የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ዘጠኝ የሐዘን ቀናት መርሐ ግብርን ይፋ አደረገ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጥንት ትውፊቷን ተከትላ ለሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የታገዘ ዘጠኝ የሐዘን ቀናትን አውጃለች።
መስዋዕተ ቅዳሴው ሁሉም ምዕመናን የሚሳተፉበት ቢሆኑም ነገር ግን በእያንዳንዱ ቀን ከቅዱስነታቸው ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው የተለያዩ ማኅበራት አባላት እንደሚሆኑ የወጣው መርሐ ግብር ይገልጻል።
የማኅበራቱ ስብጥር ሁለቱንም ማለትም ከፍተኛ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች እና የሮም ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊነትን የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ታውቋል። (የሮም ጳጳስ የቀብር ሥርዓት ከአንቀጽ 124-125)
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍትን ተከትሎ ቫቲካን ውስጥ በጸሎት፣ በአስተንትኖ እና በዝግጅት ላይ የሚገኙ ካርዲናሎች፥ ረቡዕ ሚያዝያ 16/2017 ዓ. ም. ዕለት ባካሄዱት ሁለተኛው ጠቅላላ ጉባኤ በእያንዳንዱ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለሚሳተፉ ማኅበራት መርሐ-ግብር አውጥተዋል።
ዘጠኝ የሐዘን ቀናት
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ዕረፍት በማስመልከት ከተመደቡት ዘጠኝ የሐዘን ቀናት የመጀመሪያው፥ በቀብራቸው ዕለት ቅዳሜ ሚያዝያ 18/2017 ዓ. ም. ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ይቀርባል። በዚህም መሠረተ ከቅዳሜ ቀጥሎ ባሉትን ቀናት ውስጥ የሚፈጸሙ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች የሚከተሉት ናቸው
እሁድ ሚያዝያ 19/2017 (ሁለተኛ ቀን)፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዓ. ም. ከጠዋቱ አራት ሰዓት ጀምሮ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የሚመሩት ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ሲሆኑ፥ ሥነ-ሥርዓቱን በዋናነት የሚካፈሉት የቫቲካን ግዛት ሠራተኞች እና የከተማው ምዕመናን ይሆናሉ።
ሰኞ ሚያዝያ 20/2017 (ሦስተኛው ቀን)፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከቀኑ በአሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴን የሚመሩት፥ ብፁዕ ካርዲናል ባልዳሳሬ ሬይና፥ የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ሲሆኑ፥ ሥነ-ሥርዓቱን በዋናነት የሚካፈሉት የሮም ሀገረ ስብከት ምዕመናን ይሆናሉ።
ማክሰኞ ሚያዝያ 21/2017 (አራተኛ ቀን)፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የሚመሩት ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ፥ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሊቀ ካህናት ሲሆኑ፥ ሥነ-ሥርዓቱን በዋናነት የሚካፈሉት በሮም የሚገኙ የአራቱ ባዚሊካዎች ሐዋርያዊ አገልጋዮች እና ሠራተኞች ይሆናሉ።
ረቡዕ ሚያዝያ 22/2017 (አምስተኛ ቀን)፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚጀምረውን መስዋዕተ ቅዳሴ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎት ቤቶች ሠራተኞች ጋር በኅብረት ሆነው የሚያቀርቡት ብፁዕ ካርዲናል ሌዮናርዶ ሳንድሪ፥ የካርዲናሎች ጉባኤ ምክትል ሃላፊ ናቸው።
ሐሙስ ሚያዝያ 23/2017 (ስድስተኛ ቀን)፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የሚመሩት፥ ብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ጆሴፍ ፋሬል፥ የሮም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የንብረት እና የፋይናንስ ክፍል አስተዳዳሪ ሲሆኑ፥ ሥነ-ሥርዓቱን በዋናነት የሚካፈሉት በቅድስት መንበር የከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ሠራተኞች ናቸው።
ዓርብ ሚያዝያ 24/2017 (ሰባተኛ ቀን)፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ባዚሊካ ውስጥ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የሚመሩት፥ ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጽሕፈት ቤት የቀድሞ ተጠሪ ሲሆኑ፥ ሥነ-ሥርዓቱን የሚካፈሉት የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሐዋርያዊ አገልጋዮች እና ተወካዮች ናቸው።
ቅዳሜ ሚያዝያ 25/2017 (ስምንተኛ ቀን)፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ባዚሊካ ውስጥ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ከልዩ ልዩ ገዳማት እና ሐዋርያዊ ሕይወት ከተወጣጡ አባላት ጋር በኅብረት የሚመሩት፥ ብፁዕ ካርዲናል አንገል ፈርናንዴዝ አርቲሜ፥ በቅድስት መንበር የመንፈሳዊ ተቋማት እና ሐዋርያዊ ሕይወት ማኅበራት ጽሕፈት ቤት የቀድሞ ተጠሪ ናቸው።
እሑድ ሚያዝያ 26/2017 (ዘጠነኛ ቀን)፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎት ቤቶች ሠራተኞች ጋር ሆነው የሚመሩት፥ ብፁዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ፥ የካርዲናሎች ጉባኤ ሊቀ ካኅን ናቸው።
ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎት ቤቶች ሚያዝያ 22 እና ግንቦት 26/2017 ዓ. ም. የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ በኅብረት ሆነው እንዲያቀርቡ የተፈቀደላቸው ብጹዓን ካርዲናሎች ብቻ እንደሚሆኑ መርሃ-ግብሩ ያስገነዝባል።