MAP

ብፁዕ ካርዲናል ጋምቤቲ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የተስፋ ተጓዥ ነበሩ” ሲሉ ገለጹ

በሞት ለተለዩት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀረበውን የመቁጠሪያ ጸሎት የመሩት ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የተስፋ ተጓዥ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል። የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሊቀ ካህናት እና የቫቲካን ግዛት አስተዳደር ረዳት ጳጳስ ይህን የተናገሩት ሰኞ ምሽት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተዘጋጀውን የመቁጠሪያ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት በመሩበት ወቅት ነበር።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በሚያቀርቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፥ ‘ለእኔ መጸለይን አትርሱ’ በማለት የሚያስታውሱንን ልመናችንን በልባችን ይዘን በብርሃነ ትንሳኤው ጉዞአቸው በጸሎት ልንሸኛቸው ይህን ማድረግ እንፈልጋለን” ሲሉ ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ ተናግረዋል።

ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው የእግዚአብሔር ስጦታ ነው!

“በክርስቶስ ትንሳኤ አምነን የምናከብረው ይህ የተቀደሰ በዓለ ትንሳኤ ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ጋምቤቲ፥ “ሞት የተዘጋ በር ሳይሆን ነገር ግን ልቅሶ ወደ ደስታ፣ ማቅም ወደ ደስታ መጎናጸፊያነት ተለውጦ ወደ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም የምንገባበት እንደሆነ እናውቃለን በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።  ብጹዕነታቸው በመቀጠልም፥ “በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አገልግሎት አማካይነት በማያሳዝን ተስፋው ለቤተ ክርስቲያኑ ለሰጣቸው ስጦታዎቹ እግዚአብሔርን እናመስግን” ብለዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተገኙ የ12,000 ምዕመናን ስሜት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሳምባ ምች ምክንያት ለሕክምና በሆፒታል በነበሩበት እንዳደረጉት ሁሉ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሰኞ ሚያዝያ 1432017 ዓ. ም. ምሽት በተዘጋጀው የመቁጠሪያ ጸሎት ላይ ወደ 12,000 የሚጠጉ ምእመናን ተካፋይ ሲሆኑ ብዙዎችም በማኅበራዊ መገናኛዎች ተከታትለውታል።

የባዚሊካው ሊቀ ካህናት ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ በመልዕክታቸው፥ የመድኀኒታችንን የትንሳኤ ምሥጢር በምናሰላስልበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በጸሎት ያስታወሱትን በዓለም ዙሪያ የሚገኝ የእግዚአብሔር መንጋን በማመስገን፥ ወደ መሐሪው እግዚአብሔር ዘንድ ባቀረቡት ጸሎትም የቤተ ክርስቲያን እናት እና የሰማይ ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እና የሐዋርያው ​​ቅዱስ ጴጥሮስን አማላጅነት ለምነዋል።

የቤተ ክርስቲያን እናት የቅድስት ድንግል ማርያም ምስል

ብፁዕ ካርዲናል ጋምቤቲ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ደረጃዎች ላይ በተቀመጡ ነጭ እና ሮዝ አበቦች የተዋበ የቤተ ክርስቲያን እናት የቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ፊት በመሩት የመቁጠሪያ ጸሎት፥ 266ኛውን የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለእመቤታችን ማርያም አማላጅነት በአደራ ሰጥተዋል።

ለንግደት ከዓለም ዙሪያ ወደ ቫቲካን የመጡ ነጋዲያን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተገኝተው በቅዱስነታቸው ህልፈት የተሰማቸውን ድንጋጤ ገልጸዋል። ብልጭ ድርግም በሚሉ መብራቶች ሰኞ ሚያዝያ 13/2017 ዓ. ም. ምሽት የቀረበውን የመቁጠሪያ ጸሎት በየተራ ካደረሱት መካከል የቫቲካን ግዛት ርዕሰ መስተዳድር እህት ራፋኤላ ፔትሪኒ እና በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ እህት አሌሳንድራ ሰሜሪሊ ይገኙበታል።

ብፁዕ ካርዲናል ጋምቤቲ በክብር ምስጢራት ላይ ካሰላሰሉ በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ በታላቅ ፍቅሩ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አገልግሎት አማካይነት እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ ስላበረከቷቸው ስጦታዎች ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእግዚአብሔር ምስክርነት ለተናቁት እና ለችግረኞች ርህራሄን በማድረግ፣ ለኃጢአተኞች ምህረትን በመለመን እና ለሁሉም ቸርነትን የገለጹ መሆናቸውን በማስታወስ በመጨረሻም፥ በመቁጠሪያ ጸሎቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለተገኙት ምዕመናን ቡራኬያቸውን በመጠት ሸኝተዋቸዋል።

22 Apr 2025, 15:58