ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው የተመረጡበት 12 ዓመት ታስቦ ዋለ!
የእዚህ ዘገባ አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ 12 ዓመታት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዓመታት ውስጥ በተለየ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያን ሚስዮናዊ የሆነ ተግባሯን አጠናክራ እንድትቀጥል እና ለሁሉም የሰው ልጆች በቅዱስ ወንጌል የሚገኘውን ደስታ እንድታበስር፣ በማንኛውም ቅዱስ ወንጌልን የማብሰር ሂደት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በቀጥታ ተሳታፊ ይሆን ዘንድ በመፍቀድ ማከናውን እንደ ሚገባው ቅዱስነታቸው አበክረው መናገራቸው እና አሁንም ቤተ ክርስቲያን በእዚሁ መንገድ እንድትቀጥል ማሳሰባቸውን በፍጹም አላቋረጡም።
ቅዱስነታቸው በእነዚህ 12 ዓመታት ውስጥ አራት ጳጳሳዊ መልእክቶችን ለንባብ አብቅተዋል። በላቲን ቋንቋ “Lumen fidei” (እ.አ.አ በሰኔ 29/2013 ዓ.ም) በአማርኛው “የእመነት ብርሃን” የተሰኘና በእምነት ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ ጳጳሳዊ መልእክት፣ እ.አ.አ በግንቦት 24/2015 ዓ.ም “Laudato si” በአማርኛው “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በሚል አርእስት የጋራ የመኖሪያ ቤታችንን የመንከባከብ ኃላፊነት ሁላችንም እንዳለብን በማስመልከት የጻፉት ደግሞ ሁለተኛው ጳጳሳዊ መልእክት ሲሆን፣ እ.አ.አ በጥቅምት 03/2020 ዓ.ም በጣሊያነኛ ቋንቋ "Fratelli tutti" በአLjኛው (ሁላችንም ወንድማማቾች ነን) በተሰኛው ጳጳሳዊ መልእክታቸው የጋራ የመኖርያ ቤታችን በሆነችው አለማችን ውስጥ ሁላችንም እንደ አንድ ቤተሰብ እንኖራለንና ዓለምን ወደነበረበት ለመመለስ እና በተከሰቱት ወረርሽኞች ቀውስ የተከሰቱትን በሽታዎች ለማሸነፍ ተጨባጭ እርምጃዎችን የምያቀርብ፣ ይህም አሁን የሚታዩትን የጤና፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ አንትሮፖሎጂካል (ስነ-ሰብዕዓዊ) እና ፖለቲካዊ ቀውሶች እና ሰላማዊ መፍትሄዎቻቸውን የምያወሳ ጳጳሳዊ መልእክት ደግሞ ሦስተኛው ነው፥ በመጨረሻም እ.አ.አ በጥቅምት 24/2024 ዓ.ም በላቲን ቋንቋ "Dilexit nos" (እርሱ ወደደን፣ ሮም 8፡37-39፣ ዩሐንስ 15፡9-12፣ 1ዩሐ 4፡10) በሚል አርዕስት በኢየሱስ ክርስቶስ የተቀደሰ ልብ ሰብዓዊ እና መለኮታዊ ፍቅር ላይ ያተኮረው አራተኛው ጳጳሳዊ መልእክታቸው ነው።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእነዚህ 12 የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ሰባት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያዎችን ወይም ሐዋርያዊ ምክረ ሐሳቦችን ለንባብ ማብቃታቸው የሚታወቅ ሲሆን እነዚህም በላቲን ቋንቋ “Evangelii gaudium” በአማርኛ ሲተረጎም “በወንጌል የሚገኝ ደስታ” በሚል አርእስት እ.አ.አ በኅዳር 24/2013 ዓ. ም. ለንባብ ያበቁት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፣ በእዚህም (ቤተ ክርስቲያን በጉዞ ላይ መሆን እንዳለባትና ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን ለማከናወን፣ ሰዎችን ወደ እግዚኣብሔር ለመመለስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደ ሕዝቡ መሄድ እንዳለባት የሚያሳስብ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ወይም ምክረ ሐሳብ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አሁንም በላቲን ቋንቋ “Amoris Laetitia” &Բ;በአማርኛው&Բ;“የፍቅር ሐሴት” በሚል አርእስት እ.አ.አ. በመጋቢት 19/2016 ዓ. ም. ለንባብ ያበቁት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ሲሆን ይህ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር፣ በቤተሰብ ውስጥ ስለሚታዩ ተግዳሮቶች፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለቤተሰብ ማድረግ ሰለሚጠበቅባቸው ሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚያወሳ ድህረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክረ ሐሳብ ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል። በእዚህ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ በተለይም የኃይማኖት አባቶች በቤተሰብ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በጥንቃቄ እና ብስለት በተሞላበት መልኩ፣ በጥንቃቄ በመመርመር በቤተሰብ ውስጥ የሚያግጥሙ ችግሮችን በችኮላ ከማውገዝ ይልቅ በእግዚአብሔር ምሕረታዊ ጸጋ በመታገዝ የመፍትሄ ሐሳቦችን መጠቆም እንደ ሚገባቸው፣ ይህንንም ክህሎት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ማዳበር እንዲችሉ ቤተሰብን የተመለከተ ትምህርቶች ከዘረዐ ክህነት ትምህርት ቤት ጀምሮ መስጠት አስፍላጊ መሆኑን የሚገልጽ ቃለ ምዕዳን ነው።
በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በላቲን ቋንቋ “Gaudete et exsultate” በአማርኛው “ደስ ይበላችሁ፣ ሐሴትም አድርጉ” በሚል አርዕስት እ.እ.አ. በመጋቢት 19/2018 ዓ.ም ለንባብ የበቃው እና በዛሬው ዓለም ውስጥ ወደ ቅድስና የሚወስደውን መንገድ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል የሚገልጽ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ወይም ምክረ ሐሳብ ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን “ደስ የበላችሁ ሐሴት አድርጉ” በሚል አርእስት ይፋ በሆነው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ወይም ምክረ ሐሳብ ከላይ ለመጥቀስ እንደ ሞክርነው መላው የዓለማችን ሕዝቦች በደስታ የተሞላ ሕይወት ይኖራቸው ዘድን፣ ከእዚያም በመቀጠል የቅድስና ሕይወት ለመኖር ይሞክሩ ዘንድ ጥሪ በማቅረብ ይህንን የቅድስና መንገድ ለመከተል ለሚፈልጉ የሰው ልጅ ሁሉ መንገዱ ክርስቶስ ብቻ እንደ ሆነ በስፊው የምገልጽ፣ በዛሬው ዓለማችን ውስጥ እርሱን (ኢየሱስን ማለት ነው) መከተል አሁን ባለው ዓለማችን በሰፊው እየተነጸባረቀ ከምገኘው ገንቢ ያልሆነ አስተሳሰብ በተቃራኒው መጓዝ ማለት በመሆኑ የተነሳ በእዚህ ዓለም ውስጥ በአሁን ወቅት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እየተከሰቱ የሚገኙትን መከራዎች እና ፍትሃዊ ያልሆኑ ተግባራት ከእነርሱ መሸሽ ማለት ሳይሆን በከፍተኛ ብርታት እነዚህን ነገሮች ሰላምዊ በሆነ መልኩ መዋጋት፣ ትሁት መሆን እና የርኅራኄን መንፈስ በመላበስ ወደ ቅድስና መንገድ ያለምንም ፍርሃት መጓዝ እንደ ሚገባ የሚገልጽ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ነው።
በአራተኛ ደረጃ ደግሞ በላቲን ቋንቋ “Christus Vivit” በአማርኛው “ኢየሱስ ህያው ነው” በሚል አርዕስት እ.አ.አ በመጋቢት 25/2019 ዓ.ም ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ሰለ ወጣቶች እና የመጪ ጊዜ ተስፋዎቻቸውን በመዳሰስ ‘ክርስቶስ ተስፋችን ነው’ በሚል ጭብጥ ዙሪያ ላይ በማጠንጠን ወጣቶች መቼም ቢሆን ተስፋ እንዳይቆርጡ የሚጋብዝ ሐዋርያዊ ምክረ ሐሳብ ወይም ማሳሰቢያ ነው።
በአምስተኛ ደረጃ ደግሞ እ.አ.አ በየካቲት 2/2020 ዓ.ም እና እ.አ.አ በጥቅምት 4/2023 ዓ.ም በቅደም ተከተል በስፓኒሽ ቋንቋ “Querida Amazonia” (ውድ አማዞን) በሚል አርዕስት በአማዞን ጥቅጥቅ ደን ውስጥ የሚኖሩ ቀደምት ሕዝቦችን ከአደጋ መከላከል እና መጠበቅ የምያወሳው አምስተኛው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው ነው።
በስድተኛ ደረጃ ደግሞ አሁንም በላቲን ቋንቋ “Laudate Deum” “እግዚአብሔርን አወድሱት” በሚል አርዕስት እግዚአብሔር አስተካክሎ የፈጠራትን ምድራችንን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ማውደም ተገቢ እንዳልሆነ፥ እግዚአብሔርን ፍጥረታቱን በመመልከት ማወደስ እንደሚገባ የሚገልጽ ሐዋርያዊ ምክረ ሐሳብ ወይም ማሳሰቢያ ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
በሰባተኛ ደረጃ ቅዱስነታቸው በእነዚህ 12 አመታት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ለንባብ ያበቁት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ደግሞ "C’EST LA CONFIANCE " (መተማመን ነው) በሚል አርእስት በእግዚአብሔር መሐሪ ፍቅር ላይ በመተማመን መኖር እንደሚገባ የሚገልጸው የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ነው።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእነዚህ 12 የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዓመታት በላቲን ቋንቋ “Motu proprio” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም (አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እንደራሴ በመሆኑ፣ በእዚህ በተሰጠው መንፈሳዊ ስልጣን በራሱ ተነሳሽነት ወቅታዊ ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባ መልኩ የሚጽፋቸው ሰነዶች፣ የሚያደርጋቸው ሹመቶች፣ ውሳኔዎች የተመለከቱ ጉዳዮችን ያመለክታል) በእዚህም መሠረት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግላዊ ተነሳሽነት በርካታ መልእክቶች መጻፋቸው ይታወቃል። እነዚህ በእርሳቸው የግል ተነሳሽነት የተጻፉ በርካታ መልእክቶች ወይም በላቲን ቋንቋ “motu proprio” ‘ሞቱ ፕሮፕሪዮ’ መልእክታቸው “የቅድስት መንበር የበላይ የመስተዳድር አካላት እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የቅርብ የሥራ ተባባሪዎች የመማክርት ጉባሄ ጥልቅ የሆነ ታሀድሶ እንዲያደርጉ የሚያሳስቡ መልእክቶች፣ በቅድስት መንበር ውስጥ በተለይም ደግሞ በፋይናንስ እና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያሳስቡ መልእክቶች፣ በአንድ ባል እና በአንድ ሚስት መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን እንዴት ለመፍታት እንደ ሚቻል--ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ማስቀመጥን የተመለከተ መልእክት፣ ለስርዓተ አምልኮ አገልግሎት ጥቅም ላይ የሚውሉ መንፈሳዊ መጽሐፍት በእየአንዳንዱ ሀገር ብጹዕን ጳጳሳት እውቅና አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚመጣጠን መልኩ ውጤታማ እንዲሆኑ ክለሳ እንዲደረግባቸው የሚጠይቅ መልእክት፣ እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ አርእስቶችን ያቀፉ በርካታ "ሞቱ ፕሮፕሪዮ" በራሳቸው ተነሳሽነት በጣም ተጨባጭ እና ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ገንቢ የሆኑ ሐሳቦችን በማንሳት ለመፍትሄ ማቅረባቸው ይታወቃል።
ቅዱስነታቸው በእነዚህ 12 የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ውስጥ ቤተሰብን በተመለከተ ሁለት ጳጳሳዊ ሲኖዶሶች እንዲደረጉ ማድረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን በዚህም ወቅታዊ በሆነ መልኩ በቤተሰብ መካከል አሁን የሚታዩ ተግዳሮቶችን በማንሳት እና ትኩረት በመስጠት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በቤተሰብ ጉዳይ እንዲመክሩ በማድረግ ወቅታዊ ለሆኑ ችግሮች ወቅታዊ የሆነ ምላሽ በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚሰጥበትን የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲቀይስ በር መክፈታቸው ይታወሳል።
ከታኅሳስ 01/2008 ዓ. ም. እስከ ኅዳር 11/2009 ዓ. ም. ድረስ ለ349 ቀናት ያህል የቆየው ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት ኢዩቤልዩ ማወጃቸው የሚታወስ ሲሆን ይህንን ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት በወቅቱ በክርስቲያኖች እና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ በተነሳው የእርስ በእርስ ግጭት ተጎሳቁላ በነበረች ሀገር በመገኘት የሁለቱንም የኃይማኖት ተቋማት ተወካዮች በአንድነት ፊት ለፊት አቀራርበው በማናጋገር እርቅ እንዲፈጥሩ መንገዱን በመክፈት፣ በእዚያው በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ በባንጉዊ ከተማ በሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካቴድራል ተገኝተው ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት ኢዩቤሊዪን ማስጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን በእነዚህም 349 ቀናት ውስጥ ምዕመናን መንፈሳዊ እና አካላዊ የምሕረት ተግባራት የሚፈጸሙበት ወቅት መሆኑን ገልጸው፣ በእዚህ ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት ክርስቲያኖች እርቅን እና ሰላምን ይፈጥሩ ዘንድ ማሳሰባቸው ይታወቃል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በ12 ዓመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ከጣሊያን ውጭ 47 ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በእነዚህም ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በአፍሪካ አህጉር የሚገኙትን ኬኒያን፣ ኡጋንዳን እና የመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ፣ ግብፅ፣ ደቡብ ሱዳን አንስቶ በኩባ በአሜሪካ፣ በላቲን አሜሪካ በምስራቅ አውሮፓ እና በኤሺያ አህጉር፣ በመካከለኛው አሜሪካ እና በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ የሆነችውን አቡዳቢ፣ ኢራቅ ወዘተ ... ድረስ በመጓዝ የሰላም እና የአንድነት መልእክት ማስተላለፋቸው የሚታወቅ ሲሆን 900 የካቶሊክ ምዕመናን የሚገኙባትን አዛረበጃንን ጨምሮ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የእስልምና እምነት ተከታይ ወደ ሆኑባቸው ባንግላዲሽ እና የቡዳ እምነት ተከታይ ወደ ሚበዛባት ማያን ማር (የቀድሞ ስሟ በርማ) ድረስ በመሄድ፣ በቅርቡ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ ወደ ሆነችው አቡዳቢ በመሄድ የሰለም እና የአንድነት መልእክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወሳል። በጣሊያን ግዛት ውስጥ ብቻ 17 ጣሊያን ግዛቶችን በተለይም ደግሞ በተፈጥሮ አደጋ ለምሳሌም በርዕደ መሬት አደጋ ጉዳት የደረሱባቸውን እና ከአፍሪካ እና ከተለያዩ አገራት የተውጣቱ ስደተኞች ወደ አውሮፓ አህጉር መግቢያ በር አድርገው የሚጠቀሙበትን የላፓዱዛ ደሴትን ጭምር በመጎብኘት ለስደተኞች ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ሰብአዊ መብታቸው እንዲከበር ለዓለም ድምጻቸውን ማሰማታቸው እና ዓለም ለስደተኞች ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ማሳሰባቸው የሚታወስ ሲሆን ስደተኞችም በበኩላቸው በእንግድነት የሚቀበሉዋቸውን ሀገሮች ማሕበራዊ ሕግጋቶችን በማክበር እንዲኖሩ፣ በእንግድነት የተቀበላቸውን ማኅበረሰብ ወግ እና ባሕል እንዲጠብቁ ማሳሰቢያ መስጠታቸውም ይታወሳል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእነዚህ 12 የርዕስ ሊቃነ ጵጵስና አገልግሎታቸው ዘመን ዘወትር ረቡዕ ዕለት ባደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከ30 በላይ ልዩ ልዩ አርእስቶችን በስፋት በመዳሰስ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማድረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን በእነዚህ የጠቅላላ የትምህረተ ክርስቶስ አስተምህሮዎች “የእመታችን መገለጫ ከሆነው የጸሎተ ሃይማኖት አንስተው ሰባቱን የቤተክርስቲያን ምስጢራት፣ የመንፍስ ቅዱስ ስጦታዎችን የተመለከቱ፣ ቤተ ክርስቲያንን፣ ቤተሰብን፣ ምሕረትን፣ የክርስቲያን ተስፋን እና በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ዙሪያ እና በቅርቡ “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ እና አሁን ደግሞ “መልካም እና ክፉ ስነ-ምግባር” በሚል ዐብይ አርእስት ላይ በተከታታይ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አድርገው ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ነው፣ አሁን ያልንበትን የኢዩበሊዩ አመት ምክንያት በማድረግ ቅዱስነታቸው በሕመም ምክንያት ሆስፒታል እስከገቡበት እለት ድረስ "ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን ነው፣ የኢየሱስ የልጅነት ጊዜ" በሚል አርእስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አሰትምህሮ እያደረጉ እንደ ነበረ ይታወሳል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “@ pontefix” "X" በተሰኘው የቲውተር ገጻቸው ላይ በየዕለቱ በሚያስተላልፉት ምልእክት በዓለም ዙሪያ 56 ሚልዮን በላይ ተከታይ እንዳላቸው የሚያሳይ ሲሆን በተጨማሪም Instagram በተሰኘው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ 6 ሚልዮን ተከታዮች እንዳላቸው ይታወቃል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ተተኪ በመሆን የዛሬ 12 አመት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 266ኛው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው መመረጣቸው የሚታወቅ ሲሆን በትውልድ አርጄንቲናዊ የሆኑ የ88 አመት የእድሜ ባለጸጋ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ምዕረጋቸውን ከመቀበላቸው በፊት የነበራቸውን ካርዲናል በርጎሊዮ የሚለውን የመጠሪያ ስማቸውን በመቀየር በ13ኛ ክፍለ ዘመን የኖረውን እና “የድሆች አባት” በመባል የሚታወቀውን የአዚዚውን የቅዱስ ፍራንቸስኮ ፈለግ ለመከተል በማሰብ የእርሱን የመጠሪያ ስም የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስናቸው ዘመን መጠሪያ እንዲሆን መምረጣቸው የሚታወቅ ሲሆን በእዚህም መስረት “ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም በሯን ክፍት ያደርገች፣ ለሁሉም የሰው ልጆች በቅዱስ ወንጌል የሚገኘውን ደስታ ማወጅ እና ማብሰር እንደ ሚገባት " ምኞታቸው መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች መግለጻቸው ይታወቃል።
“ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም የሰው ልጆች ማስተናገድ የሚትችል የሰው ልጆችን እንደ ሕይወታቸው ፈተና እና ድካም ቦታ ልትሰጣቸው የምትችል ቤተ ክርስቲያን እንደ ሚመኙ መግለጻቸው የሚታወቅ ሲሆን በጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም የሰው ልጆች ተደራሽ መሆን ይገባታል፣ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ የሕይወት ጫናዎች ምክንያት ከቆሰሉ ሰዎች ጋር በመሆን የፈውስ ሂደት አካል ልትሆን ይገባታል የሚል ጽኑ አቋም እንደ ሚያንጸባርቁ ያታወቃል። “አንድ በምቾት ውስጥ ያለች ቤተ ክርስቲያን በራሷ ምቾት ብቻ ራሷን ቆልፋ የምትኖር ከሆነ ያቺ ቤተ ክርስቲያን ጤናማ ቤተ ክርስቲያን ልትባል አትችልም” በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህንን የመሳሰሉ አሉታዊ ባሕርይ ያልቸው አብያተ ክርስቲያናት ይህንን አፍራሽ የሆነ ባሕሪይ በማስወገድ ሰውን ከእግዚኣብሔር ለማገናኘት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመወጣት በእምነት የሚገኘውን ውበት እና ደስታ ለሰው ዘር በሙሉ ማሳየት እንደ ሚኖርባት ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በእዚህ በ12 ዓመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዓመታት በዋነኛነት እና በማዕከላዊነት “ምሕረት” የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ መጠቀማቸው የሚታወቅ ሲሆን በእዚህም መሠረት “የሰማይ አባታችሁ መሐሪ እንደ ሆነ እናንተም ምሕረት አድራጊዎች ሁኑ” የሚለው የክርስቲያኖች የእለት ተእለት መፈክር ሊሆን ይገባል በማለት በተደጋጋሚ ማስታወሳቸው ይታወሳል። ሁላችንም የመጨረሻ ቀን ፍርድ እንደ ሚጠብቀን በመጨረሻው ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመለአክቱ ጋር በዙፋኑ ላይ ቁጭ ብሎ በጎቹን ከፊየሎቹ በመለየት በማቴዎስ ወንጌል 25 እንደ ተጠቀሰው “ተርቤ አብልታችሁኛል፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፣ ታርዤ አልብሳችሁኛል፣ እንግዳ ሆኜ መጥቼ ተቀብላችሁኛል. . .” ወዘተ በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያቀርብልን ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ከአሁኑ መዘጋጀት ይኖርብናል በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን በመጨረሻው ሰዓተ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠን ፍርድ አሁን በሕይወት እያለን በምናከናውነው የምሕረት ወይም የበጎ አድራጎት ተግባር ላይ በተመሰረተ መልኩ በመሆኑ ከአሁኑ በጎ ተግባራርትን ማከናወን ይኖርብናል በማለት መናገራቸውም ይታወሳል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በእነዚህ 12 ዓመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዓመታቸው በቤተ ክርስቲያን የቀሳውስት ብቻ ሳትሆን መላው ምዕመን በተገቢው መልኩ ይሳተፍ ዘንድ መፍቀድ እንደ ሚገባ በተደጋጋሚ ማሳሰባቸው የሚታወቅ ሲሆን ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ሚና በሚገባ እንዲወጡ ማስቻል ያስፈልጋል፣ በማነኛውም የቤተ ክርስቲያን ውሳኔዎች ውስጥ ምዕመናን በትኩረት እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል የሚል ጽኑ አቋም እንዳላቸው ይታወቃል። በተለይም ደግሞ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጾ ስላላቸው ይህንን አዎንታዊ የሆነ ሚና እንዲጫወቱ መፍቀድ ያስፈልጋል በማለት በተደጋጋሚ የተናገሩት ቅዱስነታቸው በእዚህ ረገድ ማርያም ከኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት በላይ እንደ ነበረች በማንሳት ሴቶች ለቤተ ክርስቲያን ሊያበረክቱት የሚችሉትን ከፍተኛ አስተዋጾ ቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ መገለጻቸው ይታወሳል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በእነዚህ 12 ዓመታት የጵጵስናቸው ዓመታት ክርስቲያኖች ሁሉ ቅዱስ ወንጌልን በማብሰር ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጾ መጫወት እንደ ሚገባቸው በመገለጽ ክርስቲያኖች በመንፍስ ቅዱስ በመሞላት ቅዱስ ወንጌልን “በድፍረት፣ ጮክ ብሎ እና በማነኛውም ጊዜ እና ቦታ ለማወጅ መዘጋጀት ይገባቸዋል ማለታቸውም የሚታወስ ሲሆን “በተለይም ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በስቃይ ላይ የሚገኙትን ሰዎች ተጨባጭ በሆነ መልኩ በማገዝ፣ ተስፋ እንዳይቆርጡ በማድረግ ተስፋቸው እንዲለመልም የሚያደርጉ የምሕረት ተግባራትን ማከናወን ይገባል በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወቃል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ በሚከተሉ የዓለማችን አገራት በመዘዋወር ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን በማድረግ የሰላም እና የእርቅ ሐዋርያ መሆናቸውን አስመስክረዋል።
1. እ.አ.አ ከሐምሌ 22-29/2013 ዓ. ም. በብራዚል
2. እ.አ.አ. ከግንቦት 24-26/2016 ዓ. ም. በእስራኤል፣ ዮርዳኖስ እና በፍልስጤም
3. እ.አ.አ ከነሐሴ 14-18/2014 ዓ. ም. በደቡብ ኮሪያ
4. እ.አ.አ በመስከረም 21/2014 ዓ. ም. በአልባኒያ
5. እ.አ.አ በሕዳር 25/2014 በፈረንሳይ
6. እ.አ.አ ከሕዳር 28-30/2014 በቱርክ
7. እ.አ.አ ከጥር 13-19/2015 ዓ. ም. በስሪላንካ እና በፍሊጵንስ
8. እ.አ.አ በሰኔ 6/2015 ዓ. ም. በቦሲኒያ እና በኤርዜጎቪና
9. እ.አ.አ ከሐምሌ 5-13/2015 ዓ. ም. በቦሊቪያ፣ በኤኳዶር እና በፓራጓይ
10. እ.አ.አ ከመስከረም 19-27/2015 ዓ. ም. በኩባ እና በአሜሪካ
11. እ.አ.አ ከታሕሳስ 25-30/2015 ዓ. ም. በኬኒያ፣ በኡጋንዳ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ
12. እ.አ.አ ከየካቲት 12-18/2016 ዓ. ም. በሜክሲኮ
13. እ.አ.አ በሚያዝያ 16/2016 ዓ. ም. በግሪክ
14. እ.አ.አ ከሰኔ 24-26/2016 ዓ. ም. በአርሜኒያ
15. እ.አ.አ ከሐምሌ 27-31/2016 ዓ. ም. በፖላንድ
16. እ.አ.አ ከመስከረም 30-ጥቅምት 2/2016 ዓ. ም. በጆርጂያ እና አዘረበጃን
17. እ.አ.አ ከጥምቅት 31 እስከ ሕዳር 1/2016 ዓ. ም. በሲውዲን
18. እ.አ.አ ከሚያዝያ 28-29/2017 ዓ. ም. በግብፅ
19. እ.አ.አ ከግንቦት 12-13/2017 ዓ. ም. በፖርቱጋል
20. እ.አ.አ ከመስከረም 6-10/2017 ዓ. ም. በኮሎምቢያ
21. እ.አ.አ ከሕዳር 27- እስከ ታሕሳስ 2/2017 በማያንማር (በርማ) እና በባንግላዲሽ
22. እ.አ.አ ከጥር 15-21/2018 ዓ.ም በቺሊ እና በፔሩ
23. እ.አ.አ በሰኔ 21/2018 በሲውዘርላንድ
24. እ.አ.አ ከነሐሴ 25-26/2018 ዓ. ም. በአየርላንድ
25. እ.አ.አ ከመስከረም 22-25/2018 ዓ. ም. በስቶኒያ፣ በላቲቪያ እና በሊቷኒያ
26. እ.አ.አ ከጥር 23-27/2019 ዓ.ም በፓናማ
27. እ.አ.አ ከየካቲት 3-5/2019 ዓ. ም. የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች
28. እ.አ.አ ከመጋቢት 30-31/2019 በሞሮኮ
29. እ.አ.አ ከግንቦት 5-7/2019 ዓ. ም. በቡልጋሪያ እና ሰሜን መቀዶኒያ
30. እ.አ.አ ከግንቦት 31 እስከ ሰኔ 2/2019 ዓ. ም. በሮሜኒያ
31. እ.አ.አ ከመስከረም 4 -10/2019 ዓ. ም. በሞዛንቢክ፣ ማዳጋስካር እና በሞሪሼስ
32. እ.አ.አ ከሕዳር 19-26/2019 ዓ. ም. በታይላንድ እና በጃፓን
33. እ.አ.አ ከመጋቢት 5-8/2021 ዓ. ም. በኢራቅ
34. እ.አ.አ ከመስከረም 12-15/2021 ዓ. ም. በሀንጋሪ እና በስሎቫኪያ
35. እ.አ.አ ከታኅሳስ 2-6/2021 ዓ. ም. በቆጵሮስ እና በግሪክ
36. እ.አ.አ ከሚያዝያ 2-3/2022 ዓ.ም በማልታ
37. እ.አ.አ ከሐምሌ 24-30/2022 ዓ. ም. በካናዳ
38. እ.አ.አ ከመስከረም 13-15/2022 ዓ. ም. በካዛኪስታን
39. እ.አ.አ ከሕዳር 3-6/2022 ዓ. ም. በባሕሬን
40. እ.አ.አ ከጥር 31 እስከ የካቲት 5/2023 ዓ. ም. ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ እና በደቡብ ሱዳን።
41. እ.አ.አ ከሚያዝያ 28-302023 በሀንጋሪ
42. እ.አ.አ ከነሐሴ 2-6/2023 ዓ.ም በፖርቱጋል
43. እ.አ.አ ከነሐሴ 31 እስከ መስከረም 4-2023 ዓ.ም በሞንጎሊያ
44. እ.አ.አ ከመስከረም 22-23/2023 በፈረንሳይ
45. እ.አ.አ ከመስከረም 2-13/2024 በኢንዶኔዢያ፣ ፓፓዋ ጊኒ፣ ቲሞር-ሌስት፣ በሲንጋፖር በቅደም ተከተል
46. እ.አ.አ ከመስከረም 26-29/2024 በሉክሰንበርግ እና በቤልጂዬም
47. እ.አ.አ በሕዳር 15/2024 በፈረንሳይ።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእነዚህ 12 ዓመታት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ወቅት በአጠቃላይ 47 የሚሆኑ ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ከጣሊያን ውጪ ያከናወኑ ሲሆን በእነዚህ 44 በሚሆኑ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው 68 አገራትን በመጎብኘት የሰላም እና የእርቅ ሐዋርያ መሆናቸውን አስመስክረዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው የተመረጡበት 12ኛ አመት በመጋቢት 04/2017 ዓ.ም ታስቦ በሚውልበት በአሁኑ ወቅት ቅዱስነታቸው ይህንን እለት በሆስፒታል ውስጥ ሆነው ለማሳለፍ ተገደዋል። ይህንን መታሰቢያ በተመለከተ የቫቲካን ዜና የአርትኾት ክፍል ዋና ኃላፊ የሆኑት አቶ አድርያ ቶርኔሊ የሚከተለውን መልእክት አቅርበዋል።
ዘንድሮ፣ ለአንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኘው በጂሜሊ ሆስፒታል አስረኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የሆስፒታል ክፍላቸው ውስጥ ለቆዩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እዚያው ሆነው ጳጳስ የሆኑበትን 12ኛውን አመት ያከብራሉ። የቅርብ ጊዜዎቹ የሕክምና ውጤቶች የምያወጧቸው ዜናዎች አበረታች ናቸው፣ የእርሳቸው የጤና ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ በቅርቡ ወደ ቫቲካን ሊመለሱ እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን። አሁንም፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዚህ ወቅት እያጋጠሟቸው ያሉት ነገሮች ይህን የጵጵስና ሹመት የጀመሩበትን አመታዊ በዓል እጅግ ያልተለመደ ያደርገዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ እ.አ.አ የ2025 ዓ.ም ኢዮቤልዩ አመት ባርከው ያሰጀመሩ ሲሆን፣ በዚያውም የቅዱሱ በር አከፋፈት መንፈስዊ ሥነ-ስርዓት ማከናወናቸውም ይታወሳል። የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በበሽተኞች መካከል ታመው በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት እርሳቸው ራሳቸው በመከራ እየተሰቃዩ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት ስለ ሰላም ሲጸልዩ በብዙ የዓለም ማሕበረሰቦች ጸሎት ታጅበው ነው። በእነዚህ አሥራ ሁለት ዓመታት ውስጥ “እባካችሁ ለእኔ መጸለይ እንዳትዘነጉ” ከሚለው ተማጽኖዋቸው ባሻገር እራሳቸው የመሯቸውን እና ያከናወኗቸውን ስብሰባዎች፣ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን ወይም የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት የማያውቁ ሰዎች እንኳን ዛሬ ለእራሳቸው በጥልቅ የሚጨነቁ መዕመናን እና ኢማንያን ሳይቀሩ እርሳቸውን ያስታውሷቸዋል።
አሁን የቤተክርስቲያንን ተፈጥሮ እና የሮማ ኤጲስ ቆጶስ ተልእኮ የምናስብበት ጊዜ ነው፣ ይህም ከአንድ መድብለ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ በእጅጉ የተለየ ነው። ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት፣ በወቅቱ የነበሩት ካርዲናል ቤርጎሊዮ ለጠቅላላ ጉባኤዎች ንግግር አድርገዋል፣ የሄንሪ ዴ ሉባክን አስተያየት በመጥቀስ፣ ቤተ ክርስቲያን ልትደርስበት የምትችለው “ከፉ ክፋት” “መንፈሳዊ ዓለማዊነት” ነው፡- “የራሷ ብርሃን እንዳላት የምታምን ቤተ ክርስቲያን አደጋ፣ በራሷ ጥንካሬ፣ የራሷ ስልቶች፣ የራሷ ቅልጥፍና፣ እና “ከእንግዲህ ውጤታማ ለመሆን አትችልም” የሚሉ አስተሳሰቦች መሆናቸውን ገልጸው ነበር። የሌላውን ብርሃን በማንፀባረቅ ፣ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ባለው ጸጋ ብቻ መኖር እና መተግበር አልቀረም።
እነዚህን ቃላት በድጋሚ በማስታወስ፣ ዛሬ፣ በጂሜሊ ሆስፒታል አስረኛ ፎቅ መስኮቶች በፍቅር እና በተስፋ እንመለከታለን። ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አሁንም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመቁጠሪያ ጸሎት ወቅት በቅርብ ቀናት ውስጥ ለተቀላቀለው ለዚህ ደካማ ድምጽ እናመሰግናለን - ስለሰላም የሚማጻኑ እና ጦርነትን ሳይሆን ውይይትን ይደግፋሉ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልካም አመታዊ በዓል፣ ይሁንሎት! አሁንም ድምጾን መስማት በጣም እንፈልጋለን!