MAP

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ባቀረቡበት ወቅት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ባቀረቡበት ወቅት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በጋዛ የቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና ምእመናንን በስልክ ጥሪ ማነጋገራቸውን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ በጋዛ ለሚገኝ የቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና የስልክ ጥሪ ማድረጋቸውን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ለመከታተል ለመጡት ምዕመናን ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በጦርነት የሚማቅቁ አገራትን በተለይም በዩክሬን የሚገኙ አረጋውያንን ምእመናኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በየዕለቱ እንደሚያደርጉት ሁሉ ማክሰኞ ጥር 13/2017 ዓ. ም. በጋዛ የቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና ባደረጉበት የስልክ ጥሪ፣ ነዋሪዎቹ ደስተኞች እንደ ሆኑ ገልጸዋል። ጋዛ ውስጥ በሚገኝ የቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና እና በዛው በሚገኝ ካቶሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ ወደ 600 የሚደርሱ ሰዎች ተጠልለውበት እንደሚገኙ ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሳምንታዊው የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አቸው ላይ ለተገኙ ታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር፥ አርጀንቲናዊው ተወላጅ አባ ገብርኤል ሮማኔሊ እና ረዳታቸው ግብጻዊ ተወላጅ አባ ዩሱፍ አሳድ ለሚመሩት የጋዛ ቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና ምእመናን የስልክ ጥሪ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለ15 ወራት እልቂት፣ ሁከት፣ ፍርሃት እና ረሃብ ካስጨነቀው የጋዛ ቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና መሪ ከሆኑት አባ ሮማኔሊ ጋር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የአስታውሰው፥ ካለፈው እሁድ ጀምሮ ተግባር ላይ በዋለው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ምእመናን ወደ መደበኛ ኑሮአቸው በመመለሳቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ጋዛ ውስጥ የሚገኝ የቅዱስ ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያን መሪ ቆሞስ አባ ሮማኔሊ፥ ተኩሱ ከቆመበት ከመጀመሪያዎቹ ሰዓታት ጀምሮ ሕይወት ቀስ በቀስ ወደ መደበኛነት እንደሚመለስ ገልጸው፥ ይህም የሰላም እርምጃ ውጤት መሆኑን በማስረዳት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለምዕመናኑ ያላቸውን ቅርበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ወዲህ በየዕለት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ከምእመናኑ ጋር በጸሎት ሲተባበሩ መቆየታቸው ሲታወስ፥ ባራኬን በመስጠት በጋዛ ቁምስና ውስጥ ተጠልሎ ስለሚገኝ እያንዳንዱ ሰው ይጠይቁ ቆይተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ረቡዕ ጥር 14/2017 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ምእመናን ለጋዛ፣ ለዩክሬን፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለማያንማር እንዲጸልዩ ጥሪያቸውን ከማቅረባቸው በተጨማሪ በሌሎች በርካታ የዓለማችን ክፍሎች ሰላም እንዲሰፍን መጸለይ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።

ጦርነት ዘወትር ሽንፈት መሆኑን ደጋግመው የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ምዕመናን ለሰላም እንዲጸልዩ በማሳሰብ፣ ከጦርነት የሚጠቀመው ሌላ ሳይሆን የጦር መሣሪያ አምራቾች ብቻ መሆናቸውን አስረድተው፥ በጦርነት አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዩክሬን አረጋውያንንም በጸሎታችሁ አስታውሰዋል።

 

22 Jan 2025, 16:33