MAP

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ቴክኖሎጂ ሁሉንም ሰው ሊጠቅም እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሚያዝያ ወር እንዲሆን ያዘጋጁትን የጸሎት ሐሳብ ይፋ አድርገዋል። በዓለም አቀፉ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው ቴክኖሎጂ ሁሉንም ሰው በተለይም እጅግ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ሊያገለግል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና አጠቃቀማቸውን በማስመልከት ባቀረቡት ሃሳብ፥ ቴክኖሎጂ የሰውን የእርስ በርስ ግንኙነትን መተካት እንደማይችል ነገር ግን ሰብዓዊ ክብርን ሊያስጠብቁ እንደሚችሉ እና የዘመናችንን ችግሮች መጋፈጥ እንዲችሉ ለማድረግ እንደሚችሉ ተስፋ መኖሩን በወርሃዊ የጸሎት ሃሳባቸው ገልጸዋል።

በማኅበራዊ አውታረመረቦች ዓለም ውስጥ

ዓለም በማኅበራዊ ሚዲያ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው የሰው ሠራሽ አስተውሎት በተጥለቀለቀበት ጊዜ “ቴክኖሎጂ እግዚአብሔር የሰጠን የማሰብ ችሎታ ፍሬ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው፥ ሆኖም ግን አላግባብ መጠቀም አሉታዊ ውጤቶችን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች መገለልን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ እና በቴክኖሎጂ አማካይነት እውነተኛ የእርስ በርስ  ግንኙነት ማድረግ እንደማይቻል ገልጸው፥ ከሰዎች ጋር ፊት ለፊት ሳይሆን ነገር ግን በስልካችን ላይ ብዙ ጊዜን የምናሳልፍ ከሆነ ችግር ሊያስከት እንደሚችል አስረድተዋል።

“የእጅ ስልክን ጨምሮ በተለያየ መንገድ እየጨመረ የመጣው የማኅበራዊ መገናኛ መሣሪያዎች አጠቃቀም ከጀርባው የሚያወሩ፣ የሚስቁ እና የሚያለቅሱ እውነተኛ ሰዎች መኖራቸውን እንድንረሳ ያደርገናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በዚህም የኢንተርኔት ላይ ጥቃት እና ጥላቻ በማኅበራዊ ሚዲያ አውታረ መረቦች ላይ መስፋፋት እንደሚጀምር ተናግረዋል። ቴክኖሎጂ ጥሩ ቢሆንም ሌሎችን ወደ ጎን በማለት ጥቂት ሰዎችን ብቻ የሚያገለግል ከሆነ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የሥራ ዕድል፣ የትምህርት እና ሌሎች የእኩልነት ማጣቶችን ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂ በሰው ልጅ አገልግሎት

እነዚህን አደጋዎች ለመከላከል ሁሉም ሰው ቴክኖሎጂን በአገልግሎት ላይ እንዲያውለው ያበረታቱት ቅዱስነታቸው፥ ቴክኖሎጂ ሰዎችን ለማስተባበር፣ የተቸገሩትን ለመርዳት፣ የሕሙማንን ሕይወት ለማሻሻል፣ የግንኙነት ባህልን ለማዳበር እና ምድራችንን ከውድመት ለማትረፍ እንደሚያግዝም አስረድተዋል።

ቴክኖሎጂ የተፈጠረው የሰውን ልጅ ከእውነታ እና ከተጨባጭ ግንኙነት ለማራቅ አለመሆኑን አስረድተው፥ በመሆኑም ሁሉም ሰው በእጅ ስልክ ላይ የሚያጠፋውን ረጅም ጊዜ በመገደብ እርስ በርስ በአካል መገናኘት እንደሚገባ አሳስበዋል። “ዋናው ጉዳይ ቴክኖሎጂን ከግንኙነት ጋር በማመጣጠን እያንዳንዳችን ወንድማማቾች፣ እህትማማቾች እና የአንድ አባት ልጆች መሆናችንን መገንዘብ መቻል ነው” ብለዋል።

 

08 Apr 2025, 17:23