ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም ተማጸኑ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር መግለጫ እሁድ ዕለት ባሰራጨው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ፥ ማክሰኞ ሚያዝያ 7/2017 ዓ. ም. ሱዳን ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች የተፈናቀሉበት ጦርነት የተቀሰቀሰበት ሁለተኛው ዓመት መታሰቢያ እንደሆነ አስታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ባቀረቡት አቤቱታ፥ “ወደ ሰማይ የሚጮኹ እና እንድንተገብር የሚለምኑን የሕፃናት፣ የሴቶች እና የተጋላጭ ሰዎች መከራን አስታውሰው፥ ሁከት ቆሞ የውይይት መንገዶች እንዲመቻቹ፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስፈላጊው ነፍስ አድን ዕርዳታ ለሕዝቡ እንዲያደርስ ተማጽነዋል።
ሱዳን ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት
ሱዳን የረዥም ጊዜ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን ውረደው ወደ ሲቪል አገዛዝ ከተሸጋገረች በኋላ በተቀናቃኞቹ ወታደራዊ ሃይሎች ማለትም በሱዳን ጦር ሃይሎች (ኤስኤፍኤ) እና በፓራሚሊታሪ ፈጣን ድጋፍ ሃይሎች (አርኤስኤፍ) መካከል የተካሄደው ከባድ ጦርነት ከተሞችን በማውደም በሥስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ከ 3.3 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ጨምሮ ቢያንስ 12.4 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የዕርዳታ ትብብር ጽሕፈት ቤት OCHA ቅዳሜ ዕለት ባወጣው ሪፖርቱ፥ “አስተማማኝ ሰላም የሌለው የሱዳን ሕዝብ በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛል” ሲል አስጠንቅቋል። ከሦስት ሰዎች መካከል ሁለቱ ዕርዳታ እንደሚፈልጉ እና ይህም 30 ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚደርስ የዕርዳታ ትብብር ጽሕፈት ቤቱ ቃል አቀባይ ገልጸው፥ አክለውም ይህ ትልቅ የዓለም አቀፍ ድጋፍን የሚጠይቅ ቢሆንም ነገር ግን በምትኩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ገንዘብ ለጋሾች ድጋፋቸውን ወደ ኋላ እየጎተቱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ሊባኖስ
የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየካቲት ወር አጋማሽ ሆስፒታል ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ እንዲሁም ከቅድስት ማርታ መኖሪያቸው ያቀረቡትን አቤቱታ ጠቅሶ ባሰራጨው መግለጫ፥ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ ሊባኖስን በጸሎታቸው እንዲያስታውሷት መማጸናቸውን ገልጿል።
ከሃምሳ ዓመታት በፊት አሰቃቂው የእርስ በርስ ጦርነት የተቀሰቀሰባት ሊባኖስ በእግዚአብሔር ዕርዳታ በሰላም እና በብልጽግና ትኖር ዘንድ በሎታችን እናስታውሳት ሲሉ ቅዱስነታቸው አደራ ብለዋል።
ስለ ሰላም የሚደረጉ ጸሎቶች
በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የዓለም አገራትን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “በዩክሬን፣ በፍልስጤም፣ በእስራኤል፣ በዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በምያንማር እና በደቡብ ሱዳን ሰላም ይውረድ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ “አዛኝ እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሕማማት ሳምንት ውስጥ የሰላም ጸጋን በማስገኘት ትርዳን” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።