ሌዮ 14ኛ፥ አዲሱ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ተሰየሙ
የካርዲናሎች ጉባኤ ሮበርት ፍራንሲስ ፕሬቮስትን 267ኛው የሮም ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እና የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አድርጎ መርጧቸዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባ ለተሰበሰቡት ታዳሚዎች ይህን ያበሰሩት የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀ አገልጋይ ብጹዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ ናቸው።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በቅድሚያ፥ “ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!” በማለት በአደባባዩ ለተገኘው በርካታ ቁጥር ላለው ሕዝብ ሰላምታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀ አገልጋይ ብጹዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ ቀደም ብሎ ባሰሙት ንግግር፥ “ደስታን እነግራችኋለሁ”፣ “ጳጳስ አለን!” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መመረጣቸውን አብስረው፥ “እጅግ የተከበሩ የሮም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካርዲናል ሮበርት ፍራንሲስ ፕሪቮስት፥ ሌዮ 14ኛ የሚል አዲስ ስም ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ሊቀ አገልጋይ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ማዕከላዊ ሰገነት በኩል ቆመው ባሰሙት አጭር ንግግር፥ “ሃቤሙስ ፓፓም” ውይም “ጳጳስ አለን” በማለት ለሮም ከተማ ነዋሪዎች እና ለመላው ዓለም ሕዝብ ካርዲናል ሮበርት ፍራንሲስ ካርዲናል ፕርቮስት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ ተብለው መመረጣቸውን አብስረዋል።
09 May 2025, 01:21