ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ የተበላሸ ታሪካችንን በእግዚአብሔር እግር ሥር ልናኖረው የገባል አሉ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት ለምዕመናን በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተንተርሰው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደምያደርጉ ይታወቃል። ቅዱስነታቸው በደረሰባቸው የጤና እክል ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ከተሰጣቸው በኋላ በአሁኑ ወቅት በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ ቤት ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ከሕመማቸው እያገገሙ መሆናቸው ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ቀደም ሲል ከመታመማቸው በፊት ያዘጋጁትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የቫቲካን የፕሬስ ጽ/ቤት በመጋቢት 17/2017 ዓ.ም ይፋ አድርጓል። በዚህ መሰረት በወቅቱ ጽ/ቤቱ ያፋ ባደርገው የቅዱስነታቸው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሁን የምንገኝበትን የኢዩቤሊዩ አመት ምክንያት በማድረግ ከዚህ ቀደም "ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን ነው፣ የኢየሱስ ሕይወት እና ያደረጋቸው ግንኙነቶች" በሚል ዐብይ አርእስት ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ በመቀጠል “ውሃ አጠጪኝ” (ዮሐ 4፡7) በሚል ንዑስ አርእስት ዙሪያ ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር የተገናኘበትን ሁኔታ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተመርኩዘው ይፋ ባደረጉት የክፍል ሁለት አስተምህሮ የተበላሸ የሚመስለውን ታሪካችንን በእግዚአብሔር እግር ሥር ልናኖረው የጋባል ማለታቸው ተገልጿል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች የቫቲካን የፕሬስ ጽ/ቤት በወቅቱ ይፋ ያደርገውን የቅዱስነታቸውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!
ኢየሱስን ለመፈለግ ሄዶ ከነበረው ከኒቆዲሞስ ጋር ኢየሱስ ባደረገው ግንኙነት ላይ ካሰላሰልን በኋላ፣ ዛሬ በዚያ የሕይወታችን መስቀለኛ መንገድ ላይ እሱ እየጠበቀን ያለን በሚመስል በእነዚህ ጊዜያት ላይ እናሰላስላለን። እነዚህ የሚያስደንቁ ግንኙነቶች ናቸው፣ እናም መጀመሪያ ላይ ምናልባት ትንሽ እንጠነቀቃለን፡ ጠንቃቃ ለመሆን እና እየሆነ ያለውን ነገር ለመረዳት እንሞክራለን።
ይህ ምናልባት በዮሐንስ ወንጌል አራተኛ ምዕራፍ ላይ የተገለጸው የሳምራዊቷ ሴት ልምድ ነበር (4፡5-26 ይመልከቱ)። እሷ እኩለ ቀን ላይ የውሃ ጉድጓድ በሚገኝበት አከባቢ ላይ አንድ ሰው ይገኛል ብላ አልጠበቀችም ነበር፣ እንደውም ማንንም እንደማታገኝ ተስፋ አድርጋ ነበር። እንዲያውም ከጉድጓድ ውኃ ለመቀዳት የሄደችበት ጊዜ ከወትሮው በተለየ ጊዜ በጣም ሞቃት በነበረ ጊዜ ነበር። ምናልባት ይህች ሴት በህይወቷ ታፍራለች፣ ምናልባት እንደተፈረደባት፣ እንደተወገዘች፣ ሰው እንደማይረዳት ሆኖ ተሰምቷት ሊሆን ይችላል፣ እናም በዚህ ምክንያት እራሷን አገለለች፣ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ከሁሉም ሰው ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠች።
ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ ለመሄድ ሌላ መንገድ መምረጥ ይችል ነበር፣ የግድ በሰማርያ ማለፍ አልነበረበትም።በአይሁዶችና በሳምራውያን መካከል ካለው ውጥረት አንፃር የበለጠ አስተማማኝ ይሆን ነበር። ነገር ግን በእዚያ ማለፍ ፈለገ፣ በዚያ በትክክል በዚያ ጊዜ እዚያ ሥፍራ ይቆማል! ኢየሱስ ይጠብቀናል እናም ለእኛ ምንም ተስፋ እንደሌለን ስናስብ እርሱ ራሱን ለእኛ ያቀርባል። በጥንቷ መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ያለው የውሃ ጉድጓዱ የመሰባሰቢያ ቦታ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ጋብቻዎች የሚደራጁበት፣ የመተጫጫ ቦታ ነው። ይህች ሴት ለመወደድ ትፈልጋለች፣ ኢየሱስ ደግሞ ይህች ሴት ለምትፈልገው ነገር እውነተኛ መልስ የት እንደምታገኝ እንድትገነዘብ ሊረዳት ይፈልጋል።
ይህንን ገጠመኝ ለመረዳት የፍላጎት ጭብጥ መሠረታዊ ነው። ኢየሱስ በመጀመሪያ ፍላጎቱን የገለፀው "ውሃ አጠጭኝ!" (ዩሐ. 4፡10) በሚለው ቃል ነበር። ንግግሩን ለመክፈት ኢየሱስ ራሱን ደካማ አድርጎ በመመልከት እና በማቅረብ ሌላውን ሰው እንዲረጋጋ በማድረግ ፍርሃት እንዳይሰማቸው ያደርጋል። ጥማት ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንኳን የፍላጎት ምስል ነው። እዚህ ግን ኢየሱስ ከሁሉ በፊት የተጠማው ለዚያች ሴት መዳን ነው። ቅዱስ አውግስጢኖስ ኢየሱስ “በዚህች ሴት እምነት ተጠምቷል” ሲል ሁኔታውን ገልጾታል።
ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ሄዶ የነበረ ሲሆን ቢሆንም እዚህ ላይ የምናገኘው ታሪክ ደግሞ ኢየሱስ ሳምራዊቷን ሴት ያገኛት እኩለ ቀን ላይ ማለትም ብርሃን ባለበት ጊዜ ነው። በእርግጥም የመገለጥ ጊዜ ነው። ኢየሱስ ራሱን መሲሕ እንደሆነ ያሳወቀች ከመሆኑም ሌላ በሕይወቷ ላይ ብርሃን ፈንጥቋል። ታሪኳን በአዲስ መንገድ እንደገና እንድታነብ ይረዳታል፣ ይህም የተወሳሰበ እና የሚያም ታሪክ ነበር፣ አምስት ባሎች ነበሯት እና አሁን ባሏ ካልሆነ ስድስተኛ ሰው ጋር ትገኛለች። ስድስት የሚለው ቁጥር በዘፈቀደ የመጣ አይደለም፣ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ የአንድ ነገር አለመፈጸምን ያመለክታል። ምናልባትም ይህች ሴት በእውነት ለመወደድ ያላትን ፍላጎት ማርካት ለሚችለው ለሰባተኛው ባል ፍንጭ ሊሆን ይችላል። እና ያ ሙሽራ ኢየሱስ ብቻ ሊሆን ይችላል።
ኢየሱስ ሕይወቷን እንደሚያውቅ ስትገነዘብ ሴቲቱ ንግግሯን አይሁዳውያንንና ሳምራውያንን ወደ ከፋፈለው ሃይማኖታዊ ጉዳይ ለወጠች። በምንጸልይበት ጊዜ ይህ በእኛ ላይም ይከሰታል፣ እግዚአብሔር ሕይወታችንን እና ችግሮቻችንን በሚነካበት በዚህ ጊዜ፣ አንዳንድ ጊዜ የተሳካ ጸሎት በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ገብተን ጭልጥ ብለን በሐሳቦቻችን ውስጥ ገብተን እንጠፋለን። እንደውም የመከላከያ አጥሮችን አልፈን እንሄዳለን። ጌታ ግን ሁል ጊዜ ታላቅ ነው፣ ለዚያች ሳምራዊት ሴት ከባሕል አንጻር ከተመለከትነው እንኳን ሊነገራት በማይገባት ሴት ላይ ከፍተኛውን መገለጥ ይሰጣታል፣ እሱም በመንፈስ እና በእውነት ሊመለክ የሚገባውን አብን ይነግራታል። እርስዋም በድጋሚ በመገረም እነዚህን ነገሮች በሚገባ ለመረዳት ይቻል ዘንድ መሲሑን መጠበቅ የተሻለ እንደሆነ ስታስተውል፡- ኢየሱስ “የማናግርሽ እኔ እርሱ ነኝ" (ዩሐ 4፡26) አላት። ልክ እንደ ፍቅር መግለጫ ነው፡ የምትጠብቂው ሰው እኔ ነኝ፣ በመጨረሻ የመወደድ ፍላጎቷንም ሊመልስ የሚችል እርሱ መሆኑን ያረጋግጣል።
በዚያን ጊዜ ሴትየዋ የመንደሩን ሰዎች ለመጥራት ትሮጣለች፣ ምክንያቱም ተልዕኮው የሚነሳው በትክክል የመወደድ ስሜት ስላለው ነው። እናም የመረዳት፣ የመቀበል፣ የይቅርታ ልምዷ ካልሆነ በስተቀር ምን መልእክት ልታመጣ ትችላለች? አዳዲስ መንገዶችን ለመስበክ በምናደርገው ፍለጋ ላይ እንድናሰላስል የሚያደርግ ምስል ነው።
ልክ እንደፍቅር ሰው ሳምራዊቷ ሴት በኢየሱስ እግር ስር ያለውን እንስራ ትረሳዋለች። በጭንቅላቷ ላይ የነበረው የዚያ እንስራ ክብደት፣ ወደ ቤቷ በተመለሰች ቁጥር፣ ያለችበትን ሁኔታ፣ የመከራ ህይወቷን ያስታውሳታል። አሁን ግን ያ እንስራ በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጧል። ያለፈው ጊዜ ሸክም አሁን የለም፣ ታርቃለች። ለኛም እንዲሁ ነው፤ ወንጌልን ለመስበክ መጀመሪያ የታሪካችንን ክብደት በጌታ እግር ሥር ልናስቀምጠው፣ ያለፈውን ሸክም ለእርሱ አሳልፈን መስጠት አለብን። የታረቁ ሰዎች ብቻ ናቸው ወንጌልን መስበክ የሚችሉት።
ውድ ወንድሞች እና እህቶች ተስፋ አንቆርጥም! ታሪካችን ከባድ፣ የተወሳሰበ፣ ምናልባትም የተበላሸ ቢመስልም ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር አሳልፈን ልንሰጥ እና ጉዞአችንን እንደገና ለመጀመር እድሉ አለን። እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ሁልጊዜ ይጠብቀናል!