MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሐዋርያዊ ተልዕኮዋቸው ታማኝ እንደ ነበሩ ተገለጸ

የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀ ካኅን ብፁዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ፥ የብርሃነ ትናሳኤው ሦስተኛ እሑድ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሕልፈት ዘጠነኛ እና የመጨረሻ የሐዘን ቀን መስዋዕተ ቅዳሴን መርተዋል። ብፁዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ እሑድ ሚያዝያ 26/2017 ዓ. ም. በአሥራ አንድ ሰዓት ላይ በተጀመረው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሐዋርያዊ ተልዕኮዋቸው ታማኝ እንደ ነበሩ ገልጸው፥ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተልዕኮ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሰው ልጆች በአገልግሎት የተገለጸ ፍቅር መሆኑንም አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የቅዱስ ጴጥሮስ እና የሐዋርያት ተልዕኮ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሰው ልጆች በሙሉ በአገልግሎት በኩል የተገለጸ ፍቅር ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ማምበርቲ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በዚሁ በእግዚአብሔር ፍቅር በመታገዝ ኃይላቸው እስኪያልቅ ድረስ ሐዋርያዊ ተልዕኮዋቸውን በታማኝነት እንደፈጸሙ ገልጸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማምበርቲ፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ቀጥሎ በታወጁት ዘጠኝ ተከታታይ የሐዘን ቀናት መካከል በመጨረሻው ዕለት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ላሰሙት ስብከት መሠረቱ ከዮሐንስ ወንጌል የተወሰደ እንደ ነበር ተመልክቷል።

በብርሃነ ትንሳኤው ሦስተኛው እሁድ ላይ የተነበበው ይህ ምንባብ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ በጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻ ከበርካታ ሐዋርያት ጋር መገናኘቱን እና ተልዕኮን ለጴጥሮስ ሲሰጠው “ተከተለኝ” ማለቱን የሚተርክ ክፍል እንደ ነበር ታውቋል።

ብጹዓን ካርዲናሎች ዘጠኝ የሐዘን ቀናት በመስዋዕተ ቅዳሴ በጀመሩበት ወቅት
ብጹዓን ካርዲናሎች ዘጠኝ የሐዘን ቀናት በመስዋዕተ ቅዳሴ በጀመሩበት ወቅት   (@VATICAN MEDIA)

የወንጌልን ደስታ ለሰዎች ማውጅ

ብጹዕ ካርዲናል ማምበርቲ፥ በዕለቱ የተነበበው የወንጌል ክፍል በተለይ ከሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. ጀምሮ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሚሆኑትን አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መምረጥ በሚጀመርበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ከምታቀርበው ጸሎት ጋር የሚስማማ እንደ ሆነ እና ከሐዋርያት ሥራ ተወስዶ የተነበበው የመጀመሪያ ምንባብም እንዲሁ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ሌሎች ሐዋርያት፥ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል” ማለታቸውን የሚገልጽ መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል” የሚለውን የሐዋርያቱን ውሳኔ በመጠቀም ኃያላንን ያስጠነቅቁ እንደ ነበር እና ለሰው ልጆች በሙሉ የወንጌልን ደስታ፣ የመሐሪ አባት እና የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት እንዳወጁ አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህንን በተጨባጭ ያሳዩት በአስተምህሮአቸው፣ በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው እና በአኗኗራቸው እንደ ነበር የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ማምበርቲ፥ “በብርሃነ ትንሳኤው እሑድ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሰገነት ላይ ቆመው ስቃያቸውን፣ ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን ሕዝብ እስከ መጨረሻው ለማገልገል ያላቸውን ድፍረት እና ቁርጠኝነት መስክረዋል” ሲሉ ገልጸዋል።

የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ትሁት ፍቅር

“በልቡ ውስጥ ባለው ትንሽ ፍቅር ኢየሱስ ክርስቶስ መርካቱን ያወቀው ስምዖን ብቻ ነው” ያሉትን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ቃል ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ማምበርቲ፣ ታማኝ ያለመሆን ስቃይን ለሚያውቀው ለዚህ ደቀ መዝሙር ተስፋ የሚሰጠው ይህ መለኮታዊ መረዳት እንደሆነ ገልጸው፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሐዋርያው ጴጥሮስ መምህሩን ይከተል የነበረው ደካማነቱን በሚገባ በማወቅ እንደ ነበር አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ማምበርቲ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በርዕሠ ሊቃነ ጵጵስናቸው 25ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ እና በሐዋርያው ጴጥሮስ መካከል የተደረገውን ተመሳሳይ ውይይት በየቀኑ አደርጋለሁ” ማለታቸውን አስታውሰው፥ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፥ “ጌታ ሆይ! አንተ ሁሉንም ነገር ታውቃለህ፣ እንደምወድህም ታውቃለህ” በሚሉት ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚያበረታታቸው ይሰማቸው እንደ ነበር እና ከዚያም ኢየሱስ እንደገና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ይሰጣቸው እንደ ነበር አስታውሰዋል።

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሕልፈትን በማስመልከት የተደረገ የሐዘን ቀን የመጨረሻ መስዋዕተ ቅዳሴ
የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሕልፈትን በማስመልከት የተደረገ የሐዘን ቀን የመጨረሻ መስዋዕተ ቅዳሴ   (@VATICAN MEDIA)

የአምልኮ አስፈላጊ አቅጣጫ

በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ከዮሐንስ ራዕይ ተወስዶ በተነበበው ላይ ለእግዚአብሔር እና ለበጉ የቀረበውን ውዳሴ እና አምልኮን የሚገልጸውን ሁለተኛውን ምንባብ ብፁዕ ካርዲናል ማምበርቲ አስታውሰዋል። ስግደት ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ እና ለምእመናን ሕይወት ወሳኝ ገጽታ እንደ ሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙ ጊዜ አጽንዖት መስጠታቸውን የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ማምበርቲ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2024 ዓ. ም. በተከበረው የብርሃነ ጥምቀቱ በዓል ስብከታቸው፥ “የስግደት ልማድ ማጣት ብቻ ሳይሆን ከስግደት የሚገኘው ኃይል ስለሚጎድለን ውበቱን መልሰን ለማግኝት መስገድ ይኖርብናል” ሲሉ መናገራቸውን አስታውሰዋል።

“የማምለክ ችሎታ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ ውስጥ በግልጽ ይታይ ነበር” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ማምበርቲ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጠንካራ ሐዋርያዊ ሕይወት እና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ተግባራቸው ዘወትር በቅዱስ ኢግናጤዎስ የሕይወት ተሞክሮ የተቀረጹ እና በረጅም የጸሎት ጊዜያት ውስጥ የተመሠረቱ መሆናቸውን ገልጸው፥ በዚህ ፍቅር ላይ ማሰላሰል ከዓለም የሚለየን ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የሚያደርሰን እና በጥልቀት እንድንኖር የሚረዳን ነው” በማለት አስረድተዋል።

የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀ ካኅን ብፁዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ በስብከታቸው ማጠቃለያ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእመቤታችን ቅድስትን ድንግል ማርያም ዕይታ ስር ሆነው ሐዋርያዊ አገልግሎት ማበርከት መቻላቸውን እና የሮም ከተማ ሕዝብ ጠባቂ የሆነች የታላቋ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ባዚሊካን 126 ጊዜ በመጎብኘት ጸሎት ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።

አስከሬናቸውም በባዚሊካው ውስጥ በሚገኝ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል አጠገብ በክብር መቀመጡን ገልጸው፥ ምእመናን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ነፍስ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ እና የእኛ እናት ለሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በአደራ እንዲሰጡ በማለት ብፁዕ ካርዲናል ማምበርቲ አሳስበዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ ስብከታቸውን ሲያሰሙ
ብፁዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ ስብከታቸውን ሲያሰሙ   (@VATICAN MEDIA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በማስታወስ የቀረበ ጸሎት

ስለ ምእመናን በሚቀርቡ ጸሎቶች ውስጥ እግዚአብሔር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ነፍስ በመንግሥቱ እንዲቀበል፣ በቤተ ክርስቲያን ጸሎት ላይ ያላቸውን እምነት በማመን፣ ሰብዓዊ ደካማነታቸውን ይቅር በማለት  ለታማኝ አገልጋዮች በገባው ቃል መሠረት ሽልማት እንዲሰጣቸው ቤተ ክርስቲያን ጸሎቷን አቅርባለች  

እሑድ ሚያዝያ 26/2017 ዓ. ም. አንዳንድ ብጹዓን ካርዲናሎች በሮም በሚገኙ ቤተ ክርስቲያኖቻቸው ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ካሳረጉ በኋላ በነጋታው ሰኞ ዕለት ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ እንዲሁም በድጋሚ ከሰዓት በኋላ በአሥራ አንድ ሰዓት ላይ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን አካሂደዋል። ማክሰኞ ሚያዝያ 27/2017 ዓ. ም. ጠዋት ብቻ ለመሰብሰብ የታቀደ ቢሆንም ካስፈለገም ከሰዓት በኋላም ሊሰበሰቡ እንደሚችሉ የጉባኤው መርሃ ግብር አመላክቷል።

 

05 May 2025, 16:39