የየካቲ 30/2017 የመጀመሪያው የዐብይ ጾም ሣምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የእለቱ ንባባት
1. ዘዳግም 26፡4-10
2. መዝሙር 90
3. ሮም 10፡8-13
4. ሉቃስ 4፡1-13
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
የኢየሱስ መፈተን
ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ በምድረ በዳም በመንፈስ ተመራ። ለአርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ። በእነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፤ ቀኖቹም በተፈጸሙ ጊዜ ተራበ። ዲያብሎስም፦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ፤” አለው። ኢየሱስም፦ “ ‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤” ብሎ መለሰለት። ዲያብሎስም ከፍ ወዳለው ስፍራ አውጥቶት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። ዲያብሎስም፦ “ለአንተ ይህን ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውንም እሰጥሃለሁ፤ ለእኔ ተሰጥተቶአልና ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁ፤ 7ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤” አለው። ወደ ኢየሩሳሌም ደግሞ ወሰደው፤ በመቅደስም ጫፍ ላይ አቆመው፥ እንዲህም አለው፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ ከዚህ ወደ ታች ራስህን ወርውር፤ እነሆ፥ ‘አንተን ለመጠበቅ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህም በድንጋይ ከቶ እንዳይሰናከል አንተን በእጃቸው ያነሡሃል፤’ ተብሎ ተጽፎአልና።” ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ጌታን አምላክህን አትፈታተነው፤’ ተብሏል፤” አለው። ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ለጊዜው ከእርሱ ተለየ።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
በዛሬው ስርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል የዐብይ ጾም የመጀመሪያ እሑድ የሚያስታውሰን ሲሆን ይህም ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ለአርባ ቀናት በዲያብሎስ ሊፈተን ወደ በረሃ መወሰዱን ይገልጽልናል (ሉቃ. 4፡1-13)። ኢየሱስም በዲያብሎስ ተፈትኗል፣ እናም በፈተናዎቻችን ውስጥ ከእያንዳንዳችን አብሮን ይሄዳል። በረሃው ከክፉ ማባበያዎች ጋር የሚደረገውን ትግል ያመለክታል፣ እውነተኛ ነፃነትን ለመምረጥ እንዴት እንደ ምንችል እንማርበታለን። በእርግጥም ኢየሱስ ተልእኮውን በይፋ ከመጀመሩ በፊት የበረሃን ሕይወት ልምድ ይኖራል። እሱ ምን ዓይነት መሲሕ መሆን እንዳሰበ በቆራጥነት ያረጋገጠው በዚህ መንፈሳዊ ውጊያ አማካኝነት ነው። የዚህ ዓይነት መሲህ ሳይሆን ያኛው፡ እኔ የምለው ይህ የኢየሱስ መሲሃዊ ማንነት መግለጫ፣ የኢየሱስ መሲሃዊ መንገድ ነው። "እኔ መሲሁ ነኝ፣ ግን በዚህ መንገድ" ነው የምጓዘው እንግዲያውስ እየታገለ ያለውን ፈተና በትኩረት እንመልከታቸው።
ዲያብሎስ ሁለት ጊዜ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ…” ብሎ ጠራው (ሉቅስ 4፡3፣9)። ስለዚህም እሱ ቦታውን እንዲረከብ ሐሳብ አቅርቧል፡ በመጀመሪያ የሚሰማውን ቁሳዊ ፍላጎት ለማርካት፣ ረሃብ (ሉቃስ 4፡3)፣ ከዚያም ስልጣኑን ለመጨመር (ሉቃስ 4፡6-7)። እናም በመጨረሻም፣ ታላቅ ተዐምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲያሳየው (ሉቃስ 4፡9-11)። ሶስት ፈተናዎች። “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እድሉን ተጠቀምበት!” ያለው ያህል ነው። ይህ ምን ያህል ጊዜ ይደርስብናል፡ “ነገር ግን በዚያ ቦታ ላይ ከሆንክ ተጠቀምበት! ዕድሉ አያምልጥህ፣ ዕድሉን ተጠቀሙበት" ማለትም "ጥቅማችሁን አስቡ" እንደማለት ነው። እሱ አሳሳች ሀሳብ ነው ፣ ግን ወደ ልብ ባርነት ይመራናል፣ በግል በፍላጎት እንድንጠመድ ያደርገናል ፣ ሁሉንም ነገር ወደ ቁሳዊነት፣ ስልጣን ፣ ዝና ይቀንሳል ። ይህ የፈተናዎቹ ዋና አካል ነው። ክፋት የመነጨበት "የምኞት መርዝ" ነው። ራሳችንን እንመልከት፣ እናም የእኛ ፈተናዎች ሁል ጊዜ ይህ አስተሳሰብ፣ እንደዚህ አይነት የድርጊት መንገድ እንዳላቸው እናገኘዋለን።
ኢየሱስ ግን የክፋትን መስህቦች በአሸናፊነት ይቃወማል። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ለፈተናዎች በእግዚአብሔር ቃል ምላሽ በመስጠት፣ ይህም ጥቅምን ላለመፈለግ፣ እግዚአብሔርን፣ ሌሎችን እና ነገሮችን ለራስ አለመጠቀም፣ መብቶችን ለማግኘት የራሱን ቦታ አለመጠቀም። ምክንያቱም እውነተኛ ደስታ እና እውነተኛ ነፃነት በመካፈል እንጂ ለራሳችን ብቻ በመያዝ ላይ አይደሉም የተመሰረተው፣ ሌሎችን በመውደድ እንጂ ሌሎችን በመጥቀም አይደለም። በኃይል ፍላጎት ሳይሆን በአገልግሎት ደስታ ውስጥ ነው የሚገኘው።
ወንድሞች እና እህቶች፣ እነዚህ ፈተናዎች በህይወት ጉዞ ላይ አብረውን ይመጣሉ። ንቁ መሆን አለብን - አትፍሩ፣ በሁሉም ሰው ላይ ይከሰታል - እና ንቁ ሁኑ፣ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን በመልካም ሁኔታ ውስጥ ያሳያሉ። እንደውም ተንኮለኛው ዲያብሎስ ሁል ጊዜ ማታለልን ይጠቀማል። ኢየሱስ በእውነት የአምላክ ልጅ መሆኑን ለማረጋገጥ ያቀረበው ሐሳብ ጠቃሚ እንደሆነ እንዲያምን ፈልጎ ነበር። እኛንም እንዲሁ ያደርጋል፡ ብዙ ጊዜ "በጣፋጭ ዓይኖች" "የመልአክትን ፊት ለብሶ" ይመጣል፣ በተቀደሰ ፣ ሃይማኖታዊ ዓላማዎች ራሱን እንዴት መደበቅ እንዳለበት እንኳን ያውቃል!
እናም አንድ ነገር ላይ አፅንዖት መስጠት እፈልጋለሁ። ኢየሱስ ከዲያብሎስ ጋር አልተነጋገረም፤ ከዲያብሎስ ጋር ፈጽሞ አልተነጋገረም። እርሱ በእርኩስ መንፈስ የተያዙትን ሰዎች ሲፈውስ ዲያብሎስን ሲያባርረው ይታያል፣ በራሱ ቃላት ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃላት ሲገስጸው እናያለን። ወንድሞች እና እህቶች፣ ከዲያብሎስ ጋር በፍፁም አትነጋገሩ፡ ከእኛ የበለጠ ተንኮለኛ ነው። በጭራሽ! እንደ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ቃል የሙጥኝ ብለን በመያዝ እና ቢበዛ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ቃል መልስ መስጠት ይገባል። እናም በዚህ መንገድ በጭራሽ አንሳሳትም።
ዲያብሎስ ከእኛ ጋር ይህን ያደርጋል፡ ብዙ ጊዜ "በገር ዓይኖች"፣ "የመልአክትን ፊት ለብሶ" ይመጣል። በተቀደሰ ፣ ሃይማኖታዊ ዓላማዎች እራሱን እንዴት መደበቅ እንዳለበት እንኳን ያውቃል! ለእርሱ ሽንገላ እጅ ከሰጠን ውሸታችንን በመልካም ዓላማ በመደበቅ እናጸድቀዋለን። ለምሳሌ ምን ያህል ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ይሰማናል "እንግዳ ነገር አድርጌአለሁ ነገር ግን ድሆችን ረድቻለሁ" "የእኔን ሚና - እንደ ፖለቲከኛ፣ ገዥ፣ ቄስ፣ ጳጳስ ሆኜ አከናውኛለሁ - ነገር ግን ለበጎ ነው"፤ "በደመ ነፍሴ ሰጥቻለሁ፣ ነገር ግን በመጨረሻ፣ በማንም ላይ ምንም ጉዳት አላደረስኩም" እነዚህ መመጻደቂያዎች እና ሌሎችም አንዱ ከሌላው እየጨማመርን እንመጻደቃለን። እባካችሁ ከክፉ ነገር ጋር ምንም ስምምነት አትድርጉ! ከዲያቢሎስ ጋር ምንም ውይይት የለም! ከፈተና ጋር ወደ ውይይት መግባት የለብንም፣ “ነገር ግን ነገሩ ቁምነገር አይደለም፣ ሁሉም ያደርገዋል” እንድንል በሚያደርገን የህሊና እንቅልፍ ውስጥ ልንወድቅ አይገባም! ኢየሱስን እንመልከት፣ ማደርያ የማይፈልግ፣ ከክፉ ጋር የማይስማማ መስሕ ነበር። ከዲያብሎስ በሚበረታው በእግዚአብሔር ቃል ዲያብሎስን ይቃወማል፣ በዚህም ፈተናን ያሸንፋል።
ይህ የዐብይ ጾም ጊዜ ለእኛም የበረሃ ልምድ የምናገኝበት ጊዜ ይሁንልን። ለዝምታ እና ለጸሎት ጊዜ እንስጥ - ትንሽ ትንሽ ብናደርግ ይጠቅመናል - በእነዚህ ቦታዎች ቆም ብለን በልባችን ውስጥ የሚያነሳሳውን፣ የውስጣችንን እውነት እንመልከት። ራሳችንን በእግዚአብሔር ቃል ፊት በጸሎት እናስቀምጠው፣ ውስጣዊ ግልጽነትን እናግኝ፣ ይህም በባርነት ከሚገዛን ክፋት ጋር አወንታዊ ትግል፣ የነጻነት ትግል፣ በውስጣችን እንዲፈጠር ይረዳናል።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዐብይ ጾም በረሃ ሰዓት እንድትሸኘን እና በሕይወታችን መንገድ እንድትረዳን እንማጸናት።