ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ምዕመናንን ለጸሎታቸው አመስግነው የሚሰቃዩትን በጸሎት አስታወሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ሚያዝያ 5/2017 ዓ. ም. በተከበረው በሆሳዕና በዓል ስብከታቸው፥ ምዕመናን ሐዘን እና ድካም ሲሰማቸው ተስፋን እንዳይቆርጡ፥ በጥላቻ እና በምሬት ምክንያት ልባቸውን እንዳይዘጉ፣ የሚረዳ የእግዚአብሔር አሳቢነት እና ምሕረት ዘወትር አብሮአቸው እንደሆነም አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ተጽፎ በሚገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ላይ ያስተነተኑበት እና የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ለጋዜጠኞች ያሰራቸው ጽሑፍ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ይዞ ሲሰቃይ ሥጋው ተሰባሪ ቢሆንም እስከ ሞት ድረስ በሕፃን ስሜት በእግዚአብሔር አብ እቅፍ በመተማመን ጠንካራ ሆኖ መመላለሱን እንደሚገልጽ ተመልክቷል።
የሆሳዕና በዓል ሥነ-ሥርዓት በእነዚህ ስሜቶች ላይ በማሰላሰል በራሳችን ሕይወት ላይ እንድናስተነትን ይጋብዘናል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሁላችንም ሥጋዊ እና ሞራላዊ ሐዘን ብኖረንም እምነታችን ደግሞ ተስፋ እንዳንቆርጥ፣ ልባችንን በምሬት እና በጥላቻ ሳንዘጋው ነገር ግን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ቸርነት እና ምሕረት እንድንጋፈጥ ይረዳናል” ሲሉ አስገንዝበዋል።
“ሁላችንም ሐዘን አለብን፤ ነገር ግን እምነት ተስፋ እንዳንቆርጥ ያግዘናል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በጦርነት፣ በድህነት እና በተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዱን በጸሎታቸው ከማስታወሳቸው አስቀድመው፥ በሳንቶ ዶሚንጎ ሕንፃ ተደርምሶባቸው ጉዳት የደረሰባቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው በማስታወስ፥ በሳንባ ምች ሕመም ሆስፒታል በገቡበት ወቅት እና አሁን በማገገም ባሉበት ወቅት ሳያቋርጡ በጸሎታቸው በመርዳት ላይ የሚገኙትን በሙሉ አመስግነዋል።
የበርካታ እህቶች እና ወንድሞች ጸሎት በደከመኝ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቅርበት፣ ርህራሄ እና ገርነት ይበልጥ እንዲሰማኝ ረድቶኛል” ብለው፥ ከእርሳቸው ጋር በመሆን መከራ የሚቀበሉትን ሁሉ በጸሎት እንዲያስታውሷቸው አሳስበው፥ እርሳቸውም ምዕመናኑን በሙሉ በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠዋል።