ር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ የሐዋርያዊ መሪነት መጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴን በመጭው ግንቦት 10 እንደሚያቀርቡ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሐዋርያዊ መሪነት ሥልጣናቸውን የሚጀምሩት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እሑድ ግንቦት 10/2017 ዓ. ም. ከጠዋቱ በአራት ሰዓት ላይ በሚያቀርቡት መስዋዕተ ቅዳሴ መሆኑን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።
በዚህም መሠረት በመጀመሪያዎቹ ሦስት ሳምንታት ማለትም ቅዳሜ ግንቦት 2/2017 ዓ. ም. ከካርዲናሎች ጋር እንደሚገናኙ፣ እሑድ ግንቦት 3/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሰገነት ላይ ሆነው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት የሚቀርበውን ጸሎት እንደሚመሩ፣ ሰኞ ግንቦት 4/2017 ዓ. ም. ከዓለም አቀፍ የዜና ተቋማት ጋር እንደሚገናኙ፣ ዓርብ ግንቦት 8/2017 ዓ. ም. ከዲፕሎማሲ ልኡካን ኃላፊዎች ጋር እንደሚገናኙ፣ እሑድ ግንቦት 10/2017 ዓ. ም. ከረፋዱ በአራት ሰዓት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚቀርበውን የሐዋርያዊ መሪነት ሥልጣን መጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚመሩ፣ ማክሰኞ ግንቦት 12/2017 ዓ. ም. የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ሐዋርያዊ ሃላፊነት እንደሚረከቡ፣ ረቡዕ ግንቦት 13/2017 ዓ. ም. የመጀመሪያውን ጠቅላላ ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን እንደሚጀምሩ፣ ቅዳሜ ግንቦት 16/2017 ዓ. ም. ከቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና ከቫቲካን ግዛት ሠራተኞች ጋር እንደሚገናኙ፣ እሑድ ግንቦት 17/2017 ዓ. ም. ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት የሚቀርበውን ጸሎት አድርሰው፣ የቅዱስ ዮሐንስ ላተራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ እና የታላቋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጳጳሳዊ ባዚሊካ ሐዋርያዊ ሃላፊነት እንደሚረከቡ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።
የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች እና አባላት፣ እንዲሁም ጸሐፊዎች እና የቫቲካን ግዛት ጳጳሳዊ ኮሚሽን ፕሬዚዳንቶች የነበራቸውን ሚና በጊዜያዊነት “donec aliter provideatur” እንዲቀጥሉ ቅዱስነታቸው መፈለጋቸውን መግለጫ ክፍሉ በተጨማሪ አጋርቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ ቀጠሮዎችን ከመያዛቸው ወይም ውሳኔዎችን ከማድረጋቸው በፊት ለተወሰነ ጊዜ የማሰላሰል፣ የመጸለይ እና የመወያየት መብት እንዳላቸው ታውቋል።