ፓትሪያርክ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ ከር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ ጋር በኒቂያ ለመገናኘት እንደሚመኙ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
እሑድ ግንቦት 10/2017 ዓ. ም. ጠዋት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በቀረበው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ሐዋርያዊ የአገልግሎት መጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴን ለተሳተፉት ለቁስጥንጥኒያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ 1ኛ በቫቲካን አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ጋር ሰኞ ግንቦት 11/2017 ዓ. ም. ጠዋት በቫቲካን ለመጀመሪያ ጊዜ በግል ሲገናኙ ስጦታዎችን ተለዋውጠው ለሰላም እና ለአካባቢ ጥበቃ ባላቸው የጋራ ቁርጠኝነት ላይም ተወያይተዋል። በኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ እንደገና ለመገናኘት ፍላጎት እንዳላቸው ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ ገልጸዋል።
ለብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ በቫቲካን የተደረገላቸው አቀባበል
የፓትሪያርኩ ጽሕፈት ቤት በመግለጫው፥ በቫቲካን ለብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ የተደረገላቸው አቀባበል እና በጋራ ያደረጉት ውይይትም አስደሳች እንደ ነበር ገልጾ፥ ፓትሪያርኩ በአዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ወቅት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት መላካቸውን አስታውሷል።
በውይይታቸው ወቅት ከተነሱት ጉዳዮች በተጨማሪ፥ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም በቁንስጥንጥኒያው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እና በሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ሥነ-መለኮታዊ ውይይት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፥ ማኅበራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እና ሰላም ለማስከበር የሚደረጉ ድጋፎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተወያይተዋል።
የተፈጥሮ አካባቢን በማስመልከት ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” በሚል ርዕሥ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ አስተምህሮ ውስጥ ዓለም አቀፍ የፍጥረት ቀን እንዲከበር የቀረበው ጭብጥ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ተነሳሽነት የተገኘ እንደ ነበር ታውቋል።
ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ ከሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የወንድማማችነት ግንኙነት እና ትብብር እንደ ነበራቸው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ ጋር ባደረጉት ውይይት ጠቅሰው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ ወር 2016 ዓ. ም. ወደ ሌስቦስ ደሴት ያደረጉትን የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ሳይዘነጉ ከአቴንስ እና ከመላው ግሪክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሒሮኒሞስ ጋር በመሆን ከአሥር ጊዜ በላይ ሲሰበሰቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ውይይት እና ትብብር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በበኩላቸው፥ ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ እሑድ ግንቦት 10/2017 ዓ. ም. ጠዋት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በቀረበው የሐዋርያዊ አገልግሎት መጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ በመገኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በክርስቲያኖች መካከል ውይይትን እና ትብብርን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበት፥ ከዓለም አቀፍ የዜና ተቋማት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰበሰቡበት ወቅት እንደገለጹት፥ በያዝነው ዓመት ወደ ቱርክ ለመጓዝ ባላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ከፓትርያርኩ ጋር በመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ መታሰቢያን በአንድነት ለማክበር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በኒቂያ ሐዋርያዊ ጉብኝት የማድረግ ፍላጎት
ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ ቲቪ2000 ለተባለ ካቶሊካዊ ቴሌቪዥን በሰጡት አስተያየት፥ ኦርቶዶክስ እና ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ለመላው የክርስትና እምነት እና በዓለማችን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን በሚያደርጉት ጥረት ታላቅ እርካታ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በኒቂያው ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ለመገኘት ወደ ቱርክ መምጣት እንደሚፈልጉ ማረጋገጣቸውን የገለጹት ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከባድ ሕመም ቢገጥማቸውም ያንን አስፈላጊ የሆነውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ተስፋ እና ፍላጎት እንደ ነበራቸው ተናግረዋል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ጋር ቀጠሮ ባይዙም ነገር ግን የቅዱስ እንድርያስ ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት በቀጥዩ ዓመት ኅዳር ላይ እንደሚገናኙ ተስፋ በማድረግ፥ ይህም ፍላጎታቸው እና ምኞታቸው እንደ ሆነ ገልጸው፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ምናልባትም ከቫቲካን ውጭ በሚያደርጉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወደ ኒቂያ መጥተው በቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን ይፋዊ ጉብኝት ቢያደርጉ ለእኛ ክብር ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ወዳጃቸው የነበሩ ር. ሊ. ጳ. ፍራንቸስኮስን በጸሎት ማስታወስ
“የተወደዱ እና የተከበሩ” ያሏቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ያስታወሱት ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ፥ በጵጵስና ዘመናቸው ለቤተ ክርስቲያን እና ለሰው ልጆች በሙሉ መልካም ነገርን ለማድረግ መተባበራቸውን በማስታወስ፥ ለመታሰቢያነት እንዲሆን በመካነ መቃብራቸው አበባን በማስቀመጥ ጸሎት ማድረሳቸውን ገልጸው፥ “በሰማዩ ቤታቸው ሆነው በጸሎታቸው እንደሚያስታውሱ እና ዛሬ ማለዳ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ጋር በመሆን ወንድምነታችንን፣ ፍቅራችንን እና ወዳጅነታችንን የገለጽን በሙሉ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ያለንን የወደፊት ራዕያችን፣ የተስፋችን እና የጋራ ወንድማማችነት አደራን ለእግዚአብሔር እንሰጣለን” ብለዋል።