MAP

የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩን በዓል አከባበር የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩን በዓል አከባበር  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የሕሙማን አልጋ ቅዱስ ሥፍራ ሊሆን ይችላል” ሲሉ አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችኮችስ፥ መጋቢት 28/2017 ዓ. ም. የተከበረው የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩን በማስመልከት ባቀረቡት ስብከት፥ “የሕሙማን አልጋ በበጎነት ግድየለሽነት የሚወገድበት እና ምስጋናም ተስፋን የሚያጎለብትበት ቅዱስ ቦታ ሊሆን ይችላል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 27 እና 28/ 2017 ዓ. ም. የተከበረውን የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩን በማስመልከት ላቀረቡት ስብከት የነቢዩ ኢሳይያስን ትንቢት መነሳሻ ማድረጋቸው ታውቋል።

ዕለቱን ምክንያት በማድረግ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩት፥ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ሲሆኑ፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በንባብ ባሰሙት የቅዱስነታቸው ስብከት፥ ምእመናን በስደት ላይ የነበሩ የእስራኤላውያንን ሁኔታ እንዲያጤኑ መጋበዛቸውን በመግለጽ፥ “ሁሉም ነገር የጠፋ ቢመስልም ነገር ግን በፈተና ውስጥ አዲስ አገር ያገኙበት ጊዜ ነበር” ማለታቸውን ገልጸዋል።

ይህንን ተሞክሮ በዕለቱ ከዮሐንስ ወንጌል ተወስዶ በተነበበው ላይ ከተጠቀሰችው ሴት ጋር ያነጻጽሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህች ሴት በኃጢአቷ ምክንያት የተወገዘች እና የተገለለች፥ ከሳሾቿም የመጀመሪያውን ድንጋይ ሊወረውሩባት ተዘጋጅተው ኢየሱስ በሥልጣኑ እንዳቆማቸው እና ኢየሱስም ሴትየዋን፥ “ሄጂ፣ ነፃ ነሽ፣ ድነሻል” ማለቱን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህን ታሪኮች ሲያነጻጽሩ፥ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ጣልቃ ከመግባቱ በፊት ፍጹሞች እንድንሆን እንደማይጠብቅ፣ “ይልቁንም ቁስላችን ውስጥ በመግባት፣ በመከራችን ጊዜ በሮቻችንን ያንኳኳል” ሲሉ አስረድተዋል።

ሕመም እና እንክብካቤ

ሕሙማንን እና እንክብካቤ የሚያደርጉላቸው ሰዎችን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሕመም ከፍተኛ ሥቃይ ሊያስከት እንደሚችል በማመን፥ በስደት ላይ እንደሚገኙ ሰዎች ሊያደርገን እንደሚችል ወይም በወንጌል ውስጥ የተጠቀሰች ሴት ስሜት ሊያሳድርብን እንደሚችል አስረድተዋል። ነገር ግን እርስ በርስ የምንገናኝበት፣ በትህትና እና በጸጋ እርስ በርስ መወደድን የምንማርበት ትምህርት ቤት ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

በደረሰባቸው ሕመም እና በሌሎች ጥገኛ በመሆን ላይ ያሰላሰሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህም ሸክም መሆን ሳይሆን ነገር ግን የመተማመን፣ የምስጋና እና የተስፋ ትምህርት እንደሚሆን አስረድተው፥ “ወደ ኋላ ሳንል እራሳችንን ለመፈቀር እንፍቀድ” ሲሉ አሳስበዋል።

የጤና ባለሞያዎችን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሕሙማንን ለሚንከባከቡ የጤና ባለሞያዎች  ምስጋናቸውን አቅርበው፥ እያንዳንዱን ታካሚ የሰብዓዊነት ስሜታቸውን የሚያድሱበት ዕድል አድርገው እንዲቀበሉ በማበረታታት፥ “የሕሙማን አልጋ በበጎነት ግድየለሽነት የሚወገድበት እና ምስጋናም ተስፋን የሚያጎለብትበት ቅዱስ ቦታ ሊሆን ይችላል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ርህራሄን ማሳየት እንዳለብን አሳስበዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ የቀድሞው ርዕሠ ሊቀ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ መልዕክት በማስታወስ፥ “እውነተኛ የሰው ልጅ ሥቃይ የሚለካው እርስ በርስ ባለው ግንኙነት የሚወሰን ነው” በማለት ቤተ ክርስቲያንን ማስታወሳቸውን ተናግረዋል። “ለአቅመ ደካሞች ፊቱን የሚያዞር ማኅበረሰብ ጨካኝ እና ኢ-ሰብዓዊ ይሆናል” በማለት አስጠንቅቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሥፍራው ለተገኙት በሙሉ ባስተላለፉት መልዕክት፥ አረጋውያንን፣ ሕሙማንን ወይም በአስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ሆነው የሚጨነቁትን የሚያገልል እና የሚያስረሳ ፈተናን እንዲቋቋሙ አሳስበው፥ “ይልቁንም በልባችን ውስጥ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ፍቅር መከራን ወደ ኅብረት እና ወደ ዕድገት ቦታ እንዲለውጠው መፍቀድ አለብን” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

07 Apr 2025, 15:47