የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጤና ሁኔታ መሻሻል እየታየበት መሆኑ ተገለጸ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሳንባ ምች ሕመም መጠቃታቸውን ተከትሎ በሮም ከተማ በሚገኘው ጂሜሊ ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ይታወቃል። ቅዱስነታቸው ወደ ሆስፒታል ከገቡ አሥራ አምስት ቀናት ያህል የሆናቸው ሲሆን የጤና ሁኔታቸው ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ እንደሚገኝ የቅድስት መንበር የኅትመት ክፍል አርብ ማለዳ የካቲት 21/2017 አስታውቋል።
የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሳምባ ምች በሮም ጂሜሊ ሆስፒታል ሲታከሙ፣ ‹‹እንደ ቅርብ ቀናት፣ ሌሊቱ በተረጋጋ ሁኔታ አሳልፈዋል፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱም አሁን ጥሩ እረፍት እያደርጉ ይገኛሉ። ቅዱስ አባታችን ዛሬ ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ቁርስ በልተው ጋዜጦችን አንብበዋል። ህክምናቸውን እና የትንፋሽ ፊዚዮቴራፒ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል" ሲል የቅድስት መንበር የኅትመት ክፍል አርብ ማለዳ የካቲት 21/2017 አስታውቋል።
ቫቲካን በዕለተ አርብ እንዳስታወቀችው ብፁዕ ካርዲናል አንጀሎ ደ ዶናቲስ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጪው ረቡዕ ሚያዝያ 05/2025 ዓ.ም የሚጀምረውን የዐብይ ጾም የአመድ መቀባት ሥነ-ሥርዓት ሥርዓተ አምልኮ እንደ ሚመሩም ተገልጿል።
28 Feb 2025, 15:27