በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ የጳጳሱ መኖሪያ የነበረው ቤት በሮች በማህተም ታሽገዋል!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞቱበት ምሽት፣ ከእዚህ አለም ድካም ማለፋቸውን የሚያረጋግጥ ሥነ ሥርዓት እና አስከሬናቸው በሬሳ ሣጥን ውስጥ መቀመጡ በቫቲካን መኖሪያው በሚገኘው የጸሎት ቤት ውስጥ ተካሂዷል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስከሬን በሬሳ ሣጥን ውስጥ ከመግባቱ በፊት መሞታቸውን የሚያረጋግጡበት ሥነ-ሥርዓት የተካሄደው ሰኞ ሚያዝያ 11/2017 ዓ.ም ምሽት ላይ ሲሆን በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት አስክሬናቸው ማረፉን እና በእዚያም ለቤተሰቦቻቸው እና ለሥራ ባልደረቦቻቸው ክፍት በመሆን የነብስ ይማር ጸሎት እየደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል።
የሞታቸው ይፋዊ መግለጫ ጮክ ተብሎ ተነቧል። ድርጊቱ የጸደቀው የቅድስት ሮማ ቤተ ክርስቲያን ካሜርሌንጎ ብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ፋሬል ናቸው። ሥነ ሥርዓቱ ከአንድ ሰዓት በታች ብቻ የቆየ እንደ ነበረም ተግልጿል።
በሐዋርያዊው ጽሕፈት ቤታቸው ሦስተኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የጳጳሱ ቢሮ እና ጳጳሱ ይኖሩበት በነበረው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ባለው የምኖሪያ ቤታቸው በር ላይ ማኅተሞች ተደርጎባቸው ታሽገዋል።
ማክሰኞ ጠዋት ሚያዝያ 14/2017 ዓ.ም የመጀመሪያው የካርዲናሎች አጠቃላይ ጉባኤ ይካሄዳል፣ በዚህ ጊዜ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የሚፈጸምበት ቀን ሊወሰን ይችላል።