ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ቤተ ክርስቲያን በአንድነት የሚጓዝ የእግዚአብሔር ሕዝብ ነው” ሲሉ አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የክርስቲያን ደስታ ዘወትር ሁሉን ያሚያካትት እና ለሁሉም የተሰጠ ነው” በማለት ከመጋቢት 22-25/2017 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን ውስጥ ሁለተኛ ዙር የሲኖዶሳዊነት ጉባኤ በማካሄድ ላይ ለሚገኙት የጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያናት ተወካዮች ገልጸዋል።
አራት የማዳመጥ እና የማስተዋል ጉዞ ዓመታት
የጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2021 የጀመረችው ሲኖዶሳዊ ጉዞ የመጨረሻውን “ትንቢታዊ” ምዕራፍ የሚያመላክት ሲሆን፥ ይህም በጣሊያን ውስጥ ያለውን ተልእኮ በጋራ ኃላፊነት እና በማስተዋል መንፈስ ለማብራራት፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ራዕይ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ታውቋል።
“ደስታ” የሚለው የጉባኤው መሪ ቃል፥ በእነዚህ አራት ዓመታት የመደማመጥ እና የማስተዋል ሂደት ውስጥ ከ1000 በላይ ጳጳሳት እና ከኢጣሊያ የተውጣጡ የሀገረ ስብከት ልዑካን የውሳኔ ሃሳቦች የሚያቀርቡበት ውይይት እንደሆነ ታውቋል።
የክርስቲያን ደስታ በሁሉም የሕይወት ሁኔታዎች በእግዚአብሔር መታመን ነው
“ደስታ ሙሉ ይሆን ዘንድ” በሚለው ርዕሥ፥ እውነተኛ ደስታ መከራን በማስወግድ ለችግሮች ቀላል መፍትሄዎችን የሚሰጥ ሳይሆን ነገር ግን እግዚአብሔር ፈጽሞ እንደማይተወን መሆኑን ከማመን የሚመነጭ ነው” ሲል ያስታውሳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሆስፒታል ውስጥ በነበሩበት ወቅት እና አሁን በማገገም ላይ ባሉበት ወቅት የእግዚአብሔር ቅርበት በግል እንዳጋጠማቸው አረጋግጠው፥ “የክርስቲያኖች ደስታ በሁሉም የሕይወት ሁኔታዎች ውስጥ በእግዚአብሔር መታመን እንደሆነ እና፣ በዕለት ተዕለት ኑሮ ደስታን በመጋራት የሚገኝ፣ ሰፊ ግንዛቤ እና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ያለው ነው” በማለት ጽፈዋል።
በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ አብረው መጓዝ
የጣሊያን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ለወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ በሆኑት መመሪያዎች ላይ ድምጽ ለመስጠት በምትዘጋጅበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጉባኤው ተሳታፊዎች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በሚመነጭ ስምምነት እንዲመሩ ጋብዘው፣ “ቤተ ክርስቲያን በብዙዎች ወይም በአናሳዎች የተዋቀረች ሳትሆነ ነገር ግን በታሪክ ውስጥ በእግዚአብሔር ቃል እና በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን በሚመላለስ ቅዱስ ሕዝብ የተዋቀረች ናት” ሲሉ አስገንዝበዋል።