የሮም ምእመናን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በመስዋዕተ ቅዳሴ አስታወሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ሰኞ ሚያዝያ 13/2017 ዓ. ም. ማምሻውን የሮማ ሀገረ ስብከት ምዕመናን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍትን ለማሰብ በተሰበሰቡበት ወቅት የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ በጸሎት፣ በሐዘን እና በምስጋና ድባብ የተሞላ እንደ ነበር ተመልክቷል። በባዚሊካው የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመሩት የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና፥ ስብከታቸው ለእረኛቸው ያዘኑትን የምዕመናኑን ስሜት የተመለከተ እንደ ነበር ተመልክቷል።
ብጹዕነታቸው በስብከታቸው፥ “የእኛ ሀገረ ስብከት ዛሬ አመሻሽ ላይ የመግደላዊት ማርያምን እንባ አፍስሷል” ብለው፥ ገና ጨለማ ሳለ የኢየሱስ ክርስቶስን አስክሬን የፈለገችውን የቅዱስ ወንጌል ሰው በማስታወስ፥ ፍለጋዋ የዛሬዋን ቤተ ክርስቲያን የሚያንጸባርቅ መሆኑን ተናግረው፥ በመጨረሻም አካሉን በነካችው ጊዜ አጥታ የነበረውን መፅናናት እንደምትፈልግ አስረድተው፥ “የወንጌል ምስክር፣ የምሕረት ሐዋርያ፣ የሰላም ነቢይ እና የድሆች ወዳጅ ለሆኑት ጳጳሳችን እናለቅሳለን” ብለው፥ እረኛ እንደሌላቸው በጎች የሚሰማቸው መሆኑን ብፁዕ ካርዲናል ሬይና ገልጸዋል።
መለወጥ፣ አንድነት እና ምሕረት
በስብከታቸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ዋና ዋና የጳጳሳዊነት ምልክቶችን ያስታወሱት ካርዲናል ሬይና፥ ቅዱስነታቸው የመለወጥ፣ ወደ ተገለሉ ሰዎች የመቅረብ እና በእግዚአብሔር ምሕረት የመታመን ጥሪ እንደነበሩ አስታውሰዋል። “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሰዎች ዘንድ እንድንሄድ እና እንድንፈልጋቸው ጠይቀውናል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሬይና፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ ሄደን ማኅበረሰቡን ማግኘት እንደሚገባ ደጋግመው ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመከራ ውስጥ ፍትህን እና ሰላምን ለማስፈን በሚያደርጉት ጥረት ፍትህን እና ሰላምን ለማምጣት የደፈሩ አባት እንደ ነበሩ ተናግረው፥ “ይህን ማድረግ በሚያስፈልግበት ጊዜ አካሄዳቸውን ያልቀየሩ ጳጳስ እንደ ነበሩ እና አንድን ሰው ከወደቀበት ለማንሳት ብቸኛው ጊዜ ራስን ዝቅ አድርጎ መርዳት መሆኑን በተደጋጋሚ መናገር ይወዱ ነበር” ብለዋል።
“በግዴለሽነት በሚመራው ዓለም ውስጥ ድሆች እና ስደተኞች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ምስጢራት ናቸው” ሲሉ ብጹዕ ካርዲናል ሬይና ምእመናንን አስታውሰዋል።
“ሐዘናችሁን ወደ ተልዕኮ ቀይሩት!”
የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና በሥነ-ሥርዓቱ ማጠቃለያ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ምእመናኑ ሐዘናቸውን ወደ ተልዕኮ እንዲቀይሩት ጠይቀው፥ “መግደላዊት ማርያም በኢየሱስ ሞት በሐዘን ወድቃ ሳትቀር ወደ አብ ዘንድ እንዲሄድ መተው እንዳለባት መጠየቋን አስታውሰዋል።
አክለውም፥ “በእግዚአብሔር የጊዜ ምስጢር የፋሲካ በዓልን አክብረናል፤ በጳጳሳችን ህልፈት ብናዝንም ነገር ግን በትንሳኤው መካፈላችን እምነታችንን ይደግፈዋል፤ ተስፋ እንድናደርግ ያስችለናል፣ በሐዘናችን ጊዜ ያጽናናል” ብለዋል።
“የሮም ሀገረ ስብከት ምዕመናን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የታማኝ አገልግሎት ጸጋ ምስክሮች ሆነው ቆይተዋል፤ እርሳቸውን እረኛ አድርጎ የሰጠንን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን” ብለው ምዕመናኑ አርአያነታቸውም እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት በመግለጽ ስብከታቸውን ደምድመዋል።