MAP

ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ፥ የካርዲናሎችን ዝግ ጉባኤ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራው በጸሎት ጠየቁ

የካርዲናሎች ጉባኤ መሪ ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ቀደም ብሎ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ በመሩበት ወቅት ባሰሙት ስብከት፥ የብጹዓን ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤን መንፈስ ቅዱስ እንዲመራው በጸሎት እንጠቃለን ሲሉ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕነታቸው እንዲሁም ካርዲናሎች አዲሱን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለመምረጥ ወደ ሲስቲን ጸሎት ቤት በሚገቡበት ወቅት በእምነት እና በጸሎት አንድ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበው፥ በዚህ አስቸጋሪ እና ውስብስብ በሆነ ጊዜ የሚመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያን እና የሰው ልጅ የሚያስፈልጋቸው ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ለሚቀጥሉት ዓመታት የሚመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ በሚጀመርበት ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. ማለዳ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በቀረበው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከካርዲናሎች ጋር ከአምስት ሺህ በላይ ምእመናን ተካፋይ ሆነዋል። መስዋዕተ ቅዳሴውን የመሩት የካርዲናሎች ጉባኤ መሪ ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ በዕለቱ ባሰሙት ስብከት፥ “ከሁሉም የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጋር በእምነት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ባላቸው ፍቅር እና በራስ የመተማመን መንፈስ አንድነት ይሰማናል” ብለዋል።

በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደተገለጸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ሐዋርያት ከኢየሱስ እናት ማርያም ጋር አንድ ሆነው በጸሎት ይተጉ እንደ ነበር ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ በስብከታቸው አስታውሰው፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የተሰበሰቡትም እንዲሁ አብረው እየጸለዩ እንደሆነ ተናግረዋል።

የካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ከመጀመሩ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በቀረበው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት፥ “በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከመንበረ ታቦት አጠገብ በተቀመጠው እና በቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር ላይ የቆመውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ጠቅሰዋል።

በእምነት እና በጸሎት መተባበር

ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ በስብከታቸው፥ በዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንለምናለን ብለው፥ “የእርሱን ብርሃን እና ብርታት በመጠየቅ አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሚመረጡበት ይህ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እና የሰው ልጅ አስቸጋሪ እና ውስብስብ በሆነ የታሪክ ለውጥ ወቅት መሆኑን አብራርተዋል።

መራጭ ካርዲናሎች ከፍተኛውን የሰው ልጅ እና የቤተ ክርስቲያን ሃላፊነት የሚወጡበት ልዩ ምርጫን ለማካሄድ በሚዘጋጁበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስን በመማጸን ወደ እርሱ መጸለይ ብቸኛው እና ትክክለኛው አስተሳሰብ እንደሆነ አስረድተው፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የቤተ ክርስቲያንን እና የሰብዓዊነት ተግባርን በአእምሯችን እና በልቡናችን መያዝ ያለበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ወሰን የሌለው ፍቅር

በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ በተነበበው ወንጌል ላይ እንደተገለጸው፣ ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ሁሉን ሰው እንደወደደ ሁሉ ሰዎችም እርስ በእርሳቸው እንዲዋደዱ ጥሪ አቅርበው፥ ይህም እግዚአብሔር አዲስ ትእዛዝ ብሎ የጠራው ወሰን የለሽ የፍቅር መልዕክት እንደሆነ አስረድተዋል።

ለወንድማማችነት ፍቅር እና አንድነት ተጠርተናል

ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ በስብከታቸው፥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የተነበበው ወንጌል ለወንድማማችነት ፍቅር፣ ለጋራ መረዳዳት፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ለዓለም አቀፍ የሰው ልጅ ወንድማማችነት የሚጠራ መሆኑን አስታውሰዋል። የጴጥሮስ ተተኪ ቁልፍ ተግባር በሁሉም መልኩ ኅብረትን ማፍራት፣ ክርስቲያኖች በሙሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራቸው፣ ጳጳሳት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ኅብረት እንዲኖራቸው፥ ጳጳሳት በመካከላቸው ኅብረት እንዲኖራቸው፥ በሰዎች፣ በሕዝቦች እና በባህሎች መካከል ሙሉ በሙሉ ኅብረት እንዲኖር የሚያሳስብ እንደሆነ አስረድተዋል።

በልዩነት ውስጥ የሚታይ አንድነት

የወንጌል ምንባቡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ያዘጋጀውን መንገድ በመከተል የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የመጠበቅ ግዴታን ያስታውሰናል ብለው፥ “ይህ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ተግባራዊ የሚሆነው በክርስቶስ ፈቃድ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

“እያንዳንዱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተልዕኮውን የሚፈጽመው ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በመተባበር በምድር ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚወክል እና ቤተ ክርስቲያን የታነጸችበት ዓለት እንደሆነ በመግለጽ፥ (ማቴ. 16፡18) የአዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መመረጥ ተራ የሰዎች መተካካት አይደለም” ሲሉ አስረድተዋል

በጸሎት መተባበር

መራጭ ካርዲናሎች በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ድምፃቸውን ሲሰጡ፥ ባለፉት መቶ ተከታታይ ዓመታት እውነተኛ ቅዱሳን እና ታላላቅ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የሰጠን መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሰው ልጅ መልካም ነገር ባደረገበት በእግዚአብሔር ፍቅር አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን እንድንሰጠን መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል።

“እግዚአብሔርን የመርሳት ዝንባሌ ባለው ዓለማችን ውስጥ የሁሉን ሰው ኅሊና የሚያነቃቃ፣ በዘመናዊው ኅብረተሰብ ውስጥ ያለውን ሥነ ምግባራዊ እና መንፈሳዊ ኃይል የሚያውቅ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሰጠን ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ” ብለዋል።

የሰው ልጆች አብረው የሚኖሩበት እና የወደፊት ትውልዶች የሚመኩበትን ሰብአዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን ዓለም ከቤተ ክርስቲያን ብዙ እንደሚጠብቅ አስገንዝበው፥ በቤተ ክርስቲያን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት መንፈስ ቅዱስ የብፁዓን ካርዲናሎችን ልቦና እንዲያበራ እና ጊዜያችን በሚፈልገው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ላይ እንዲስማሙ በመመኘት ስብከታቸውን ደምድመዋል።

 

 

 

 

07 May 2025, 16:48