ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመጨረሻዎቹ ሰዓታት በተረጋጋ መንፈስ ምስጋና ማቅረባቸው ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ወደ አደባባይ ስላወጣኸኝ አመሰግናለሁ!”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በህመማቸው ጊዜ ሁሉ እንዲሁም ከዚያ በፊትም ሳይታክት ይከታተላቸው ለነበረ ሰው ካቀረቡት የመጨረሻዎቹ የምስጋና ቃላት መካከል አንዱ ሲሆን፥ ማሲሚላኖ ስትራፕቲ እንደ እርሳቸው ገለጻ የአንጀት ቀዶ ጥገና ባደረጉበት ወቅት ሕይወታቸውን ከሞት ያተረፈው እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2022 ዓ. ም. ጀምሮ የግል የጤና ረዳት አድርገውት የሾሙት እንደ ሆነ ሲያወቅ፥ ከዕረፍታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ማዕከላዊ ሰገነት የሚወስደውን መንገድ ለቀጣዩ ቀን ለመገምገም አብረው መሄዳቸው ታውቋል።
ምዕመናኑ የሰጣቸው ድጋፍ
ከዚያ በኋላ እሑድ ሚያዝያ 12/2017 ዓ. ም. ጠዋት በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ፊት ለፊት ባለው ባልኮን ላይ ሆነው ከመጀመሪያው ቁጥር በላይ ወደ 50,000 ለሚደርሱ ምዕመናን ቡራኬ ለመስጠት እና ከዚያ በኋላም ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በማምራት የመጨረሻ ሰላምታቸውን ለማቅረብ መፈለጋቸው እና የማቅማማት ስሜት ቢታይባቸውም የጤና ረዳታቸውን እንዳበረታታቸው ተነግሯል።
ከጄሜሊ ሆስፒታል ከወጡ በኋላ የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ሰላምታቸውን በአደባባዩ ለነበሩት ምዕመናን በተለይም ለሕጻናት አቅርበዋል። የደከሙ ቢሆንም እርካታ የተሰማቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አደባባይ በማምጣት ከምዕምናኑ ጋር እንዲገናኙ ያደረገውን የግል የጤና ረዳታቸውን አመስግነዋል። ከልብ የሚመነጩ ቃላቶች የእርስ በርስ ግንኙነት የጵጵስናቸውን መገለጫ ያደረጉት አርጀንቲናዊው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሕዝቡ መካከል ለመሆን ያላቸውን ጥልቅ ፍላጎት በተጨባጭ አሳይተዋል።
የቅዱስነታቸው መጨረሻዎቹ ሰዓታት
በዕለቱ ከሰዓት በኋላ ጥሩ ዕረፍት ካደረጉ በኋላ ማታ እራታቸውን የበሉት ቅዱስነታቸው ከንጋቱ 11:35 አካባቢ የመጀመሪያዎቹ የሕመም ምልክቶች ሲሰማቸው የጤና ረዳቶቻቸው አፋጣኝ ምላሽ ሰጥቷቸው እንደ ነበር ታውቋል።
ከአንድ ሰዓት በላይ በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ በሚገኘው መኖሪያቸው ለጤና ረዳታቸው የስንብት ምልክት ካሳዩ በኋላ ኮማ ውስጥ መግባታቸው ተነግሯል። በመጨረሻዎቹ ጊዜያት አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች እንደሚናገሩት፥ ምንም ዓይነት ስቃይ ሳይሰማቸው በቶሎ በሰላም ማረፋቸውን ገልጸዋል።
ጤንነታቸው ዘወትር ተጠብቆላቸው የቆዩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለ ስቃይ በድንገት ማለት በሚቻል ሁኔታ የተከሰተው የቅዱስነታቸው ዕረፍት ሰላማዊ ዕረፍት የነበረ ሲሆን፥ የሮም ከተማን እና መላው ዓለምን በባረኩበት፣ ከብዙ ጊዜ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለነበሩት በርካታ ምዕመናን እንደገና ልባዊ ሰላምታ ማቅረብ በቻሉበት በብርሃነ ትንሳኤው ማግስት በስጋ መለየታቸው የሰላም እረፍት እንደነበር ተነግሯል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን በበላይነት ለማገልገል ከተመረጠበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከመጋቢት 13/2013 ዓ. ም. ጀምሮ ከሕዝብ ጋር በአንድነት ለመራመድ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።