ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሱዳን ውስጥ የሚካሄደው ብጥብጥ ያስከተለውን አሳዛኝ ሰብዓዊ ቀውስ አወገዙ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል የኢዮቤልዩ ዓመት እየተከበረ ባለበት የዐብይ ጾም አራተኛው እሑድ መጋቢት21/2017 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ያደረጉትን ንግግር ይፋ አድርጓል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሉቃስ ወንጌል ተወስዶ የተነበበውን የዕለቱን ወንጌል መሠረት በማድረግ ባሰሙት ንግግር፥ ምእመናን በሙሉ ይህን የጾም ጊዜ በፈውስ ጊዜነት እንዲኖሩት አሳስበው፥ እርሳቸውም ይህን የዐቢይ ጾም ወቅት በነፍስ እና በሥጋ እየተለማመዱት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን በመቀጠል፥ “በአዳኙ እግዚአብሔር አምሳል ለባልንጀሮቻቸው በቃላቸው እና በእውቀታቸው፣ በደግነት እና በጸሎት የፈውስ መሣሪያ የሆኑትን በሙሉ ከልብ የሚያመሰግኑት ለዚህም ነው” ሲሉ ገልጸዋል። “ሁላችንንም የሚያመሳስለን ነገር ደካማነት እና ሕመም ቢሆንም ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስገኘልን ድነት ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ብለዋል።
ማያንማርን ጨምሮ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የቀረበ የሰላም ጥሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለምዕመናኑ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ጦርነት እና ግጭት በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን በጋራ እንጸልይ በማለት ጋብዘዋል። በተለይም በጦርነት በሚሰቃዩ ዩክሬን፣ ፍልስጤም፣ እስራኤል፣ ሊባኖስ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ምያንማር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓርብ መጋቢት 19/2017 ዓ. ም. በማያንማር መንደሌይ ግዛት የተከሰተው እና በሬክተር መለኪያ 7.7 ያስመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ1,700 በላይ ሰዎች ሕይወት ማጥፋቱን በሐዘን አስታውሰው፥ በተመሳሳይ አደጋ በታይላንድም ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን አስታውሰዋል።
የደቡብ ሱዳናውያንን ስቃይ ለማቃለል ገንቢ ውይይት ማድረግ
በደቡብ ሱዳን ያለውን ሁኔታ በከፍተኛ ስጋት መከታተላቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “በአገሪቱ ያለውን ውጥረት ለማርገብ ሁሉም መሪዎች የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ልባዊ ጥሪያቸውን አቀርበው፥ “ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው በድፍረት እና ኃላፊነት በተመላበት መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ገንቢ ውይይት እንዲያደርጉም አሳስበዋል። ንግግራቸውን በመቀጠል፥ “የተወዳጁን የደቡብ ሱዳን ሕዝቦችን ስቃይ ማቃለል እና የወደፊት ሰላም እና መረጋጋት መፍጠር የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው” ብለዋል።
ለሱዳን ዘላቂ መፍትሄ መጸለይ
በተጨማሪም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሱዳን ያለው ጦርነት ንጹሃንን እየጎዳቸው እንደሆነ በማስታወስ፥ ከዚህ ጋር በተያያዘ በግጭቱ ውስጥ የሚመለከታቸው አካላት የሲቪል ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን ሕይወት ከአደጋ እንዲጠብቁ ጠይቀው፥ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄን ለማምጣት የሚያስችል አዲስ ድርድር በተቻለ ፍጥነት እንደሚጀመር ተስፋ በማድረግ ተማጽነዋል። በማከልም “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስከፊውን ሰብዓዊ አደጋ ለመቅረፍ የሚያደርገውን ጥረት እንዲያሳድግ” በማለት አሳስበዋል።
በታጂኪስታን እና በኪርጊስታን መካከል የተሰማ መልካም ዜና
ሆኖም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በተለይ በታጂኪስታን እና በኪርጊስታን መካከል ያለውን ድንበር የማካለል ስምምነት መጽደቁን በመጥቀስ፥ ለዚህ አዎንታዊ ክስተት እግዚአብሔርን አመስግነው፥ “ሁለቱም ሀገራት በዚህ መንገድ እንዲቀጥሉ አበረታታለሁ” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ መጋቢት 21/2017 ዓ. ም. ካቀረቡት የመልእከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ያደረጉትን ንግግር ሲያጠናቅቁ፥ “የሰው ልጆች በሰላም እንዲታረቁ የምሕረት እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳቸው” በማለት በጸሎት ንግግራቸውን ደምድመዋል።