MAP

በሮም ከተማ የሚገኘው የጂሜሊ ሆስፒታል በሮም ከተማ የሚገኘው የጂሜሊ ሆስፒታል  

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጤና ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለጸ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ የካቲት 19/2017 ዓ.ም ምሽቱን በመልካም ሁኔታ ማሳለፋቸው የተገለጸ ሲሆን የጤና ሁኔታቸው ለባለፉት ሁለት ቀናት መሻሻል እያሳየ መምጣቱ ተዘግቧል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምሽቱን በጥሩ ሁኔታ እንዳሳለፉ እና የጠዋቱን የመጀመሪያ ክፍል በማረፍ እያሳለፉ እንደ ሆነ የቅድስት መንበር የዜና ማሰራጫ ክፍል ሐሙስ የካቲት 20/2017 ዓ.ም በወጣው መግለጫ ገልጿል።

“ጳጳሱ በሌሊት ጥሩ እንቅልፍ ተኝተው ነበር እና አሁን እያረፉ ነው” ሲል አጭር መግለጫ አስነብቧል።

እሮብ ምሽት ላይ የፕሬስ ጽህፈት ቤቱ የጳጳሱ የጤና ሁኔታ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በትንሹ መሻሻል አሳይቷል ብሏል።

“በቅርብ ቀናት ውስጥ የሚታየው ቀላል የኩላሊት የጤና እክል አሁን ጋብ ብሏል። “[ማክሰኞ] ምሽት የተደረገው የደረት ሲቲ ስካን የሳንባ እብጠት መደበኛ እድገት አሳይቷል። [ረቡዕ] የተደረገው የደም ምርመራዎች [ማክሰኞ] የታየውን መሻሻል አረጋግጠዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በከፍተኛ ሁኔታ የኦክስጅን ህክምና ላይ ይገኛሉ፣ ነገር ግን እስከ እሮብ ምሽት ድረስ እንደ አስም አይነት የመተንፈሻ ቀውሶች አላጋጠሙዋቸውም።

የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽ/ቤት እንደገለጸው፣ የእርሳቸው የጤና ሁኔታ ትንበያ እንደምያሳየው ቅዱስነታቸው አሁንም ለተወሰኑ ቀናት በሆስፒታል እንደሚቆዩ ያሳያል።  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የብሮንካይተስ በሽታን ተከትሎ አርብ የካቲት 07/2017 ዓ.ም በሮም ከተማ በሚገኘው የጂሜሊ ሆስፒታል ገብተው የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን በመተንፈሻ አካላቸው ላይ በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት አሁንም ለባለፉት 13 ቀናት ያህል የሕክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደ ሚገኝ ይታወቃል።

27 Feb 2025, 11:20