MAP

ካርዲናል ፓሮሊን በታላቋ እመቤታችን ማርያም ባዚሊካ ውስጥ የቀረበውን የመቁጠሪያ ጸሎት መርተዋል

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ማክሰኞ ምሽት በታላቋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ አዘጋጅነት የቀረበውን የመቁጠሪያ ጸሎት የመሩ ሲሆን፥ ይህም ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባዚሊካው ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀ የመቁጠሪያ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንደ ነበር ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መታሰቢያ በታላቋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ማክሰኞ ሚያዝያ 14/2017 ዓ. ም. ምሽት ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀውን የመቁጠሪያ ጸሎት መርተዋል።

ብፁዕነታቸው በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ መግቢያ ላይ ባሰሙት ንግግር፥ “ሐዋርያው ​​ጳውሎስ ዓይናችንን ወደ ሰማይ አቅንተን በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመለከት መጋበዙን አስታውሰው፥ “ይህን በማድረግ የዘላለም ሕይወት ለማጣጣም፥ በተለይም በዚህ ምሽት በምናቀረበው ጸሎት የምንወዳቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የሮም ከተማ ጠባቂ ለሆነች ለታላቋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአደራ እንሰጣለን” ብለዋል።

“የክርስቲያኖች ጠበቃ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ ታማልዳለች” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ከአምስቱ የክብር ምሥጢራት መካከል በመጀመሪያው ላይ ያደረጉትን አስተንትኖ ለምዕመናኑ አቅርበዋል።

ብፁዕነታቸው በአስተንትኖአቸው ማጠቃለያ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሕይወታቸው መጨረሻ ስቃያቸውን ለዓለም ሰላም እና ለሕዝቦች ወንድማማችነት ማቅረባቸውንም አስታውሰዋል።

 

23 Apr 2025, 12:11