ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ እንደ ማርያም እና ኢየሱስ ጌታን በተስፋ እንፈልገው ማለታቸው ተገለጸ!
ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ እንደ ማርያም እና ኢየሱስ ጌታን በተስፋ እንፈልገው ማለታቸው ተገለጸ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት ለምዕመናን በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተንተርሰው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደምያደርጉ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ቅዱስነታቸው በደረሰባቸው የጤና እክል ምክንያት በሆስፒታል ውስጥ እንደ ሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ቀደም ሲል ሆስፒታል ከመግባታቸው በፊት ያዘጋጁትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በየካቲት 26/2017 ዓ.ም የቫቲካን የፕሬስ ጽ/ቤት ይፋ ያደረገ ሲሆን በዚህ መሰረት በወቅቱ ጽ/ቤቱ ያፋ ባደርገው የቅዱስነታቸው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሁን የምንገኝበትን የኢዩቤሊዩ አመት ምክንያት በማድረግ ከዚህ ቀደም "ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን ነው፣ የኢየሱስ የልጅነት ጊዜ" በሚል ዐብይ አርእስት ጀምረው ከነበረው አስተምህሮ በመቀጠል " “ልጄ ሆይ! ለምን እንዲህ አደረግህብን?" (ሉቃስ 2፡49) በሚል ንዑስ አርእስት ዙሪያ ሕጻኑ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ መገኘቱን በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተመርኩዘው ይፋ ባደረጉት የክፍል ስምንት አስተምህሮ እንደ ማርያም እና ኢየሱስ ጌታን በተስፋ እንፈልገው ማለታቸው ተገልጿል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በእለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል
ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ እየሰማቸውና እየጠየቃቸው በመቅደስ አገኙት (...) ባዩትም ጊዜ እጅግ ተገረሙ፤ እናቱም፦ “ልጄ ሆይ! ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር እኮ፤” አለችው። እርሱም፦ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም (ሉቃስ 2፡46. 48-50)።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
በኢየሱስ የልጅነት ሁኔታ ዙሪያ ላይ በተዘጋጀው በዚህ የመጨረሻ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ኢየሱስ በአስራ ሁለት አመቱ፣ ለወላጆቹ ሳይናገር በቤተ መቅድስ ክፍል ውስጥ በቆየበት ጊዜ ቤተሰቦቹ እርሱን በጉጉት እየፈለጉት እና ከሶስት ቀን በኋላ ስላገኙት ሁኔታ ዛሬ መመልከት እንጀምራለን። ይህ ታሪክ በማርያምና በኢየሱስ መካከል የተደረገውን በጣም አስደሳች ውይይት ያቀርብልናል፤ ይህም የኢየሱስ እናት በነበረችበት መንገድ ላይ እንድናሰላስል ይረዳናል፤ ይህ ጉዞ ቀላል አልነበረም። በእርግጥም ማርያም የልጇን ምሥጢር በመረዳት የገፋችበትን መንፈሳዊ የጉዞ መስመር ዘረጋች።
የዚህን ጉዞ የተለያዩ ደረጃዎች መለስ ብለን እንመልከት። በእርግዝናዋ መጀመሪያ ላይ ማርያም ኤልሳቤጥን ጎበኘች እና ትንሹ ዮሐንስ እስኪወለድ ድረስ ለሦስት ወራት ያህል ከእሷ ጋር ቆየች። ከዚያም በዘጠነኛው ወር እርግዝናዋ ላይ ሆና በሕዝብ ቆጠራው ምክንያት ከዮሴፍ ጋር ወደ ቤተልሔም ሄደች ኢየሱስንም ወለደች። ከአርባ ቀን በኋላ ሕፃኑን ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፣ እና ከዚያ በኋላ በየዓመቱ ወደ ቤተመቅደስ በመሄድ መንፈሳዊ ንግደት አድርገው ይመለሳሉ። ነገር ግን ገና ሕፃን እያለ ኢየሱስን ከሄሮድስ ለመከላከል ለረጅም ጊዜ በግብፅ ተጠልለው ቆይተው ንጉሱ ከሞተ በኋላ ናዝሬት እንደገና መኖር ጀመሩ። ኢየሱስ ጎልማሳ ሲሆን አገልግሎቱን ሲጀምር ማርያም በቃና ሰርግ ላይ ዋና ተዋናይ ነበረች፣ ከዚያም “በሩቁ” ተከተለችው፣ ወደ እየሩሳሌም የመጨረሻ ጉዞው ድረስ፣ እና እስከ ሕማማቱ እና ሞቱ ድረስ። ከትንሣኤ በኋላ፣ ማርያም የመንፈስ ቅዱስን መፍሰስ በመጠባበቅ ላይ ሳለች፣ የደቀ መዛሙርት እናት እንደመሆኗ መጠን በኢየሩሳሌም ቆየች።
በዚህ ጉዞ ውስጥ፣ ድንግል የተስፋ ተጓዥ ነች፣ በጠንካራ አስተሳሰብ የደቀመዛሙርቱ የመጀመሪያዋ “የልጇ እናት” ሆናለች። ማርያም የሰው ልጅ ተስፋ የሆነውን ኢየሱስን ወደ ዓለም አመጣች፣ ራሷን በእግዚአብሔር ቃል ለመቀረጽ ቀዳሚ በመሆን አሳደገችው፣ ተከተለችው። ቤኔዲክት 16ኛ እንደተናገሩት፣ “ማርያም በቤት ውስጥ ምን ያህል ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር እንዳለች እናያለን… ሀሳቧ እንዴት ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር እንደተስማማ፣ ፈቃዷ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር አንድ እንደሆነ እናያለን። ማርያም ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ቃል ስለተሞላች፣ የሥጋ ለባሽ የቃል እናት ልትሆን ትችላለች” (ጳጳሳዊ መልእክት ዴውስ ካሪታስ ኤስት ቁ. 41)። ይህ ልዩ የሆነ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር መገናኘቷ ከሚያስፈልገው “ልምምድ” ጥረት አያድናትም።
የአሥራ ሁለት ዓመቱ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በሚደረገው ዓመታዊ መንፈሳዊ ንግደት ጉዞ ወቅት የጠፋበት ሁኔታ ማርያምን ያስፈራት ከመሆኑም ሌላ ጠፍቶ የተገኘውን ልጃቸውን ይዘው ሲመለሱ ስለ ዮሴፍ ተናግራለች:- “ልጄ ሆይ፣ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እኔና አባትህ በታላቅ ጭንቀት ስንፈልግህ ነበርን” (ሉቃስ 2፡48) ማርያም እና ዮሴፍ የጎደለ ልጅ ያላቸው ወላጆች ስቃይ ተሰምቷቸው ነበር፡ ሁለቱም ኢየሱስ ከዘመዶቻቸው ጋር አብሮ እየተጓዘ እንዳለ አስበው ነበር፣ ነገር ግን አንድ ቀን ሙሉ እሱን ሳያዩት ከሄዱ በኋላ አካሄዳቸውን ወደ ኋላ ለመመለስ የሚያበቃውን ፍለጋ ጀመሩ። ወደ ቤተ መቅደሱ ሲመለሱ፣ በዓይናቸው፣ ከጥቂት ጊዜ በፊት፣ ገና ሕፃን ሆኖ የነበረ አሁን ግን በድንገት ያደገ ይመስላል፣ አሁን በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ውይይት ለማድረግ፣ ከሕግ አስተማሪዎች ጋር ራሱን ያስቀምጣል።
ኢየሱስ የእናቱ ተግሣጽ ሲገጥመው ትጥቅ በሚያስፈታ ቀላል መንገድ መለሰ፡- “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አታውቁምን? (ሉቃስ 2:49) ማርያም እና ዮሴፍ አላስተዋሉም፥ የእግዚአብሔር ምስጢር ከአእምሮአቸው በላይ ሆነ። ወላጆቹ ያንን ውድ ልጅ በፍቅራቸው ክንፍ ሥር ለመጠበቅ ይፈልጋሉ፣ ይልቁኑ፣ ኢየሱስ በአገልግሎቱ ውስጥ እንዳለ እና በቃሉ ውስጥ ሰምጦ የሚኖር የአብ ልጅ ሆኖ ጥሪውን መኖር ይፈልጋል።
የሉቃስ ወንጌል ስለኢየሱስ የልጅነት ጊዜ ያደረጋቸው ትረካዎች ስለዚህ የዮሴፍን አባትነት ለኢየሱስ ያለውን አባትነት በሚያስታውሱት የማርያም የመጨረሻ ቃላቶች እና በኢየሱስ የመጀመሪያ ቃላቶች ይህ አባትነት ከሰማያዊ አባቱ የመነጨ መሆኑን ይገነዘባል፣ የማይከራከርም የበላይነቱን አምኗል።
ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ እንደ ማርያም እና ዮሴፍ፣ በተስፋ የተሞላ፣ እራሳችንን በፍላጎታችን ውስጥ ብቻ ገድበን እንድንኖር የማይፈቅደው እና እራሱን በአንድ ቦታ ላይ ብዙም እንዲገኝ የማይፈቅደውን የጌታን ፈለግ እንከተል፣ ነገር ግን በፍቅር ርህራሄ ለሆነው መለኮታዊ አባትነት ምላሽ፣ የፍቅር ምላሽ የልጅነት ህይወት ነው።