ራሱን መለወጥ የሚችልበት መንገድ እንደሆኑ በመረዳት፥ እነዚም ለሰው ልጅ ጥቅም ሲባል ለቤተ ክርስቲያን በአደራ የተሰጡ የማይነጣጠሉ የመዳን ምልክቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

“በእርግጥም በእናቶቻችን ማኅፀን ውስጥ ከመፈጠራችን በፊት እግዚአብሔር የመረጠን፣ በጥምቀት ዳግመኛ የተወለድን፣ ከአቅማችን በላይ የሆነውን ነገር አሸንፈን ወንጌል ለፍጥረት በሙሉ ይሰበክ ዘንድ ወደዚህ ደረጃ አድርሶናል” በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።

“ለቤተ ክርስቲያን ታማኝ እንድሆን ጠርቶኛል!”

ሐሙስ ሚያዝያ 30/2017 ዓ. ም. ከቀትር በኋላ በሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ምትክ 267ኛ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ እግዚአብሔር እንደጠራቸው ገልጸው፥ “በእርሱም ዕርዳታ ለመላዋ ቤተ ክርስቲያን ስል ታማኝ ሐዋርያዊ መሪ እሆን ዘንድ ይህን ሃብት በአደራ ሰጥቶኛል” ብለዋል።

ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?" (ማቴ. 16:13) ብሎት ለጠየቀው ልዩ ጥያቄ መልስ በመስጠት እምነቱን እንደገለጸ አስታውሰው፥ ይህ ጥያቄ የአገልግሎታችን አስፈላጊ ገጽታ ማለትም የምንኖርበትን ዓለም ውስንነትን እና አቅሙን፣ ጥያቄዎቹን እና እምነቶቹን የሚመለከት ነው” በማለት አጉልተው ገልጸውታል፣

ሁለት የተለያዩ አመለካከቶች

ኢየሱስ “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ያለውን ጥያቄ በድጋሚ ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ “በዚህ ትዕይንት ላይ ብናሰላስል የተለያዩ አመለካከቶችን የያዙ ሁለት መላሾችን እናገኛለን” ብለው፥ የመጀመሪያው ዓለማዊ ምላሽ እንደ ሆነ እና ይህም ኢየሱስን ለመናቅ እና ለማስወገድ ወደ ኋላ የማይል፣ በሚያስጨንቅ ሞራላዊ መስፈርቶች ምክንያት የእርሱ ​​መኖር አሳፋሪ እንደሆነ እና፥ ሁለተኛው ምላሽ፥ ኢየሱስን እንደ ደፋር ሰው የሚመለከቱት ተራ ሰዎች፥ ሰው ብቻ እንደሆነ እና በዚህም በአደጋ ጊዜ እና በስሜታዊነት ወቅት ተስፋን በመቁረጥ ትተውት የሄዱ መሆናቸውን የሚገልጽ እንደ ነበር አስረድተዋል።

“ምስክርነትን ለመስበክ በአስቸጋሪ ቦታዎች ሚስዮናዊነት ያስፈልጋል”

በእነዚህ ሁለት አመለካከቶች ላይ የሚያስገርመው፥ በዘመናችን ውስጥ በብዙ ሰዎች አንደበት ላይ በቀላሉ ልናገኛቸው የምንችላቸውን ሐሳቦች የሚያካትቱ፥ መሠረቱ ተመሳሳይ ቢሆንም በተለያዩ ቋንቋዎች የተገለጹ ሐሳቦችን ያካተቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

“ዛሬም ቢሆን ለደካሞች እና ለማያስተውሉ ሰዎች የክርስትና እምነትን እንደ ተራ ነገር የሚቆጠርባቸው ብዙ ሁኔታዎች እንዳሉ ተናግረው፥ እነርሱም እንደ ቴክኖሎጂ፣ ገንዘብ ወይም ሃብት፣ ስኬት፣ ስልጣን እና ጊዜያዊ ደስታ የመሳሰሉ ሌሎችም እንደ ዋስትና የሚመረጡባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።

“ወንጌልን መስበክ እና እውነትን መመስከር አስቸጋሪ የሚሆንባቸው፥ ለምሳሌ አማኞች የሚዘባበቱበት፣ የሚጠሉበት፣ የሚናቁበት ወይም የሚራራቁበት ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸው፥ “ሆኖም ግን እነዚህ በትክክል ለእኛ የሚስዮናዊያን አገልግሎት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ቦታዎች ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

እምነት ማጣት ከሕይወት ትርጉም ማጣት የሚመጣ ነው!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ “እምነት ማጣት ብዙውን ጊዜ የሕይወት ትርጉም ማጣትን፣ ምሕረትን ችላ ማለትን፣ ሰብዓዊ ክብር መጣስን፣ የቤተሰብ ቀውስ እና ሌሎች በርካታ ቁስሎች በማስከተል ኅብረተሰባችንን ይጎዳሉ” ብለዋል።

ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሰው አድናቆት ቢሰጠውም ወደ አንድ ‘ካሪዝማቲክ’ መሪነት ወይም ‘ሱፐርማን’ነት የተቀየረባቸው ብዙ ሁኔታዎች አሉ” ብለው፥ “ይህም በማያምኑት ሰዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በተጠመቁ በርካታ ክርስቲያኖች መካከልም እንደሚከሰት በማስገንዘብ፥ “በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሰዎች በአምላክ የለሽነት መንፈስ ውስጥ ይኖራሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን መነሻ በማድረግ፥ “በመሆኑም ይህ ዓለም ለእኛ የተሰጠን እንደሆነ ለካርዲናሎች አረጋግጠው፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙ ጊዜ እንዳስተማሩን ሁሉ፥ ይህ ዓለም በአዳኙ ክርስቶስ ላይ ያለንን አስደሳች እምነት እንድንመሰክር የተጠራንበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። “ስለዚህ እኛም ደግሞ ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር፥ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ”  ማለት ያስፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ዕለታዊ የመለወጥ ጉዞ

ይህንን ለማድረግ በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግላዊ ግኑኝነት፣ በየቀኑ የመለወጥ ጉዞን ለማድረግ ቁርጠኞች መሆን እንደሚያስፈልግ ተናግረው፥ ከዚያም “እኛም እንደ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁ ማድረግ እንዳለብን እና ለእግዚአብሔር ያለንን ታማኝነት አብረን በመለማመድ የምሥራቹን ለሁሉ መስበክ አለብን” ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ አሥራ አራተኛ በቫቲካን ከካርዲናሎች ጋር ያቀረቡት የመጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴ
ር. ሊ. ጳ. ሊዮ አሥራ አራተኛ በቫቲካን ከካርዲናሎች ጋር ያቀረቡት የመጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴ   (@Vatican Media)

“ይህንን ከሁሉ በፊት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እና የሮም ጳጳስ በመሆን ተልዕኮዬን ስጀምር በግል ለራሴ እናገራለሁ” ብለው፥ መሥዋዕቱ ወደ ሚቀርብበት ወደዚች ከተማ በሰንሰለት ታስሮ የመጣው ቅዱስ ኢግናጤዎስ፥ በሥፍራው ለነበሩት ክርስቲያኖች፥ “ዓለም ሥጋዬን ሲያይ በእውነት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እሆናለሁ” ብሎ መጻፉንም አስታውሰዋል።

ለኢየሱስ ክርስቶስ ቦታ መስጠት

ቅዱስ ኢግናጢዎስ በአውሬዎች እንደሚበላ መናገሩ እውን መሆኑን አብራርተው፥ “ነገር ግን ንግግሩ በጠቅላላ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአገልግሎት ሥልጣንን ተግባራዊ ለሚያደርጉት ሁሉ አስፈላጊ ቁርጠኝነት መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ይህ ቁርጠኝነት ለኢየሱስ ክርስቶስ ቦታን በመስጠት፥ ራስን ዝቅ በማድረግ በምላሹ በሁሉ ዘንድ እውቅና እና ክብር ማግኘት፣ ሌሎችም ኢየሱስን ለማወቅ እና ለመውደድ ዕድል እንዲኖራቸው ለማድረግ ራስን እስከ መጨረሻ ድረስ ለአገልግሎት መስጠት ነው" በማለት አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ “እግዚአብሔር ዛሬ እና ዘወትር ይህንን ጸጋ የቤተ ክርስቲያን እናት በሆነች በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይስጥልኝ” በማለት ስብከታቸውን ደምድመዋል።

 

09 May 2025, 17:50