ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የእግዚአብሔር ምሕረት ርኅሩዎች እንድንሆን ይጋብዘናል" ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የሕማማት ሳምንት ዋዜማ ላይ ባቀረቡት ስብከት፥ ወሰን በሌለው በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ እንድናስተነትን አደራ ብለው፥ በሕማማት ሳምንት ውስጥ የራሳችንን መስቀል እንዴት መሸከም እንደሚገባን እና በዙሪያችን የሚገኙ ሰዎች መከራንም በመሸከም እንድንረዳቸው ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ በመምራት በአርባ ሺህ ለሚገመቱ ምዕመናን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ስብከት በንባብ ያሰሙት፥ የካርዲናሎች መማክርት ምክትል ሃላፊ ብፁዕ ካርዲናል ሳንድሪ ናቸው።
ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በርካታ ሕዝብ “ሆሳዕና!”፥ “አሁን አድነን! እያሉ በደስታ እንደተቀበሉት፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ተፈርዶበት የመከራ እና የሐዘን መስቀል ተሸክሞ ከከተማዋ መውጣቱን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብከታቸው አስታውሰዋል።
የቄሬናዊው ስምዖን
በዕለቱ ከሉቃ. 22:14-23፣56 ተወስዶ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከት፥ በሮማውያን ወታደሮች ተይዞ ለተወሰነ ጊዜ የኢየሱስን መስቀል ለመሸከም የተገደደውን የቄሬናዊውን ስምዖን ማንነት በማስታወስ፥ ይህ ሰው ለዚህ ቅጣት የተገባ ባይሆንም እንኳ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ተካፋይ መሆኑን እና የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የእርሱ መስቀል መሆኑን ተናግረዋል። ፍላጎቱ ባይሆንም ወደ ቀራንዮ በሚወስደው መንገድ ላይ የኢየሱስን መስቀል ለመሸከም መገደዱን እና ይህ ሲሆን በኢየሱስ እና በስምዖን መካከል ምንም ዓይነት ንግግር እንደሌለ፥ ነገር ግን በሁለቱ መካከል የእንጨት መስቀል ብቻ መኖሩን አስታውሰዋል።
ቄሬናዊው ስምዖን ሚና በድነት ታሪክ ውስጥ
የቀሬናዊው ስምዖን ልብ ለመረዳት፥ የኢየሱስን መከራ ለመካፈል የተገደደው በመራራቱ ይሁን አይሁን ለማወቅ ልቡን መመልከት እንደሚገባ የጠቆሙት ቅዱስነታቸው፥ የእግዚአብሔር ልብ ምሕረትን ሊያደርግ እና ህመም ሊቀበል ዘወትር ክፍት ሲሆን የሰው ልብ ግን ዝግ ሆኖ ይኖራል” ብለው፥ ቄሬናዊው ስምዖን ቁጣ፣ ርኅራኄ ወይም ብስጭት ይሰማው እኛ የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል።የምናውቀው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆች ኃጢአትን በመስቀሉ እንደተሸከመ ብቻ ነው” ብለዋል።
“ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆች ኃጢአትን የተሸከመው ለፍቅራችን እና የአባቱን ትዕዛዝ ለመፈጸም ነው” ብለው መከራን የተቀበለው ከእኛ ጋር ለእኛ እንደሆነ ተናግረው፥ “ቀሬናዊው ስምዖን በዚህ ማንም እንግዳ በማይሆንበት ያልተጠበቀ እና አስደናቂ ሁኔታ ውስጥ የድነት ታሪክ አካል ሆኗል” ሲሉ አስረድተዋል።
አንዱ የሌላውን መስቀል በመሸከም መረዳዳት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እኛም በሕይወታችን ውስጥ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ሰው በሁሉ ሁኔታ መካከል ሊያገኝ እንደመጣ የሚያስተምረንን የቄረናዊው ስምዖን ፈለግ እንዴት መከተል እንደምንችል ሐሳብ አቅርበዋል።
“ማድረግ ያለብን ዙሪያችንን መመልከት ብቻ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ጥላቻና ዓመፅ እጅግ በርካታ ወንዶችና ሴቶች ወደ ቀራኒዮ በሚወስድ መንገድ ለመጓዝ እንዳስገደዳቸው ገልጸው፥ የዓለማችን መንገድ “እግዚአብሔር ለእኛ ሲል ነፍሱን አሳልፎ ለመስጠት የተጓዘበት በመሆኑ ድነት ያለበት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“በዘመናችን ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል በጫንቃቸው ላይ የተሸከሙ ስንት የቄሬና ስምዖኖች እንዳሉ ማወቅ እንችላለን? በጦርነት እና በድህነት በወደቁት ሰዎች ዓይን ኢየሱስን ማየት እንችላለን? አስከፊው ኢ-ፍትሃዊነት ሲገጥመን የኢየሱስን መስቀል የምንሸከመው በከንቱ ሳይሆን ፍቅሩን የምንካፈልበት ተጨባጭ መንገድ ነው” ብለዋል።
የኢየሱስ መከራ እንዴት የርህራሄ ሆነ?
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብከታቸው ማጠቃለያ፥ ለተሰቃዩት እጃችንን ስንዘረጋ፣ የወደቁትን ስናነሳ፣ ተስፋ የቆረጡትን ስናጽናና የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ዛሬ እንዴት ወደ ርኅራኄነት እንደሚለውጥ አስረድተው፥ በሕማማት ሳምንት የእግዚአብሔርን ታላቅ ምሕረት ለመለማመድ የራሳችንን እና በዙሪያችን የሚሠቃዩ ሰዎች መስቀል መሸከም እንደሚገባ አደራ ብለዋል።