የብፁዓን ካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ በቫቲካን ተጀመረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነፍስ በፈጣሪዋ ዘንድ ትረፍ ዘንድ የመጀመሪያው የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ የጽሞና ጸሎት ማክሰኞ ሚያዝያ 14/2017 ዓ. ም. ጠዋት ተጀምሯል።
ሥነ-ሥርዓቱን ምክንያት በማድረግ ወደ ስልሳ የሚጠጉ ካርዲናሎች በሲኖዶሱ አዳራሽ የተሰበሰቡ ሲሆን፥ “ኡኒቨርሲ ዶሚኒቺ ግሬጂስ” ወይም “መላው የእግዚአብሔር መንጋ” በሚለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሐዋርያዊ ደንብ መሠረት፥ የአዲሱ የሮም ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ምርጫን እና ሥነ-ሥርዓቱን በታማኝነት ለመፈጸም ቃለ መሐላ ፈጽመው የመንፈስ ቅዱስን ዕርዳታ በዜማ ጸሎት ጠይቀዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ “መላው የእግዚአብሔር መንጋ” የሚለውን ደንብ የሚመለከቱ አንቅጽ 12 እና 13 ከፍ ባለ ድምጽ የተነበቡ ሲሆን፥ እነዚህ አንቀጾች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሥልጣን በሌለበት ጊዜ ሊከተሏቸው የሚገቡትን ሃላፊነቶችን እና ሂደቶችን የሚዘረዝሩ መሆናቸው ተመልክቷል።
የቅድስት መንበር የንብረት እና የፋይናንስ ክፍል ጠባቂ እና አስተዳዳሪ ብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ፋረል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ቃለ ኑዛዜ ለካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ በንባብ አሰምተዋል።
ጠቅላላ ጉባኤው አዲስ የሚመረጡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እስኪወስኑ ድረስ ሊታወጅ የታሰበው የብጽዕና በዓል እንዲዘገይ አድርጓል።
የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ የቅዱስ አባታችን አስከሬን ከሚገኝበት ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የሚዛወርበትን ቀን የወሰነ ሲሆን፥ ቀደም ሲል የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ቅዳሜ ሚያዝያ 18/2017 ዓ. ም. ከረፋዱ 4:00 ሰዓት ላይ እንደሚፈጸም ማስታወቁ ይታወሳል።
ሁለተኛው የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ረቡዕ ሚያዝያ 15/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት ሲሆን በማለዳው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስከሬን በክብር ወደሚቀመጥበት ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ እንደሚዛወር ታውቋል።
እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት ደንብ መሠረት ዘጠኝ የሐዘን ቀናት የታወጁ ሲሆን፥ እሑድ ሚያዝያ 19/2017 ዓ. ም. በርካታ ምዕመናን በሚገኙበት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንደሚፈጸም ይጠበቃል።
በእነዚህ ልዩ ቀናት ውስጥ ሊፈጸሙ ካታቀዱት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መካከል ሁለተኛ የሆነውን የእሑዱን መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የሚመሩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን እንደሚሆኑ መርሃ ግብሩ አመልክቷል።
እስከ ሰኞ ሚያዝያ 20/2017 ዓ. ም. ድረስ በአሥራ አንድ ሰዓት ላይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚቀርብ ሲሆን፥ ይህም ለቅዱስ አባታችን ነፍስ ዘላለማዊ ዕረፍት ለማግኘት በሚደረግ ጸሎት ላይ ምእመናን እንዲተባበሩ ለማድረግ እንደሆነ ታውቋል።
“መላው የእግዚአብሔር መንጋ” በሚለው የቤተ ክርስቲያኒቱ መመሪያ ደንብ መሠረት፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሥልጣን በሌለበት ወቅት የቅድስት መንበር የንብረት እና የፋይናንስ ክፍል ጠባቂን እና አስተዳዳሪን የሚያግዙ ሦስት ካርዲናሎችን ጠቅላላ ጉባኤው መርጧቸዋል።
እነዚህ ሦስቱ ካርዲናሎች የጠቅላላ ጉባኤውን ሦስት የአባላት ቡድኖችን የሚወክሉ እና በየሦስት ቀናት የሚተኩ መሆናቸው ታውቋል። በዚህም መሠረት ከሦስቱ ካርዲናሎች መካከል የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ተወካይ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላትን እና የቤተ ክኅነቱ ተወካይ ብጹዕ ካርዲናል ስታኒስላው ራይሎኮ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ፍላጎት ለይቶ በማወቅ አስተዳደሯንም የሚመራ ቡድን ተወካይ ብጹዕ ካርዲናል ፋቢዮ ባጆ እንዲሆኑ በማድረግ ጉባኤው መርጠዋቸዋል።
ማክሰኞ ሚያዝያ 14/2017 ዓ. ም. ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነፍስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚደረግ የመቁጠሪያ ጸሎት ምእመናን እንዲተባበሩ ተጋብዘዋል።