የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ እንዴት ይካሄዳል?
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“Eligo in Summum Pontificem” ወይም “እንደ ጠቅላይ ጳጳስ ሆኜ እመርጣለሁ” የሚለው ጽሑፍ 133 መራጭ ካርዲናሎች 267ኛውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ በሚጠቀሙባቸው እያንዳንዱ የድምፅ መስጫ ካርድ ላይ የታተሙ ቃላት ናቸው። የድምጽ መስጫው ካርድ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሲሆን የላይኛው ግማሽ የላቲን ጽሑፍ ያለው ሲሆን ከታች በስተግራ በኩል ያለው ግማሽ ክፍት ቦታ መራጭ ካርዲናል የመረጧቸውን እጩ ስም የሚጽፉበት ነው። “መላው የእግዚአብሔር መንጋ” በሚለው ሐዋርያዊ ሕግ ዝርዝር ውስጥ እንደተደነገገው፥ የድምጽ መስጫ ካርዱ ለሁለት እንዲታጠፍ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።
የድምጽ መስጫ ካርድ እደላ
እያንዳንዱ መራጭ ካርዲናል ቢያንስ ሁለት ወይም ሦስት የምርጫ ካርዶችን ይቀበላል። ካርዶቹ በሥነ-ሥርዓቱ አስተባባሪዎች እንዲታደሉ ይደረጋል። ከዚያም ከፍተኛው ካርዲናል ዲያቆን የምርጫ ድምጾችን የሚቆጥሩ እና የሚመረምሩ ሦስት አባላትን፣ በድምጽ መስጫው ወቅት ሕመም ቢያጋጠማቸው ድምጾቻቸውን የሚሰበስቡ ሦስት የጤና ባለሞያዎችን፣ የድምጽ ቆጠራውን ትክክለኛነት በመገምገም የሚያረጋግጡ ሌሎች ሦስት አባላትን ይሰይማል። ከተሰየሙት መካከል አንዳቸውም በሕመም ወይም በሌሎች ምክንያቶች ሚናቸውን መወጣት ካልቻሉ በምትካቸው አዲስ ስሞች ይዘጋጃሉ። ይህ ደረጃ የምርጫ ቅድመ ምርመራ በመባል ይታወቃል።
ድምጽ መስጠት ከመጀመሩ በፊት ሁሉም መራጮች፥ የካርዲናሎች ኅብረት ዋና ጸሐፊን፣ የጳጳሳዊ ሥርዓተ አምልኮ ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ እና የሥነ-ሥርዓቱ አስከባሪዎችን ጨምሮ ሁሉም ከሲስቲን ጸሎት ቤት ለቅቀው ይወጣሉ። እነርሱ ከወጡ በኋላ ከፍተኛ ካርዲናል ዲያቆን የጸሎት ቤቱን በሮች ይዘጋቸዋል። እንደ አስፈላጊነቱ የታማሚ ካርዲናሎች ድምጽ ለመሰብሰብ ሲሄዱ እና ሲመለሱ ይከፍታቸዋል፣ ይዘጋቸዋልም።
“የእንባ ክፍል”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ከተመረጠ በኋላ ዕጩ ተመራጭ እጩ ተመርጭ ነጭ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልብሶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደሚለብስባት፥ “የእንባ ክፍል” ተብላ ወደምትታወቅ እና ከሲስቲን ጸሎት ቤት አጠገብ ወደምትገኝ ጠባብ ክፍል ያመራሉ።
የድምጽ አሰጣጥ ሂደት
እያንዳንዱ ካርዲናል በቅደም ተከተሉ መሠረት የመረጡትን እጩ ስም በድምጽ መስጫው ካርድ ላይ በመጻፍ እና በማጠፍ፥ ካርዱ እንዲታይ ከፍ በማድረግ ወደ መንበረ ታቦት ይወስድና በዚያም ክዳን ባለው ጽዋ ውስጥ ያስገባል።
እያንዳንዱ መራጭ ካርዲናል በጣሊያንኛ ቋንቋ የተጻፈውን ጮክ አድርጎ ያነበዋል። ትርጉሙም የሚከተለው ነው፥ “ፈራጄ እና ምስክሬ የሚሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እጠራለሁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመረጥ ብዬ ላመንኩት ጳጳስ የምርጫ ድምፄን እሰጣለሁ” ካለ በኋላ የምርጫ ካርዱን ጽዋው ውስጥ አስገብቶ በመንበረ ታቦት ፊት ከሰገደ በኋላ ወደ መቀመጫው ይመለሳል።
ምርጫውን የተሳተፉት ነገር ግን በሕመም ምክንያት ወደ መንበረ ታቦት ድረስ መምጣት ያልቻሉ ካርዲናሎች የታጠፈውን የድምጽ መስጫ ካርድ ለአንደኛው መርማሪ ይሰጣሉ። እርሱም ወደ መንበረ ታቦት አምጥቶ ካስቀመጠው በኋላ በተመሳሳይ መንገድ ቃለ መሐላን ያቀርባል።
ሕመም የሚሰማቸው ካርዲናሎች ከክፍላቸው ሆነው ድምጽ ይሰጣሉ
ካርዲናሎች በሕመም ምክንያት በጸሎት ቤቱ ውስጥ መገኘት ካልቻሉ የእነዚህን ካርዲናሎች ድምጽ የሚሰበስቡ ሦስት የጤና ባለሞያዎች፥ በውስጡ የምርጫ ካርድ እንደሌለበት አስቀድሞ የተረጋገጠውን እና በቁልፍ የታሸገውን ሳጥን ይዘው ወደሚገኙበት ክፍል ይሄዳሉ። የሳጥኑ የላይኛው ክፍል የታጠፈ የድምፅ መስጫ ካርድ የሚገባበት ቀዳዳ አለው። ድምጾች ከተሰጡ በኋላ የጤና ባለሞያዎቹ ሳጥኑን ወደ ጸሎት ቤቱ መልሰው በመራጮች ፊት ከፍተው የምርጫ ድምጽ ካርዶችን ከቆጠሯቸው በኋላ በዋናው ድምጽ መሰብሰቢያ ውስጥ ያስገቧቸዋል።
የምርጫ ድምጽ ቆጠራ
ሁሉም የምርጫ ድምጾች ከተሰበሰቡ በኋላ የመጀመሪያው መርማሪ በድምጽ መስጫ ሳጥኖች ውስጥ የሚገኙ ካርዶችን ለመደባለቅ ሳጥኑን ያናውጣል። ከዚያም የመጨረሻው መርማሪ አንድ በአንድ ከቆጠራቸው በኋላ ወደ ሁለተኛው ባዶ ጽዋ ውስጥ ያስተላልፋል። የድምጽ መስጫዎቹ ቁጥር ከመራጮች ቁጥር ጋር የማይዛመድ ከሆነ ሁሉም የድምፅ መስጫዎች ከተቃጠሉ በኋላ አዲስ ድምጽ የመስጠት ሂደት ይካሄዳል። ቆጠራው ትክክል ከሆነ ጽዋዎቹ ተከፍተው የምርጫ ድምጽ ካርዶች ይነበባሉ።
ሦስቱም የድምጽ መስጫ ካርድ መርማሪዎች በመንበረ ታቦት ፊት ባለው ወንበር ይቀመጣሉ። የመጀመሪያው በድምጽ መስጫው ካርድ ላይ የተጻፈውን ስም ካነበበ በኋላ ለሁለተኛው ያስተላልፋል። እሱም ስሙን አረጋግጦ ለሦስተኛው ያስረክባል። ሁሉ ሰው እንዲሰማው ጮክ ብሎ ካነበበው በኋላ እንዲመዘገብ ያደርጋል። ሁለት ድምጽ መስጫ ካርዶች በአንድ ሰው የተፃፉ እና ተመሳሳይ ስም ካላቸው እንደ አንድ ድምጽ ይቆጠራል። ምንም እንኳን አጠቃላይ ድምጹ ትክክለኛ ቢሆንም ነገር ግን የተለያዩ ስሞችን የሚያሳዩ ከሆነ ሁለቱም ውድቅ ይደረጋሉ።
ሁሉም የድምፅ መስጫ ካርዶች ከተነበቡ እና ከተሰበሰቡ በኋላ የመጨረሻው መርማሪ እያንዳንዱን ድምጽ “መርጫለሁ” የሚል ቃል በተጻፈበት መርፌ ወግቶት በሲባጎ ያስራቸዋል። የሲባጎው ጫፎች ተቋጥረው የድምጽ መስጫ ካርዶቹ ደህንነታቸው በተጠበቀ ሥፍራ ይከማቻሉ።
ተፈላጊው አብላጫ ድምጽ
አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ የሁለት ሦስተኛው አብላጫ ድምፅ ያስፈልጋል። ረቡዕ ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. በተጀመረ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ከተሳተፉ 133 መራጭ ካርዲናሎች መካከል ተመራጩን ለመለየት ቢያንስ 89 ድምጾች ያስፈልጋሉ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዕለቱ ይመረጡ ወይም አይመረጡ የምርጫ ገምጋሚዎቹ የድምጽ ቆጠራውን ሂደት በጥንቃቄ በመከታተል ሁሉም በትክክል መከናወኑን ለማረጋገጥ በተቆጣጣሪዎቹ የተሠሩ ማስታወሻዎችን ይመለከታሉ። ከዚህ በኋላ መራጭ ካርዲናሎች ከሲስቲን ጸሎት ቤት ከመውጣታቸው በፊት ሁሉም የድምፅ መስጫ ካርዶች ለመጀመሪያ ጊዜ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1939 ዓ. ም. ጥቅም ላይ መዋል በጀመረው የብረት ምድጃ ውስጥ እንዲቃጠሉ ይደረጋል። መርማሪዎቹ ይህንን የሚያከናውኑት በከፍተኛ ዲያቆን ካርዲናል በተሰየሙት በካርዲናሎች ኅብረት ዋና ጸሐፊ እና በሥነ-ሥርዓት አስፈጻሚ አባላት እገዛ ነው።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2005 ዓ. ም. የተገጠመው ሁለተኛ ምድጃ ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከሚታይ የጭስ ማውጫ ጋር የተገናኘ ነው። ለጭሱ የሚፈለገው ማለትም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያልተመረጡ ከሆነ ጥቁር ጭስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተመረጡ ከሆነ ነጭ ጭስ እንዲወጣ ለማድረግ ኬሚካሎች የጨመርበታል። ሁለት ተከታታይ ድምጽ መስጫ ሂደቶች የተካሄዱ እንደሆነ ሁለቱም የምርጫ ድምጾች በሁለተኛው ዙር መጨረሻ አንድ ላይ እንዲቃጠሉ ይደረጋል።
የድምጽ አሰጣጥ ዙሮች እና የአስተንትኖ ጊዜያት
ድምጽ የመስጠት ሥነ-ሥርዓት በቀን አራት ጊዜ ማለትም ጠዋት ሁለት ጊዜ ከሰዓት በኋላ ሁለት ጊዜ ይካሄዳል። ከሦስት ቀናት በኋላ እጩ ካልተመረጠ፣ ድምጽ የመስጠቱ ሥነ-ሥርዓት ከፍተኛ ካርዲናል ዲያቆን ከሚመሩት አጭር መንፈሳዊ ምክር እና ጸሎት ጋር መደበኛ ባልሆኑ ውይይቶች ለአንድ ቀን እንዲቋረጥ ከተደረገ በኋላ እንደገና ይጀምራል። በየሰባት ተጨማሪ ዙሮች ያለ ስኬት ከቀረ በቅድሚያ በሊቀ ካርዲናል ቄስ፣ በኋላም አስፈላጊ ከሆነ በሊቀ ካርዲናል ጳጳስ መሪነት በጸሎት የማሰላሰል እና የዕረፍት ጊዜ ይመደባል።
ከ21 ዙር ድምጽ መስጠት በኋላ አሁንም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ካልተመረጡ ለጸሎት፣ ለውይይት እና ለአስተንትኖ የመጨረሻ ጊዜ ይመደባል። ነገር ግን በዚህ ጊዜ ካርዲናሎቹ ባለፈው ዙር ብዙ ድምጽ ካገኙ ሁለት እጩዎች መካከል አንዱን ሊመርጡ ይችላሉ። በዚህም ጊዜ የሁለት ሦስተኛ ድምጽ ያስፈልጋል። ብዙ ድምጽ ያገኙ ሁለቱ እጩዎች ድምጽ እንዲሰጡ አይፈቀድላቸውም።