MAP

የስሎቫክያ ነጋዲያን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ የስሎቫክያ ነጋዲያን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “እምነት ከሌሎች ጋር በደስታ የምንካፈለው ሃብት ነው” ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጎርጎሮሳውያኑን የዘመን አቆጣጠር በሚከተሉት ምዕመናን ዘንድ እየተከበረ ባለው የኢዮቤልዩ ዓመት ወደ ሮም ለመጡት የስሎቫክያ ነጋዲያን መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለነጋዲያኑ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “እምነት ከሌሎች ጋር በደስታ የምንካፈለው ሃብት ነው” ብለው፥ ለእግዚአብሔር መታዘዝ የሰላምን አድማስ የሚከፍት መሆኑን ማየት አስደናቂ እንደሆነ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ይህን የእምነት እና የአንድነት ጊዜን ከእናንተ ጋር ለመካፈል እመኝ ነበር” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከስሎቫክያ ምዕመናን ጋር በብሔራዊ የኢዮቤልዩ ዓመት ንግደት ዝግጅት ላይ መገኘት ባለመቻላቸው የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። የቅሱነታቸውን መልዕክት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ለተካፈሉት የስሎቫክያ ነጋድያን ዓርብ መጋቢት 26/2017 ዓ. ም. በንባብ ያሰሙት፥ የኮሼስ ሊቀ ጳጳስ እና የስሎቫክያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዘደንት አቡነ ቤርናርድ ቦበር ናቸው።

በስሎቫክያ ብሔራዊ የኢዮቤልዩ ዓመት ንግደት ላይ ከተገኙት 4,300 ምዕመናን መካከል የስሎቫክያው ፕሬዚደንት ፒተር ፔሌግሪኒ፣ የመንግሥት ሚኒስትሮች እና በስሎቫኪያ የሐዋርያዊ መንበር እንደራሴ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኒኮላ ጂራሶሊ ይገኙበታል።

እምነትን በደስታ ለሌሎች ማካፈል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለነጋዲያኑ ባስተላለፉት በመልዕክት፥ “እምነት ከሌሎች ጋር በደስታ ልንካፈል የሚገባን ሃብት ነው” ሲሉ አስታውሰው፥ እምነት በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ ቢሆን በእግዚአብሔር በመታመን የምናድግበት እና ለእርሱ የምንገዛበት ዕድል ነው” በማለት አስረድተዋል። ስለዚህ የእኛ ልባዊ መታዘዝ ልክ እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ኃይል ታላቅ ነገርን ለማከናወን መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

“ዛሬ ለእግዚአብሔር መታዘዛችን ለራሳችን እና እርሱ በመንገዳችን ላይ ለሚያስቀምጣቸው ሰዎች አዲስ የእምነት፣ የተስፋ እና የሰላም አድማስ እንድንከፍት ያስችለናል” ሲሉ ብርታትን ተመኝተው፥ ምእመናን በሲኖዶሳዊነት ስልት በአዲስ ነገር ሳይደናገጡ ነገር ግን ዘወትር የሚያስደንቅ የእግዚአብሔርን አነሳሽነት በማየት መንፈስ ቅዱስን እንዲያዳምጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የዕድሜ ልክ ነጋዲያን ነን!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስሎቫክያ ነጋዲያን በላኩት መልዕክት፥ “በኢዮቤልዩ ዓመት ወደ ሮም ያደረጋችሁት ንግደት እምነትን ለማደስ፣ ከቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ለማጠናከር እና የማያሳዝን ተስፋን በደስታ ለመመስከር ያላችሁን ፍላጎት የሚያሳይ ተጨባጭ ምልክት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

“ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚመነጭ ይህ ተስፋ፥ ዘወትር እንድንከተለው የኢዮቤልዩ በዓል የሚጋብዘን ተስፋ እንደሆነ እና በሕይወታችን ሁሉ መንፈሳዊ ተጓዦች ወይም ነጋዲያን እንድንሆን የሚጠራን የዘላለማዊ ጉዞ መጀመሪያ ነው” ሲሉ አስረድተው፥ ይህ መንፈሳዊ ንግደት በቅዱስ በሮች በኩል በማለፍ የሐዋርያትን እና የሰማዕታትን መቃብር በመጎብኘት በሮም የሚያበቃ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስሎቫክያ ነጋዲያን እንዳስገነዘቡት፥ “በኢዮቤልዩ ዓመት ያካሄዱት ይህ መንፈሳዊ ንግደት፥ ቅዱስ ቄርሎስ እና ቅዱስ መቶድዮስ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ቅዱሳን ከሺህ ዓመታት በላይ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ምስክርነት ያሳደጉት የምድራችሁ ውድ የክርስቲያናዊ ባህል አካል ነው” ሲሉ አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ “የሰባቱ ሐዘኖች እመቤታችን” እያሉ የሚያከብሯት የስሎቫክያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥበቃን እና ተስፋን በመማጸን መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

05 Apr 2025, 15:31