የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አስከሬን ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ተወሰደ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር የንብረት እና የፋይናንስ ክፍል አስተዳዳሪ ብጹዕ ካርዲናል ፋረል በሥነ-ሥርዓቱ መክፈቻ ላይ ባቀረቡት ጸሎት፥ ሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአሥራ ሁለት ዓመታት ያበረከቱትን ሥፍር ቁጥር የሌለውን ሐዋርያዊ አገልግሎት በማስታወስ እግዚአብሔርን አመስግነዋል።
“እግዚአብሔር በምሕረቱ እና በቸርነቱ የሟቹን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነፍስ በመንግሥተ ሰማያት በዘላለማዊው ቤቱ ይቀበልልን” ብለው፥ ለከፍተኛ የጳጳሳዊ ምክር የሥራ ተባባሪዎች፣ ለሮም ቤተ ክርስቲያን እና ለመላው ዓለም ምእመናን መጽናናትን እንዲሰጣቸው ጸልየዋል።
በመቀጠልም ጠቅላላ የካርዲናሎች ጉባኤ የቅዱስነታቸውን አስከሬን በማጀብ ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያመሩ ሲሆን፥ የቅዱስነታቸው አስከሬን ወደ ባዚሊካው ባመራበት ወቅት በሥፍራው የነበሩ በሃያ ሺህ የሚገመቱ ምዕመናን በጭብጨባ ተቀብለውታል።
የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ቅዳሜ ሚያዝያ 18/2017 ዓ. ም. ከመፈጸሙ በፊት ረቡዕ ከቀኑ አምስት ሰዓት ጀምሮ ምእመናን ወደ ባዚሊካው በመሄድ የቅዱስነታቸውን አስከሬን መሳለም የጀመሩ ሲሆን፥ ባዚሊካውም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል።
ሐሙስ ሚያዝያ 16/2017 ዓ. ም. ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ የአስከሬናቸው ሳጥን ለምዕመናን ክፍት ሆኖ ከቆየ በኋላ እኩለ ሌሊት ላይ እንደሚዘጋ እና ዓርብ ዕለት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ስድስት ሰዓት ድረስ ክፍት እንደሚሆን መርሃ-ግብሩ አስታውቋል።