MAP

የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶች ለድሆች ቅድሚያን እንዲሰጡ ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሁድ መጋቢት 28/2017 ዓ. ም. ባስተላለፉት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት መልዕክታቸው፥ ለጤና ባለሞያዎች ድጋፍ እና አክብሮት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በተጨማሪም ያፈው ሰኞ መጋቢት 22/2017 ዓ. ም. ሁለት መነኮሳት የተገደሉበትን የሄይቲ ሁከት በማውገዝ በመላው ዓለም ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዐብይ ጾም 5ኛ እሑድ መልዕክት ይፋ አድርጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው እሑድ መጋቢት 28/2017 ዓ. ም. ከዮሐ. 8 ተወስዶ በተነበበው እና ኢየሱስ ጎንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ መጻፉን በሚናገር የወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን፥ ጻፎችና ፈሪሳውያን በድንጋይ ሊገድሏት ለሚፈልጓት ሴት “አዲስ ታሪክ” መጻፉን ተናግረዋል።


“የእግዚአብሔር ፈዋሽ እጅ”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሆስፒታል ውስጥ በቆዩባቸው ጊዜያት እና ወደ ቫቲካን ተመልሰው ባሳለፏቸው 15 የማገገሚያ ቀናት ውስጥ የተገነዘቡትን የእግዚአብሔር እጅ እና የእርሱ የደግነት እንክብካቤን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩ በተከበረበት እሑድ መጋቢት 28/2017 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የእግዚአብሔር የፍቅሩ እንክብካቤ በስቃይ ላይ የሚገኙትን እና እነርሱን የሚንከባከቧቸውን የጤና ባለሞያዎችን እንዲያበረታታቸው” በማለት በጸሎት ጠይቀዋል።

አንዳንድ ጊዜ በሥራቸው መካከል ዶክተሮችን፣ ነርሶችን እና የጤና ባለሞያዎችን የሚደርስ ጥቃት ያሳሰባቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ተልዕኳቸው ቀላል እንዳልሆነ በማስረዳት ድጋፍ እና አክብሮት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም፥ የዓለም መሪዎች በሕክምናው እና በምርምር ዘርፍ መዋዕለ ንዋይ እንዲመድቡ ጥሪ አቅርበው፥ “የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶች እጅግ ድሃ እና ደካማ የሆኑ ሰዎችን የሚያቅፉ እና ትኩረት የሚሰጡ እንዲሆኑ” በማለት አሳስበዋል።

በመላው ዓለም ሰላም እንዲወርድ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ወትሮው ምእመናን ለዓለም ሰላም እንዲጸልዩ ጠይቀው፥ በተለይም በጦርነት ምክንያት በበርካታ ንጹሃን እና ህጻናት ላይ ጥቃቶች በሚደርስባት ዩክሬን ውስጥ ሰላም እንዲወርድ መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸሎት ጥሪያቸውን ያቀረቡት፥ የቫቲካን የውጪ ሃገራት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ከሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርገይ ላቭሮቭ ጋር በስልክ ከተነጋገሩ ከሁለት ቀናት በኋላ እንደሆነ ታውቋል።

ነዋሪዎቿ በማይታሰብ ሁኔታ ያለ መጠለያ፣ ያለ ምግብ እና ያለ ውሃ የሚሰቃዩባትን ጋዛን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በሁለቱ ወገኖች ማለትም በእስራኤል መንግሥት እና በጋዛ ታጣቂዎች መካከል የሚደረግ የሰላም ድርድር እንደገና እንዲጀመር፣ ታጋቾች እንዲፈቱ እና የጦር መሣሪያ ጥቃት እንዲቆም በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

“በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን፣ በዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በመሬት መንቀጥቀጥ በተመታች በርማ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን እንጸልይ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሁለት መነኮሳት የተገደሉበትን የሄይቲን አመጽ አውግዘዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህም በላይ ስፖርት ለሰላም እና ለልማት በሚል ርዕሥ በተከበረው ዓለም አቀፍ ቀን ባስተላለፉት መልዕክትም፥ “ስፖርት ሰላምን እና ማኅበራዊ አንድነትን ለሚፈልጉ ብዙ ሰዎች የተስፋ ምልክት ይሆናል” በማለት ገልጸው፥ በመጨረሻም በሮም ከሚገኝ ረቢቢያ ወሕኒ ቤት ታራሚ ሴቶች ለተላከላቸው የመልካም ምኞት መግለጫ ካርድ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

07 Apr 2025, 15:58