MAP

የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተገኝተው ምዕመናንን አመሰገኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በያዝነው የኢዮቤልዩ ዓመት እሑድ መጋቢት 28/2017 ዓ. ም. በተዘጋጀው የሕሙማን እና የዓለም ጤና አጠባበቅ በዓል ማብቂያ ላይ ተገኝተው ለምዕመናን ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ ከምዕመናን ጋር በአደባባይ ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መጋቢት 28 ቀን ከምዕመናን ጋር የሚገናኙበት ቀጠሮ ባይያዝላቸውም፥ ነገር ግን የሕሙማን እና የዓለም ጤና አጠባበቅ በዓል በተከበረበት ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በድንገት ተገኝተው ከምዕመናን ጋር ተገናኝተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መስዋዕተ ቅዳሴውን በመካፈል ላይ ከሚገኙት ምዕመናን መካከል በማለፍ ወደ መሠዊያው የደረሱ ሲሆን፥ በዕለቱ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩት በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ እንደነበሩ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመጨረሻው ቡራኬ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን በሙሉ መልካም ዕለተ ሰንበትን ከተመኙላቸው በኋላ ምስጋናቸውን አቅርበው ወደ ቅድስት ማርታ መኖሪያቸው ተመልዋልሰ። በአደባባዩ የነበሩት ነጋዲያንም በበኩላቸው ደስታቸውን በጭብጨባ ገልጸው፥ “ረጅም ዕድሜ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት” ሲሉ ያላቸውን መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናን ሰላምታ ከማቅረባቸው እና ከማመስገናቸው በፊት ንስሐ በመግባት ሙሉ የኃጢአት ሥርየት ከተቀበሉ በኋላ በጸሎት መንፈስ ቅዱስ በርን አልፈው ወደ ጳጳሳዊ መኖሪያቸው መመለሳቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል።

ቅዱስነታቸው በዚህም ያለፈው ቅዳሜ እና እሁድ የተከበረውን የሕሙማን የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩን ለማክበር ወደ ቫቲካን ከመጡ ምዕመናን ጋር ሙሉ የኃጢአት ስርየት ለማግኘት የሚያስፈልጓቸውን ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን አድርገዋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል የቅዱስነታቸውን የጤና ሁኔታ በማስመልከት ዓርብ መጋቢት 26/2017 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፥ “ቅዱስነታቸው ጤናቸው እየተሻሻለ በመምጣቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ” ሲል ማሳወቁ ይታወሳል።

 

07 Apr 2025, 15:53