ሊቀ ጳጳስ ብሮግልዮ አዲስ የተመረጡትን ር. ሊ. ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ‘መከራ ውስጥ ለምትገኘው ዓለም አዲስ የተገኙ እረኛ' በማለት ተቀብለዋቸዋል
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት ሊቀ ጳጳስ ቲሞቲ ብሮግሊዮ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መመረጣቸው ይፋ ከተደረገ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ‘በብጹአን ካርዲናሎቹ ምርጫ በጣም መደሰታቸውን’ ገልጸው፥ በውጤቱ መገረማቸውን፥ ሆኖም ግን ጥልቅ ደስታ እንደተሰማችው እና በአዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
“ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በእርግጠኝነት ከልቤ ጸሎት አደርጋለሁ” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ተልዕኮዋቸውን በሰላም እንዲጀምሩ እና ስኬታማ እንዲሆኑም ጭምር እጸልያለሁ ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ብሮግሊዮ የዩናይትድ ስቴትስ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት አካል ሆነው በሮም ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ወቅት፣ እንዲሁም በሲኖዶሳዊ ጉባኤ ወቅት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ተገናኝተው እንደነበር በመግለጽ፥ ተግባቢ፣ ግልጽ እና ለመተባበር እውነተኛ ፍላጎት ያላቸው ሰው እንደነበሩ አስታውሳለው ብለዋል።
ሊቀ ጳጳሱ አክለውም “በሁለቱም አጋጣሚዎች እሳቸውን ባገኘዋቸው ወቅት በጣም ጨዋ እና ትሁት፣ ብሎም ለመረዳዳት እና አብሮ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል፤ ለዚህም በጣም አመስግናለሁ” በማለት ገልጸዋል።
ስማቸው የሚያስታውሰን ነገር ምንድን ነው?
“ሊዮ” የሚለውን ስም ከቤተክርስቲያኒቷ የበለጸገ ታሪክ ጋር ጥልቅ ትስስር እንዳለው የሚታወቅ ሲሆን፥ በተለይም ከዚህን በፊት እንደ ጎረጎሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ 1878 እስከ 1903 ዓ.ም. ድረስ ቤተክርስቲያኒቷን ለ 25 ዓመታት የመሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ በካቶሊክ ማሕበራዊ አስተምህሮ ላይ በሰሩት ታላቅ ሥራ እና በ 1891 ዓ.ም. ደግሞ የሠራተኞች መብትን አስመልክተው በፃፉት ‘ሬረም ኖቫረም’ ተብሎ በሚጠራው ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው ይታወሳሉ።
ሊቀ ጳጳስ ብሮግሊዮ እንደተናገሩት አዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመረጡት ሥም፥ “የቤተ ክርስቲያንን ማኅበራዊ አስተምህሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልፅ የተናገሩትን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛን ያስታውሰናል” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ይህ ሥም ስለ አዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የዘር ሃረግም እንደሚገልጽ የጠቆሙት ሊቀ ጳጳሱ፥ “ሊዮ የዘር ሃረጋቸው ከሮም አከባቢ ስለሆነ፥ በዋናነት የሮም ሰዎች በጣም ደስተኞች ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
የሰላም ጥሪ
ሊቀ ጳጳስ ብሮግልዮ ዓለማችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ በማጉላት፥ በዓለም ዙሪያ በተከሰቱት በርካታ ቀውሶች ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰላም እና የውይይት ድምጽ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
“በዓለማችን ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ በቀጠሉት ሁኔታዎች ሁላችንም በጣም የተጨነቅን ይመስለኛል” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ በአሁኑ ወቅት ፓኪስታን እና ህንድ እየገቡበት ያለው ቀውስ ያሳስበኛል፥ ይህ ብቻ ሳይሆን በዩክሬን እና በመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም በብዙ የአፍሪካ ክፍሎች ውስጥም ጭምር ቀውሱ ተባብሶ መቀጠሉን ማስታወስ አለብን ካሉ በኋላ፥ አዲስ የተመረጡት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስለ ሰላም መናገራቸው አስፈላጊ መሆኑን አሳስበው፥ “በዓለማችን ውስጥ ሰላም እና ውይይትን የበለጠ ሊያበረታቱ የሚችሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
የተባበረች ቤተ ክርስቲያን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስለ ተባበረች ቤተ ክርስቲያን በተናገሩት ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት ሊቀ ጳጳስ ብሮሊዮ፥ ይህ መልዕክት ለዩናይትድ ስቴትስ ህዝብም ጭምር ጠቃሚ እንደሆነ በማመላከት፥ “መማር ካለብን ነገሮች ውስጥ አንዱ እርስ በርስ መደማመጥ ነው” ካሉ በኋላ፥ “ላንስማማ እንችላለን፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ነው የተፈጠረው፣ ይሄ መቼም ቢሆን መረሳት የለበትም፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን መልዕክት እንደምንሰማው ተስፋ አደርጋለሁ፥ ይህ አንድ እንድንሆን እና የውይይት መሳሪያዎች እንድንሆን ያቀረቡልን ግብዣ ነው” በማለት አስረድተዋል።
ሁለንተናዊ እረኛ
ሊቀ ጳጳስ ብሮግሊዮ ከዚህም በተጨማሪም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን ዓለም አቀፋዊ ልምድ በማስታወስ፥ ብጹእነታቸው የፈረንሣይ እና የጣሊያን የካበተ ልምድ ስላላቸው፣ ብሎም በላቲን አሜሪካ ለረጅም ጊዜያት የሃዋሪያዊ አገልግሎት ልምድ ስላላቸው ለዓለም አቀፉ አገልግሎታቸው ትልቅ ስጦታ እና ግብዓት ነው ብለዋል።
“በተለያዩ የዓለም ክፍሎች መኖር ትልቅ ለውጥ ያመጣል” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ “ይህም በመሆኑ ቤተክርስቲያኗን ለመምራት የሚረዳቸውን ጥልቅ እይታ እና እምቅ አቅም ስለሚሰጣቸው፣ ይህ በጣም ጥሩ ይመስለኛል” ካሉ በኋላ፥ እንዲህ ያለው ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ ቤተክርስቲያን “በራሷ ጓሮ ውስጥ እንዳትጠፋ ይረዳል” በማለትም አክለዋል።
የሁሉም አገልጋይ
ሊቀ ጳጳስ ብሮግሊዮ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ያደረጉት ንግግር በጣሊያንኛ እንዲሆን መወሰናቸውን በመጥቀስ፥ ቋንቋ ለሃዋሪያዊ አገልግሎት ያለውን ጠቀሜታ አስገንዝበዋል።
“የሮም ጳጳስ እንደመሆናቸውም ጭምር፣ ጣልያንኛ መናገር አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉ የተናገሩት ሊቀ ጳጳሱ፥ ይህ ምርጫ በተለይም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በቅርቡ ከዚህ ዓለም ድካም ከማረፋቸው አንጻር፥ ለስፓኒኛ ተናጋሪ ካቶሊኮች የሚሰጠውን ምቾት ጠቅሰው፥ “አዲሱ አገልጋያቸው ልባቸውንም ሊነካው እንደሚችል ማየታችን የሚያበረታታ ነው” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ብሮግሊዮ በመጨረሻም ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “መልካም ጊዜ እንዲኖራቸው እና በአገልግሎታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ እመኛለሁ” በማለት ምኞት እና ጸሎታቸውን አቅርበዋል።