ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ከሕመማቸው እያገገሙ መሆናቸው ተገለጸ!
የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በመጪው እሁድ የሚደርገው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካለፉት እሑዶች ጋር ሲነጻጸር በተለየ ሁኔታ ሊፈጸም ይችላል፣ ይህንን በተመለከተ የተሻሻለ መረጃ ቅዳሜ እንደሚቀርብ የቅድስት መንበር ኅትመት ጽ/ቤት አርብ ጠዋት መጋቢት 26/2017 ለጋዜጠኞች አስታውቋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እያገገሙ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የሁለትዮሽ የሳንባ ምች በሽታን ያስከተለ ፖሊሚክሮቢያል ኢንፌክሽን ምክንያት ሆስፒታል መግባታቸውን ተከትሎ የፕሬስ ጽ/ቤቱ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የጤና ሁኔታ አስመልክቶ በተከታታይ በሚሰጠው መግለጫ የጤና ሁኔታቸው መሻሻሎችን እያሳየ መሆኑን የምያመላክቱ ዘገባዎችን በተከታታይ ማውጣቱን ቀጥለዋል።
በአሁኑ ወቅት ቅዱስነታቸው ከሆስፒታል ወጥተው በቫቲካን ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሆነው ከሕመማቸው እያገገሙ እንደሚገኝ ይታወቃል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁኔታ መጠነኛ የትንፋሽ፣ የመንቀሳቀስ እና ከድምፅ ጋር የተያያዙ መሻሻሎችን አሳይቷል ሲል የፕሬስ ጽ/ቤቱ ገልጿል።
የቅርብ ጊዜ የደም ምርመራዎችም የሳንባ በሽታ እንፌክሽን ላይ ትንሽ መሻሻሎች እንዳሉ ያሳያሉ።
ቅዱስ አባታችን ሕክምናቸውን፣ እንቅስቃሴ ማድረግ እና የመተንፈሻ አካላት አካላዊ ሕክምናን ማድርግ ቀጥለዋል፣ በተጨማሪም አነስተኛ ተጨማሪ ኦክሲጅን ያስፈልጋቸዋል። በቀን ውስጥ የተለመደው የኦክስጂን አስተዳደር ፍሰት ይቀጥላል፣ በምሽት ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ በአፍንጫቸው ቦይ ከፍተኛ ፍሰት ያለው ኦክሲጅን ይሰጣቸዋል።
ከዚህም በላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሥራ እንቅስቃሴያቸውን እንደቀጠሉ እና በጥሩ መንፈስ ላይ መሆናቸውን የፕሬስ ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።
በቫቲካን ጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ በጳጳሳዊ ቤት ሰባኪ አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ የተደረገውን የዓብይ ጾም አስተንትኖ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አርብ ማለዳ በቪዲዮ ሊንክ ተከታትለዋል።
የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 20ኛ ዓመት የሙት ዓመት ምክንያት በማድረግ በቫቲካን ዋና ጸኃፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን መሪነት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ተካሂዶ የነበረውን መስዋዕተ ቅዳሴም ትላንት ሐሙስ መጋቢት 25/2017 ዓ.ም በቴለቪዢን መከታተላቸውም ተገልጿል።
የፕሬስ ጽህፈት ቤቱ ጉብኝቶች እንዳልተደረጉ በመጥቀስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቅዱስ ሳምንት ሥርዓተ አምልኮ ላይ ስለሚኖራቸው ተሳትፎ ለመነጋገር ወቅቱ አሁን ገና ነው ብሏል።
ቅዱስ አባታችንን የተመለከተ የሚቀጥለው መግለጫ በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ እንደሚሰጥ የፕሬስ ጽ/ቤቱ አክሎ ገልጿል።