ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የማርያም አገልግሎት በእግዚአብሔር ላይ ያላትን ጥልቅ ተስፋ ይገልጻል” አሉ
ክቡራትን እና ክቡራን አድማጮቻችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በዕለቱ ያቀረቡትን አስተምህሮ ሙሉ ትርጉም ከማቅረባቸን አስቀድመን ለአስተንትኖ ይሆናቸው ዘንድ የመረጡትን የቅዱስ ወንጌል ክፍል እንደሚከተለው እናነብላችኋለን፥
“በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል በገሊላ ወደምትገኝ ከተማ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤ የተላከውም ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር። የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። መልአኩም ገብቶ፥ ‘ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ጸጋን የተመላሽ ሆይ! ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት” (ሉቃ. 1:26 - 28)።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! ዛሬ ‘ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን ነው’ ወደሚለው የኢዮቤልዩ ዓመት ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንመለሳለን። ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ መጀመሪያ ላይ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቤተ መቅደሱ አዳራሽ ብቻ ሳይሆን ለዮሴፍ ወደ ታጨች እና ከቤተሰቧ ጋር ወደምትኖር ማርያም ወደምትባል አንዲት ወጣት ዘንድም ደርሶ ያመጣውን የመለወጥን ውጤት ያሳያል።
ከኢየሩሳሌም በኋላ የታላቁ መለኮታዊ ብስራት መልዕክተኛ ገብርኤል በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሳ ወደማታውቅ ናዝሬት ወደ ተባለች መንደር ተላከ። በዚያን ጊዜ ናዝሬት በእስራኤል ውስጥ ገጠረማ አካባቢ በምትገኝ በገሊላ የምትገኝ አንዲት ትንሽ መንደር ነበረች። ናዝሬት በብዙ ችግሮች ውስጥ ከሚገኙ አረማውያን ጋር በድንበር የምትገናኝ መንደር ናት።
በዚያም መልአኩ ገብርኤል ፈጽሞ ያልተሰማ ይዘት ያለውን መልዕክት ይዞ በመጣ ጊዜ የማርያም ልብ ተረበሸ። ‘ሰላም ላንቺ ይሁን’ በሚለው ጥንታዊ የሰላምታ አሰጣጥ ምትክ ገብርኤል ድንግል ማርያምን በአክብሮት “ደስ ይበልሽ!’ አላት። ይህ ዓይነት ሰላምታ ነቢያት የመሲሁን መምጫ ለጽዮን ሴት ልጅ ለመንገር የሚጠቀሙት ስለሆነ ከቅዱሳት ታሪኮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው። (ሶፎ. 3፡14፤ ኢዩኤል 2፡21-23፣ ዘካ 9፡9)። እንዲሁም እግዚአብሔር ግዞቱ በሚያበቃበት ጊዜ እና በመካከላቸው በንቃት መገኘቱን ለሕዝቡ የሚገልጽበት የደስታ ግብዣ ነው።
በተጨማሪም እግዚአብሔር ማርያምን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ በማይታወቅ ተወዳጅ ስም፥ ‘በመለኮታዊ ጸጋ የተሞላሽ’ ብሎ ይጠራታል። ይህ ስም የእግዚአብሔር ፍቅር ለተወሰነ ጊዜ የኖረ እና በማርያም ልብ ውስጥ ገብቶ ማደሩን እንደሚቀጥል ይናገራል። ምን ያህል ‘ጸጋን የተሞላች’ እንደ ሆነች እና ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ጸጋ ምን ያህል ወደ ውስጧ ገብቶ የድንቅ ሥራው ውጤት እንዳደረጋት ይናገራል።
እግዚአብሔር ለማርያም ብቻ የሚሰጣት ይህ ተወዳጅ ስም ወዲያውኑ ከማረጋገጫ ጋር አብሮ ‘እይዞሽ አትፍር!’ በሚል ይቀርብላታል። ይህም እግዚአብሔር አስፈላጊ የሆኑ ተልዕኮዎችን ለአገልጋዮቹ በአደራ ሲሰጥ የሚነግቸው የማበረታቻ ቃል ነው። እግዚአብሔር ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለሙሴ እና ለኢያሱ ‘አትፍሩ!’ ይላቸዋል (ዘፍ. 15:1፤ 26:24፤ ዘዳ 31:8፤ ኢያሱ 8:1)። ‘ሁሉን ቻይ’፣ ‘ምንም የማይሳነው’ አምላክ እርሱ (ሉቃ. 1: 37) ከማርያም ጋር አብሯት እንደሆነ፣ ደጋፊዋ እና ዋና አጋሯ እንደሆነ እና ከሕዝቡም ጋር ለዘላለም የሚኖር አምላክ መሆኑን ይናገራል (ዘፍ. 28፡15፤ ዘፀ 3፡12፤ መሳ 6፡12)።
ከዚያም መልአኩ ገብርኤል ለድንግል ማርያም ተልዕኮዋ ምን እንደሆነ አበሰረላት። ከእርሷ መወለድ ስላለባት ሕፃን ንግሥና እና መሲሃዊ ተፈጥሮ የሚናገሩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በልቧ ውስት በማስተጋባት የጥንት ትንቢቶች ፍጻሜ አድርጎ አቀረበላት። ከአርያም የመጣው ቃል ማርያም ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የዳዊት ዘር የመሲሁ እናት እንደሆነች ያስታውሳታል። ንጉሥ የሚሆነው በሰብዓዊ እና በሥጋ ሳይሆን ነገር ግን በመለኮታዊ እና በመንፈሳዊ ሁኔታ ነው። ስሙ ‘ኢየሱስ’ ይባላል። ትርጉሙም ‘እግዚአብሔር ያድናል’ ማለት ነው (ሉቃ. 1፡31፣ ማቴ 1፡21)። የሚያድነውም ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ሁሉም ሰው ለዘላለም እንዲያውቀው በማሳሰብ ነው። በእርግጥም የነቢዩ ኢሳይያስን ቃል የሚፈጽም እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡- “ያዳናቸው መልዕክተኛው ወይም ልዑኩ ሳይሆን የእርሱ መገኘት። ‘በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ ከቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው’ (ኢሳ 63፡9)።
ይህ በፍፁም ልዩ የሆነ የእናትነት ክብር ማርያምን እስከ ውስጥ ድረስ ያሳስባታል። አስተዋይ ሴት በመሆኗም ክስተቶችን በልቧ ታሰላስል ነበር (ሉቃ. 2፡19፣51)። በራሷ ላይ እየደረሰ ያለውን ነገር ለመረዳት እና ለይታ ለማወቅ ትጥራለች። ማርያም ውስጣዊ እንጂ ውጫዊ ነገር አትመለከትም። ምክንያቱም ቅዱስ አጎስጢኖስ፥ ‘እውነት በውስጣዊ ሰው ውስጥ ይኖራል’ በማለት እንደሚያስተምረው ነው። ‘internale homine habitat veritas’ (De vera religione 39፣72)። በዚያ በተከፈተው እና ስሜታዊ በሆነው ልቧ ውስጥ በእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ በታመን እርሱ ያዘጋጀላትን ልዩ የ ‘በዓለ ሃምሳ’ ግብዣ ሰማች። ልክ በፍጥረት መጀመሪያ ላይ እንዳደረገው (ዘፍ. 1፡2) እግዚአብሔር ማርያምን በመንፈሱ ሊያሳድጋት ፈለገ። ተጠብቆ የቆየውን የሰው ልጅ ነፃነት ሳይጥስ በኃይሉ በ ‘ደመና’ ሊሸፍናት ፈለገ (1ኛ ቆሮ. 10፡1-2)። ምክንያቱም ወልድ በእርሷ ይኖራል፣ እርስዋም በወልድ ትኖራለችና።
ማርያምም በእምነት ደመቀች። ‘ቴዎፋነስ በቀኖና ብሥራት’ ላይ እንደገለጸው ‘ማርያም ብዙ መብራቶች ያሏት መብራት’ ናት። እጅ ሰጠች፣ ታዛዥም ሆነች፣ ቦታም አዘጋጀች። እርሷ ‘በእግዚአብሔር የታነጸች የሠርግ ቤት ናት’። ማርያም ቃሉን በሥጋዋ ተቀብላ በዚህ መንገድ ለሰው ፍጥረት የተሰጠውን ታላቅ ተልዕኮ ጀመረች። ራሷን እንደ ባሪያ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር አብ ተባባሪነት፣ ተሞልታ በቃና ዘገሊላ ሠርግ ላይ እንዳደረገች ሁሉ፣ ብዙዎች በሁለቱም እጆቻቸው ከእርሱ መቀበል እንዲችሉ የመለኮታዊ ሃብት ስጦታዎችን በክብር እና በሥልጣን ታስተዳድራለች።
ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ልባችን እርሱ ወደሚገኝበት ታቦት ይለወጥ ዘንድ፣ ጆሮአችን መለኮታዊ ቃሉን እንዲሰማ፣ የደከሙትን እና ተስፋ የሚያስፈልጋቸውን በእንግድነት ተቀብለን መንከባከብን ከአዳኛችን እናት ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንማር።”