ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በሰደድ እሳት የተጎዱ የሎስ አንጀለስ ነዋሪያዎችን ማስታወሳቸውን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ በተነሳው አስከፊ የሰደድ እሳት አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች በመጸሎት ማስታወስ እንደሚገባ አሳስበው፥ ልባቸውም በአደጋ ከተጎዳው የሎስ አንጀለስ ነዋሪዎች ጋር መሆኑን ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሳምንታዊ አስተምህሮአቸው ማጠቃለያ ላይ ለታዳሚው ባቀረቡት ጥሪ፥ መላውን ሠፈሮች እና ማኅበረሰቦችን ባወደመ እሳት ነዋሪውን ብዙ መከራ እንደደረሰበት በማስታወስ፥ ምዕመናኑ የጸሎት ዕርዳታ እንዲያደርጉ አደራ ብለው፥ የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድታማልድላቸው በማለት ጸሎት አቅርበዋል።
ያለፉት ጥሪዎች
የሰደድ እሳቱ ከፍተኛ ውድመት ካደረሰበት እና የሰው ሕይወት ከጠፋበት ጊዜ ጀምሮ ቅዱስነታቸው የሎስ አንጀለስን ሕዝብ በተደጋጋሚ ማስታወሳቸው ሲታወቅ፥ ያለፈው እሁድ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካቀረቡ በኋላ፣ በአውዳሚ የሰደድ እሳት የተጎዳውን በካሊፎርኒያ ግዛት የሎስ አንጀለስ አካባቢ ነዋሪዎችን በጸሎት ማስታወሳቸው ይታወሳል።
ቅዳሜ እለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሎስ አንጀለስ ከተማ አቅራቢያ እየተቀጣጠለ ባለው የእሳት አደጋ በደረሰው የሕይወት መጥፋት እና ሰፊ የንብረት መውድመት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን፥ ለሎስ አንጀለስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሆሴ ጎሜዝ በላኩት የቴሌግራም መልዕክት መግለጻቸው ይታወሳል።
ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎሜዝ እና በአደጋው ለተጎዱትን ማኅበረሰቦች ያላቸውን መንፈሳዊ ቅርበት አረጋግጠው፥ የሟቾችን ነፍስ ሁሉን ቻይ ለሆነው አምላክ በአደራ በመስጠት ሐዘን ለደረሰባቸው ቤተሰቦች በሙሉ መጽናናትን ተመኝተውላቸዋል።
ቅዱስነታቸው በተጨማሪም የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሚያደርጉትን የዕርዳታ ጥረት በጸሎት በመደገፍ፥ መጽናናትን እና ብርታትን ያገኙ ዘንድ ለሁሉም ሰው የእግዚአብሔርን ቡራኬ ሰጥተዋል።
በሎስ አንጀለስ አካባቢ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ቢያንስ የ28 ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ፣ ከ15,000 በላይ ህንፃዎች እንደወደሙ እና 63 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ በእሳት መቃጠሉ ታውቋል።