ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የብፁዕ ፒተር ቶ ሮት የቅድስና መዝገብ አጸደቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት ሰኞ መጋቢት 22/2017 ዓ. ም. የቀረቡ በርካታ የቅድስና ጉዳዮች መዛግብትን ከተመለከቷቸው በኋላ ያጸደቁ ሲሆን፣ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በዚህም መሠረት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሦስት አዳዲስ ቅዱሳን፣ አንድ ብጹዕ እና አንድ የተከበረ፥ በድምሩ አምስት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የነበሩትን ይፋ እንደምታደርግ ይጠበቃል።
የመጀመሪያው የፓፑዋ ኒው ጊኒ ቅዱስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅድስና መዝገቡን ያጸደቁለት የፓፑዋ ኒው ጊኒ ተወላጅ ብጹዕ ፒተር ቶ ሮት መጋቢት 26/1904 ዓ. ም. የተወለደ እና ለእምነቱ ሲል ሰማዕትነት የተቀበለ እንደሆነ ይነገራል። ብጹዕ ፒተር ቶ ሮት የክርስትናን እምነት ከተቀበለ በኋላ በትምህርተ ክርስቶስ መምህርነት ያገለገለ፥ ሕይወቱን ለበጎ አድራጎት ሥራ፣ ድሆችን እና ወላጅ አልባ ሕፃናትን በትሕትና ለማገልገል ያዋለ እንደ ነበር የሕይወት ታሪኩ ይመሠክራል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጃፓኖች ፓፑዋ ኒው ጊኒን በያዙበት ወቅት ብፁዕ ፒተር በእስር ላይ የሚገኙ ሚስዮናውያን ጥንዶችን ለጋብቻ አዘጋጅቷዋል። ሐዋርያዊ አገልግሎት የተከለከለ መሆኑን በሚገባ ቢያውቅም ሕይወቱን ለአደጋ በማጋለጥ ሐዋርያዊነቱን በድብቅ ፈጽሟል።
ለጋብቻን ቅድስና አጥብቆ በመሟገት፥ ከአንድ በላይ ማግባትን በመቃወም ሁለተኛ ሚስት ካገባ ታላቅ ወንድሙ ጋር ሳይቀር ተከራክሯል። ወንድሙ ለፖሊስ ሲያመለክት የሁለት ወር እስራት ከተፈረደበት በኋላ በሐምሌ ወር 1937 ዓ. ም. ሕይወቱ በመርዝ ማለፉ ታውቋል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በጥር 9/1987 ዓ. ም. በፓፑዋ ኒው ጊኒ መዲና ፖርት ሞርስቢ የፒተር ቶ ሮት ብፁዕናን በይፋ ማውጃቸው ይታወሳል።
በዘር ማጥፋት ወቅት በሰማዕትነት ያረፉ የአርመን ሊቀ ጳጳስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅድስናን መንገድ ካመቻቹላቸው መካከል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1869 ዓ. ም. በማርዲን በዛሬዋ ቱርክ ውስጥ የተወለዱት ብፁዕ ኢግናሽየስ ቹክራላህ ማሎያን አንዱ ናቸው።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1883 ሊባኖስ ውስጥ የክኅነት ማዕረግ የተቀበሉት ብጹዕ ኢግናሽየስ በሁለቱም ቋንቋዎች ማለትም በአረብኛ እና በቱርክ ቋንቋዎች ጥሩ ሰባኪ በመሆን ራሳቸውን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እና በግብፅ አሌክሳንድሪያ ውስጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናት ይታወቅ ነበር።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1911 ዓ. ም. የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ በሮም የአርመን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በተካሄደበት ወቅት የማርዲን ሊቀ ጳጳስ አድርገው የሾሟቸው ሲሆን፥ ይህም በቱርክ የተጀመረውን የወጣቶች እንቅስቃሴ ሁኔታን ከመረመሩት በኋላ እንደ ነበር ታውቋል።
የቱርክ ጦር ወደ አንደኛው የዓለም ጦርነት ከገባ በኋላ ሊቀ ጳጳስ ማሎያን ከ13 ካኅናት እና 600 ክርስቲያኖች ጋር በተለይም የአርመን ክርስቲያኖችን ወከባ ባጋጠማቸው ወቅት ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።
ሊቀ ጳጳስ ማሎያን እና ጓደኞቻቸው ሃይማኖታቸውን እንዲክዱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ግንቦት 26/1907 ዓ. ም. ከተገደሉ በኋላ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መስከረም 27/1994 ዓ. ም. ብጽዕናቸውን በይፋ ማወጃቸው ይታወሳል።
የመጀመሪያዋ ቬነዙዌላዊት ቅድትስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቬነዙዌላ መዲና ካራካስ ውስጥ ነሐሴ 5/1895 ዓ. ም. የተወለደች እና ተአምሯ የታወቀላት ብጽዕት ካርመን ኤሌና ሬንዲልስ ማርቲኔዝ ቅድስናንም ሰኞ መጋቢት 22/2017 ዓ. ም. ያጸደቁ ሲሆን፥ ብፅዕት ማርያ ዴል ሞንቴ ካርሜሎ ለቬነዙዌላ የመጀመሪያ ቅድስት እንደምትሆን ታውቋል።
ብፅዕት ማርያ ዴል ሞንቴ ካርሜሎ በ1919 ዓ. ም. የቅዱስ ምስጢር ኢየሱስ ክርስቶስ ገዳማውያት ማኅበርን ተቀላቅላ ከዚያም ከሌሎች የላቲን አሜሪካ ገዳማዊ እህቶች ጋር በ1938 ዓ. ም. የኢየሱስ አገልጋዮች ማኅበርን እንደመሠረተች ታውቋል።
በ1966 ዓ. ም. በደረሰባት የመኪና አደጋ ምክንያት የመጨረሻዎቹን የሕይወቷን ዓመታት በተሽከርካሪ ወንበር በማሳለፍ በግንቦት 1/1969 ዓ. ም. ማረፏ ይታወሳል። በ 2007 ዓ. ም. የተፈጸመው የአማላጅነቷ ተአምሯ ካራካስ ውስጥ የምትኖር አንዲት የልብ ታማሚ ወጣት ፈወስን ማካተቱ ታውቋል።
የጣሊያናዊ ካኅን ተአምር እና የብራዚል ካኅን የበጎነት ተጋድሎ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጣሊያናዊው ካኅን አባ ካርሜሎ ዴ ፓልማ ተአምር እውቅና የሰጡ ሲሆን፥ አባ ካርሜሎ ዴ ፓልማ በደቡብ ጣሊያን ባሪ ከተማ ውስጥ ጥር 19/1868 ዓ. ም. መወለዳቸው ይታወሳል።
በቅዱስ ብሩክ የምንኩስና ሕይወት የተማረከው ደ ፓልማ “የኑዛዜ አባት” በመባል የሚታወቅ ሲሆን፥ በዚህ ስጦታው ለካህናት፣ ለመነኮሳት እና ለዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች መንፈሳዊ መመሪያ በመስጠት ያገለግል እንደ ነበር ታውቋል። በ 2005 ዓ. ም. የተፈጸመው የአማላጅነት ተአምሩ የቅዱስ ብሩክ ገዳም መነኩሴን ፈውስ ከሌለው ሕመም ማዳኑ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ መጋቢት 22/2017 ዓ. ም. ለበጎነት ገድሉ እውቅና የሰጡት የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆሴ አንቶኒዮ ዴ ማሪያ ኢቢያፒና ሲሆን፥ ሆሴ አንቶኒዮ በኋላ ላይ የክኅነት ማዕረግ የተቀበለ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ብራዚላዊ ፖለቲከኛ እንደ ነበር ይሕይወት ታሪኩ ይገልጻል።