ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ የተስፋ መንፈሳዊ ተጓዢ አብነት የሆኑትን ስምዖን እና ሀናን ምሳሌ እንከተል አሉ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት ለምዕመናን በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተንተርሰው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደምያደርጉ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ቅዱስነታቸው በደረሰባቸው የጤና እክል ምክንያት በሆስፒታል ውስጥ እንደ ሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ቀደም ሲል ሆስፒታል ከመግባታቸው በፊት ያዘጋጁትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በየካቲት 19/2017 ዓ.ም ቫቲካን ይፋ ያደረግች ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሁን የምንገኝበትን የኢዩቤሊዩ አመት ምክንያት በማድረግ ከዚህ ቀደም "ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን ነው፣ የኢየሱስ የልጅነት ጊዜ" በሚል ዐብይ አርእስት ጀምረው ከነበረው አስተምህሮ በመቀጠል "ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና" (ሉቃስ 2፡30) በሚል ንዑስ አርእስት ዙሪያ ላይ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ የተወሰደበትን ሁኔታ በሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተመርኩዘው ባደረጉት የክፍል ሰባት አስተምህሮ የተስፋ መንፈሳዊ ተጓዢ አብነት የሆኑትን ስምዖን እና ሀናን ምሳሌ እንከተል ማለታቸው ተገልጿል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በእለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል
"ስምዖን በመንፈስም ተነሣስቶ ወደ መቅደስ መጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ሊያደርጉለት ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው፤ እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ! አሁን እንደ ቃልህ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ" (ሉቃስ 2፡27-29)።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
ዛሬ ስለ “ተስፋችን ኢየሱስ ክርስቶስ” (1ኛ ጢሞ 1፡1) በቤተመቅደስ ውስጥ በቀረበበት ወቅት ስለነበረው ምሥጢር ውበት እናሰላስላለን።
በኢየሱስ የልጅነት ታሪክ ውስጥ፣ ወንጌላዊው ሉቃስ ማርያምን እና ዮሴፍን ለጌታ ህግ ታዛዦች መሆናቸውን ያሳየናል። እንደ እውነቱ ከሆነ በእስራኤል ውስጥ ሕፃኑን በቤተ መቅደሱ የማቅረብ ግዴታ አልነበረበትም፤ ነገር ግን የሕጉን ቃል በመስማት የሚኖሩና ሕጉን ለመከተል የሚፈልጉ ሰዎች ሕጉን እንደ ጠቃሚ ልማድ ይመለከቱት ነበር። መካን የነበረችው የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐናም እንዲሁ አደረገች። እግዚአብሔር ጸሎቷን ሰምቶ ልጇን ወልዳ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደችውና ለእግዚአብሔር ለዘላለም አቀረበችው (1ሳሙ 1፡24-28)።
ስለዚህ ሉቃስ በቅድስት ከተማ በኢየሩሳሌም የተከበረውን የኢየሱስን የመጀመሪያ የአምልኮ ተግባር ይተርካል፣ እሱም ወደዚያ ለመውጣት ፅኑ ውሳኔ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ የሙሉ ተጓዥ አገልግሎቱ መድረሻ ይሆናል (ሉቃ. 9፡51)፣ ወደ ተልእኮው ፍፃሜ ሲያመራ የምያሳይ ምስል ጭምር ነው።
ማርያም እና ዮሴፍ ኢየሱስን በቤተሰብ፣ በህዝቡ፣ ከጌታ አምላክ ጋር ባለው የቃል ኪዳን ታሪክ ውስጥ ብቻ አላካተቱም። እድገቱን ይንከባከባሉ፣ እና ወደ እምነት እና የአምልኮ አየር ውስጥ ያስተዋውቁታል። እናም እነሱም ቀስ በቀስ ከእነሱ የሚበልጥ ጥሪ በመረዳት ያድጋሉ።
በቤተመቅደስ ውስጥ "የጸሎት ቤት" (ሉቃስ 19: 46) የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ለአንድ አረጋዊ ሰው ልብ ተናግሯል፣ ይህም ሰው ስምዖን የሚባል ሲሆን የእግዚአብሔር ቅዱሳን ሕዝብ አባል በመጠባበቅ እና ተስፋ ማድረግ የተማረ፣ እርሱም በነቢያት በኩል ለእስራኤል የገባው የተስፋ ቃል እንዲፈጸም ያለውን ፍላጎት ያሳድጋል። ስምዖን በቤተ መቅደሱ ውስጥ የተቀባው ጌታ መገኘትን ተረድቷል፣ በሕዝቦች መካከል የሚበራውን ብርሃን “በጨለማ” ውስጥ ተከስቶ አየ (ኢሳ. 9፡1) እና ኢሳይያስ እንደተነበየው “ለእኛ ተወልዶልናልና”፣ “ለእኛ የተሰጠን ልጅ"፣ “የሰላም ልዑል" (ኢሳያስ 9፡5) የተባለውን ልጅ ሊገናኘው ሄደ። ስምዖን ያንን ሕፃን ትንሽ እና አቅመ ቢስ የሆነውን ሕጻን፣ በእቅፉ ውስጥ ያረፈው ሕጻን፣ ነገር ግን እሱ ነው፣ በእውነቱ እርሱን ወደ እራሱ በመያዝ ማጽናኛ እና የህልውናውን ሙላት የሚያገኘው በእዚህ ሕጻን አማካይነት ብቻ ነው። ይህንንም በቤተክርስቲያን ውስጥ በቀኑ መጨረሻ ጸሎት በሆነው ልባዊ ምሥጋና በተሞላ ቃና ገልጿል።
"ጌታ ሆይ! አሁን እንደ ቃልህ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና፤ እርሱም በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን፥ ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው” (ሉቃስ 2፡29-32) በማለት ጸልዩዋል።
የእምነት፣ የተስፋ እና የፍቅር ምስክር
ስምዖን እርሱን ያዩት፣ እርሱን የሚያውቁ እና ከእስራኤል አዳኝ እና ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ለሌሎች ለማስተላለፍ የቻሉትን ሰዎች ደስታ ይዘምራል። እርሱ እንደ ስጦታ የተቀበለው እና ለሌሎች የተነገረው የእምነት ምስክር ነው፣ እርሱ የማያሳዝን የተስፋ ምስክር ነው፣ የሰውን ልብ በደስታና በሰላም የሚሞላ የእግዚአብሔር ፍቅር ምስክር ነው። በዚህ መንፈሳዊ መጽናኛ የተሞላው አረጋዊው ስምዖን ሞትን እንደ ፍጻሜ ሳይሆን እንደ ፍጻሜ ሙላት ያየዋል፣ እንደ “እህት” እየጠበቀው እንደማይጠፋ ነገር ግን አስቀድሞ የቀመሰውን እና ያመነበትን እውነተኛ ሕይወት ያስተዋውቃል።
ተስፋ በልባችን ውስጥ እንደገና ፈነጠቀ
በዚያ ቀን፣ በሕፃኑ በኢየሱስ መዳን ሥጋ ሆኖ ያየ ስምዖን ብቻ አይደለም። ከሰማንያ ዓመት በላይ የሆናት፣ መበለት የሆነች፣ ለቤተመቅደስ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ያደረች እና ለጸሎት የተቀደሰች አና ላይም ተመሳሳይ ነገር ደረሰ። በእርግጥ፣ ሕፃኑን ባየች ጊዜ፣ በዚያ ሕፃን ውስጥ ሕዝቡን የዋጀውን የእስራኤልን አምላክ ታከብራለች፣ እና ለሌሎች ስለ እሱ በመናገር የትንቢቱን ቃል በልግስና አሰራጭታለች። የሁለት አረጋዊያን የቤዛነት መዝሙር ለሰዎች እና ለአለም ሁሉ የኢዮቤልዩ አዋጅን ያወጣል። ተስፋችን ክርስቶስ ስለገባባት በኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ውስጥ በልቦች ውስጥ ፈንጥቋል።
በተስፋ የተሞላ መንፈሳዊ ነጋዲያን
ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ እኛም ከመልክ ባሻገር ማየት የሚችሉ ጥርት ያለ ዓይን ያላቸው፣ የእግዚአብሔርን ህልውና በጥቂቱ ለይተው የሚያውቁ፣ የእግዚአብሔርን ጉብኝት በደስታ እንዴት እንደሚቀበሉ እና በወንድሞችና እህቶች ልብ ውስጥ ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያውቁ፣ እነዚን ስምዖንና አናን እንምሰል።