ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፡ የመለወጥ አቅም እንደሌለህ አውቀህ ብትፈራም ተስፋ አትቁረጥ ማለታቸው ተገለጸ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት ለምዕመናን በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተንተርሰው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደምያደርጉ ይታወቃል። ቅዱስነታቸው በደረሰባቸው የጤና እክል ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ከተሰጣቸው በኋላ በአሁኑ ወቅት በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ ቤት ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ከሕመማቸው እያገገሙ እንደሚገኙ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ቀደም ሲል ከመታመማቸው በፊት ያዘጋጁትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የቫቲካን የፕሬስ ጽ/ቤት በመጋቢት 24/2017 ዓ.ም ይፋ አድርጓል። በዚህ መሰረት በወቅቱ ጽ/ቤቱ ያፋ ባደርገው የቅዱስነታቸው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሁን የምንገኝበትን የኢዩቤሊዩ አመት ምክንያት በማድረግ ከዚህ ቀደም "ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን ነው፣ የኢየሱስ ሕይወት እና ያደረጋቸው ግንኙነቶች" በሚል ዐብይ አርእስት ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ በመቀጠል “ዘኬዎስ ሆይ! ዛሬ በቤትህ መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ” (ሉቃስ 19፡5) በሚል ንዑስ አርእስት ዙሪያ ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር የተገናኘበትን ሁኔታ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተመርኩዘው ይፋ ባደረጉት የክፍል ሦስት አስተምህሮ የመለወጥ አቅም እንደሌለህ አውቀህ ብትፈራም ተስፋ አትቁረጥ ማለታቸው ተገልጿል።
በእለቱ የተነበበው ምንባብ
ኢየሱስ እና ቀራጩ ዘኬዎስ
ወደ ኢያሪኮም ገብቶ በዚያ በኩል አልፎ እየሄደ ነበር። እነሆም ዘኬዎስ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱም የቀራጮች አለቃ ነበረ፤ ሀብታምም ነበረ። ኢየሱስ ማን እንደሆነም ለማየት ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱም አጭር ነበረና ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ አቃተው። በዚያችም መንገድ ማለፍ ነበረበትና ወደ ፊት ቀድሞ ሮጠና በአንድ ሾላ ላይ ወጣ። ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና “ዘኬዎስ ሆይ! ዛሬ በቤትህ መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ፤” አለው።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች የቫቲካን የፕሬስ ጽ/ቤት በወቅቱ ይፋ ያደርገውን የቅዱስነታቸውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣
ኢየሱስ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ከተጠቀሱት አንዳንድ ገፀ-ባህሪያት ጋር የተገናኘበትን ሁኔታ በሚገልጸው ክፍል ላይ በጀመርነው አስተምህሮ ላይ ማሰላሰላችንን አሁንም እንቀጥል። በዚህ ጊዜ በዘኬዎስ ምስል ላይ ማተኮር እፈልጋለሁ፡ በተለይ ወደ ልቤ በቀረበው ክፍል ላይ፣ ምክንያቱም በመንፈሳዊ ጉዞዬ ውስጥ ልዩ ቦታ አለውና።
የሉቃስ ወንጌል ዘኬዎስን ሊስተካከል በማይችል መልኩ የጠፋ የሚመስለውን ሰው አድርጎ ያቀርባል። ምናልባት እኛ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ይሰማናል-ተስፋ ቢስ እንሆናለን። ዘኬዎስ ግን ጌታ አስቀድሞ ይፈልገው እንደነበረ ይገነዘባል።
እንዲያውም ኢየሱስ እንደ ሲኦል ተደርጋ በምትቆጠረው ከባሕር ወለል በታች ወደምትገኘው ኢያሪኮ ወረደ። በተጨባጭም የተነሣው ጌታ ዛሬም ወደ ሲኦል፣ ወደ ጦርነት ቦታ፣ ወደ ንጹሐን ስቃይ፣ ልጆቻቸው ሲሞቱ በሚያዩ እናቶች ልብ ውስጥ፣ በድሆች ረሃብ ውስጥ መውረዱን ቀጥሏል።
በተወሰነ መልኩ ዘኬዎስ የባከነ ወይም የጠፋ ሰው ይመስላል፣ ምናልባት አንዳንድ መጥፎ ምርጫዎችን አድርጎ ይሆናል ወይም ምናልባት ሕይወት ለማምለጥ በሚታገልባቸው ሁኔታዎች ውስጥ አስገብቶት ይሆናል። ሉቃስ በእውነቱ የዚህን ሰው ባህሪያት አጥብቆ ተናግሯል ወይም ገልጿል፡- ቀረጥ ሰብሳቢ ብቻ ሳይሆን ከወገኖቹ ለሮማውያን ወራሪዎች ግብር የሚሰበስብ፣ ነገር ግን ኃጢአቱ ይበዛል ለማለት ያህል የቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቃ ነበር ሲል ገልጾታል።
ከዚያም ሉቃስ ዘኬዎስ ሀብታም እንደሆነ ገልጿል፤ ይህ ደግሞ ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም ሌሎችን በመበዝበዝ ባለጠጋ ሆኗል ሲል ተናግሯል። ነገር ግን ይህ ሁሉ መዘዝ አለው፡ ዘኬዎስ ምናልባት በሁሉም ሰው እንደተናቀ ይሰማው ይሆናል።
ኢየሱስ በከተማው ውስጥ እንዳለፈ ሲሰማ ዘኬዎስ እሱን ለማየት ፍላጎት አደረበት። ከእርሱ ጋር ፊት ለፊት ለመገናኘት ድፍረት አለነበረውም፣ ከሩቅ ሆኖ ማየት ብቻ ነው የፈለገው። ነገር ግን ይህ ፍላጎቱ እንቅፋት ያጋጥመዋል እናም ወዲያውኑ እውን ሊሆን አልቻለም ነበር፣ ምክንያቱም ዘኬዎስ ቁመቱ አጭር የነበረ ሰው ነው! ይህ የእኛ እውነታ ነው፣ ልንቋቋማቸው የሚገቡ ውስንነቶች አሉን። እናም አንዳንድ ጊዜ የማይረዱን ሌሎች ነገሮችም አሉ፡ ህዝቡ ዘኬዎስን ኢየሱስን እንዳያይ ከለከለው። ምናልባት የእነሱ የበቀል እርምጃም ትንሽ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን ጠንካራ ፍላጎት ካላችሁ ለነችግሮች መፍትሄ አታጡም። ድፍረት ካላችሁ እና ምንም የማታፍሩ ሰዎች ከሆናችሁ፣ እንደ ልጆች የዋሆች እና ስለ ግል ምስላችሁ ብዙ የማትጨነቁ ከሆነ የፈለጋችሁትን ነገር ማግኘት ትችላላችሁ። ዘኬዎስ ልክ እንደ ልጅ ዛፍ ላይ ይወጣል። በተለይም ከቅጠሎች ጀርባ ተደብቀው መመልከት ጥሩ የመመልከቻ ነጥብ መሆን አለበት።
ነገር ግን ከጌታ ጋር ሁል ጊዜ ያልተጠበቀ ነገር ይከሰታል፡ ኢየሱስ በአቅራቢያው ሲደርስ ቀና ብሎ ይመለከታል። ዘኬዎስ እንደተጋለጠ ተሰምቶታል እና ምናልባት የህዝብ ተግሣጽ ይጠብቃል። ሰዎቹ ተስፋ አድርገውት ሊሆን ይችላል፤ ግን ቅር ይላቸዋል፡- ኢየሱስ ዘኬዎስን በዛፉ ላይ ባየው ጊዜ ተገርሞ ወዲያው እንዲወርድ ጠየቀው እና “ዘኬዎስ ሆይ! ዛሬ በቤትህ መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ፤” አለው (ሉቃስ 19፡6)። እግዚአብሔር የጠፋውን ሳይፈልግ አያልፍም።
ሉቃስ በዘኬዎስ ልብ ውስጥ ያለውን ደስታ ጎላ አድርጎ ገልጿል። የታየው ደስታ የታወቁ እና ከሁሉም በላይ ይቅርታ የተደረገላቸው ሰዎች ደስታ ነው። የኢየሱስ እይታ የነቀፋ ሳይሆን የምሕረት እይታ ነው። በተለይ እኛ ምሕረት ሊደረግላቸው አይገባም ብለን የምናስባቸውን ሰዎች እግዚአብሔር ይቅር ሲል ስናይ ያን ዓይነት ምሕረት ለመቀበል አንዳንድ ጊዜ እንቸገራለን። በአምላክ ፍቅር ላይ ገደብ ማድረግ ስለምንፈልግ እናጉረመርማለን።
ዘኬዎስ በቤቱ ውስጥ ባለው ትዕይንት ውስጥ፣ የኢየሱስን የይቅርታ ቃል ከሰማ በኋላ፣ ከሞተበት የተነሣ መስሎ ተሰማው። እናም ቃል ኪዳን ለመፈጸም ተነሳ፡ የሰረቀውን አራት እጥፍ ለመመለስ ወሰነ። የእግዚአብሔር ይቅርታ ነፃ ነውና ይህ ቃል ኪዳን እርሱ የሚከፍለው ዋጋ አይደለም፣ ነገር ግን የወደደን እርሱን ለመምሰል መሻት ነው። ዘኬዎስ የማይጠበቅበትን ቁርጠኝነት ወስዷል፣ ነገር ግን የሚያደርገው ይህ የእሱ የፍቅር መንገድ መሆኑን ስለሚረዳ ነው። ይህንንም የሚያደርገው ስለ ስርቆት እና ስለ ንስሐ የወጡትን የሮማውያን ሕግጋት ሁለቱንም አንድ ላይ በማሰባሰብ ነው። ዘኬዎስ የፍላጎት ሰው ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዴት እንደሚወስድ የሚያውቅ ሰው ነው። አላማው ሁሉን አቀፍ ወይም ረቂቅ ሳይሆን ከራሱ ታሪክ ይጀምራል፡ ህይወቱን ተመልክቶ ለውጡን የሚጀምርበትን ነጥብ ለይቷል።
ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ የተገለልን ወይም የመለወጥ አቅም እንደሌለን በሚሰማን ጊዜም ተስፋ እንዳንቆርጥ ከዘኬዎስ እንማር። ኢየሱስን ለማየት ያለንን ፍላጎት እናዳብር፣ እና ከሁሉም በላይ ራሳችንን በጠፋንበት በማንኛውም ጊዜ እኛን ለመፈለግ በሚመጣው በእግዚአብሔር ምሕረት እንድንገኝ እንፍቀድ።