ሊቃነ ጳጳሳት እና ኢዮቤልዩ፡ በታሪክ ውስጥ የቅዱስ በር መክፈቻ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
የእያንዳንዱ ኢዮቤልዩ ምሳሌያዊ ምስሎች አንዱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ የቅዱስ በርን ደፍ አቋርጠው የሚገቡበት ሁኔታ ነው። ይህ በመካከለኛው ዘመን ውስጥ ሥር የሰደደ ጊዜ ነው። ይህንን ቅዱስ በር በማቋረጥ የመጀመሪያው መንፈሳዊ ነጋዲ ወይም ተሳላሚ የሚሆነው ሁል ጊዜ የሮም ጳጳስ ነው። እ.አ.አ በ1450 ዓ.ም በጆቫኒ ሩሴላይ ዲ ቪቴርቦ የግል ሰንድ ላይ እንደ ተገለጸው እ.አ.አ በ1423 ዓ.ም የቅዱስ በርን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈተው በቅዱስ ዮሐንስ ላተራን ባዚሊካ በኢዮቤልዩ ዓመት ውስጥ ሲሆን ይህም የተከናወነው በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ማርቲን አምስተኛ ነበር። በቫቲካን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቅዱስ በር መክፈቻ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘገበው እ.ኤ.አ. በ 1499 የገና በዓል ላይ ሲሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አሌክሳንደር ስድስተኛ አማካኝነት ነበር፣ ይህ የቅዱስ በር የመክፈቻ ስነ-ስርዓት በቅዱስ ዮሐንስ ላተራን ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሮማውያን አብያተ ክርስትያኖችም ውስጥ እንዲከፈት ትእዛዝ ሰጥተዋል። " በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፤ ይገባልም፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል" (ዩሐንስ 10፡9)።
የቅዱስ በር የመክፈት ስነ-ስረዓት
የቅዱስ በር በጳጳሱ መከፈቱ የኢዮቤልዩ መጀመሪያን ያመለክታል። እ.ኤ.አ. የ2025 ዓ.ም ቅዱሱ ዓመት ይህንን ሥርዓት ያጠቃልላል፣ በመቀጠልም በገና ዋዜማ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተከናወነው መስዋዕተ ቅዳሴ በይፋ ተጀምሯል። የቅዱሱን በር የሚዘጋው የውስጥ ግድግዳ ፈርሶ እና በሩን ለመክፈት ቁልፉን የያዘው የብረት ሳጥን ተከፍቶ፣ በእዚያ በሚገኘው ቁልፍ አማካይነት ቅዱሱ በር ተከፍቷል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በምሳሌያዊ ሁኔታ በሩን ይከፍታሉ፥ ከእዚህ ቀደም ግን እንደ ባሕል በውጭ በኩል ያለውን የጡብ ማህተም ለመምታት መዶሻን መጠቀም ባሕል ለደህንነት ሲባል ግን ተቋርጧል። ከበዓሉ በኋላ፣ ምዕመናን በዚህ ቅዱስ በር እንዲያልፉ በሩ ለዓመት ክፍት ሆኖ ይቆያል። ይህ የገለጻ እንቅስቃሴ ከቅዱስ አመት ጋር የተያያዘውን የጋለ ስሜት ሙሉ ልምድን ያመለክታል።
ይህንን ደፍ መሻገር ደግሞ ከክርስቶስ ጋር በመገናኘት የታተመውን የልወጣን ወይም መንፈሳዊ ለውጥ የማምጣት ጉዞ ማለትም "በር" ከአብ ጋር አንድ ያደርገናል። ኢዮቤልዩ ለዓለም በሮችን የሚከፍት ጥልቅ የእምነት ታሪክ አካል ነው—የጳጳሱ እርምጃዎች ከእግዚአብሔር ሰዎች ጋር በይቅርታ ጎዳናዎች የሚሄዱበት ጉዞ ነው።
የ1900 ኢዮቤልዩ
የ1900 ዓ.ም ኢዮቤልዩ ዋና ዓላማዎች የዘመናዊነትን ፈተናዎች መጋፈጥን ያካተተ ነበረ። እ.ኤ.አ. በታህሳስ 24/1899 ዓ.ም የቅዱስ በር ተከፈተ። ሎ ኦዜርቫቶሬ ሮማኖ የተሰኘው ጋዜጣ በወቅቱ እንደ ዘገበው ከሆነ ከማለዳው ሰአታት ጀምሮ በከተማው ውስጥ “ያልተለመደ ግርግር” ይታይ ነበረ ሲል በወቅቱ ዘግቧል። የካርዲናሎች፣ የኤጲስ ቆጶሳት፣ ዲፕሎማቶች እና መኳንንት እንዲሁም ብዙ ምዕመናን በእግር ወይም በሕዝብ ማመላለሻ የሚጓዙ ሠረገላዎች ወደ “ትልቁ የክርስትና ቤተ መቅደስ” አቀኑ በማለት ገልጾ ነበር። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በአቅራቢያው ከሚገኙ መንገዶች የሚፈሱ ሠረገላዎች እይታ "አስደሳች" ሆነ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ ሦስተኛ "መጀመሪያ እና ብቸኛ" የቅዱስ በርን ተሻግረው ወደ ባሲሊካ ገቡ። ሥነ ሥርዓቱ እንዳለቀ ምእመናን እንዲገቡ በሮቹ ተከፈቱ።
የ1925 ዓ.ም
እ.አ.አ በታኅሣሥ 24/1924 ዓ.ም የገና ዋዜማ እለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የቅዱስ በር ከፈቱ። የቫቲካን ጋዜጣ እንደዘገበው የተከበረው ሥነ ሥርዓት የቅዱስ ዓመት መጀመሪያን ያመለክታል። የአምልኮ ሥርዓቱ የተካሄደው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ሲሆን በቅዱስ በር በአንደኛው በኩል የሊቃነ ጳጳሳቱ ዙፋን እና የጳጳሳዊ የመዘምራን ቡድን ከበስተጀርባው ይገኛል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ወደ ቅዱሱ በር ከመግባታቸው በፊት በጣሊያነኛ ቋንቋ "በሴዲያ ጌስታቶሪያ" (ተንቀሳቃሽ ዙፋን) ሥር ተቀምተዋል። "ፈጣሪ የሆንክ ጌታ ሆይ ና" ከተሰኘው ዝማሬ በኋላ በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ፒዩስ 11ኛ ወደ ቅዱስ በር ቀርቦ ከዓለም ዙሪያ ከሚገኙት የካቶሊክ ጳጳሳት ስጦታ የተሰጣቸውን መዶሻ ተቀበሉ፣ ከእዚያም በመቀጠል የቅዱስ በሩን ሦስት ጊዜ በመዶሻ መቱት፣ የአምልኮ ስነ-ስረዓት ከተከናወነ በኋላ የቅዱስ በሩን አልፈው መግባታቸው ይታወሳል።
የ1933 ኢዮቤልዩ
1900ኛውን የክርስቶስ ሙት አመት ዝክረ በዓል ምክንያት በማድረግ እ.አ.አ በ1933 ዓ.ም አንድ አስደናቂ ኢዮቤልዩ ታውጆ ነበር። ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ምዕመናን ለዚያ ቅዱስ ዓመት ሮም መጥተው ነበር።በምያዚያ 3/1933 ዓ.ም የቅዱስ በር መከፈት የደህንነት አመት ኢዮቤልዩ መጀመሩን ያመለክታል። ሎ ኦዜርቫቶሬ ሮማኖ የተሰኘው ጋዜጣ በእለቱ “በቅዱስ ጴጥሮስ፣ በቅዱስ ዮሐንስ፣ በቅዱስ ጳውሎስ እና በቅድስት ማርያም ማጆር ባዚሊካዎች ውስጥ የተገኙት ምዕመናን ቁጥር ከፍተኛ ነበር” ሲል በወቅቱ ገልጾ ነበር። የመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ከሰዓታት በኋላ በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ፒየስ 11ኛ የተከናወነ ሲሆን ከሚላን ከተማ ለመጡ 500 ምዕመናን በወቅቱ ልዩ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር።
የ1950 ዓ.ም
እ.አ.አ በታኅሣሥ 24/1949 ዓ.ም የክርስቲያኑ ዓለም “ልዩ የጸጋ ስጦታ” በፊት ተደስተው ነበር፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 12ኛ የቅዱሱን በር ምሳሌያዊ በሆነ መልኩ ሦስት ጊዜ በሩን በመዶሻ መትተው ከፍቱ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሲስቲና የጸሎት ቤት ውስጥ የመጀመሪያውን ሥርዓተ አምልኮ ካደረጉ በኋላ ወደ ቅዱሱ በር በመሄድ "የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፥ ወደ እነርሱ ገብቼ ጌታን አመሰግናለሁ። ይህች የጌታ ደጅ ናት፥ ወደ እርሷ ጻድቃን ይገባሉ። ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፥ ይህች ከጌታ ዘንድ ሆነች፥ ለዓይናችንም ድንቅ ናት። ጌታ የሠራት ቀን ይህች ናት፥ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርሷም ደስ ይበለን" (መዝሙር 118፡19-24) የሚለውን መዝሙር ሦስት ጊዜ ከዘመሩ በኋላ ሦስት ጊዜ በሩን በመዶሻ መቱ፣ የታሸገው የጡብ ግንብ ፈራረሰ፣ እና ጳጳሱ እምነትንና በጎ አድራጎትን የሚያመለክት ሻማ ይዞ የቅዱስ በሩን መድረክ አልፎ በመግባት የኢዮቤልዩ በዓልን አሰጀመሩ።
የ1975 ኢዮቤልዩ
ለእርቅ የተሠጠው እ.አ.አ የ1975ቱ ቅዱስ ዓመት በ1974 ዓ.ም የገና ዋዜማ የጀመረ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ የቅዱስ በር ከፈቱ። የአምልኮ ሥርዓቱ ጳጳሱ የቅዱስ በር መድረኩን ከማለፋቸው በፊት የመንፈስ ቅዱስን ጥሪ መዘመር እና የበሩን መቃኖች በተቀደሰ ውሃ መባረክን ያካተተ እንደ ነበረ ተዘግቧል።
የ1983 ዓ.ም
እ.ኤ.አ. በ1983 ዓ.ም፣ የክርስቶስን ህማማት እና ትንሳኤ የሚያስታውስ ልዩ ኢዮቤልዩ ነበር። እ.አ.አ በመጋቢት 25/1983 ዓ.ም ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቅዱስ በርን ከፈቱ፣ ምሳሌያዊ ተፈጥሮውን ወደ ጸጋ እና የድነት ሁኔታ እንደመግባት እንደሚቆጠር አጽንኦት ሰጥተው ተናግረው ነበረ።
የ 2000 ኢዮቤልዩ
እ.አ.አ በ1999 ዓ.ም የገና ዋዜማ ላይ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ ለ2000 ዓ.ም ታላቁ ኢዮቤልዩ ቅዱስ በር ከፈቱ። ድርጊቱ የሁለት ሺህ ዓመታት ታሪክን ወደ አንድ አስደሳች ጊዜ ያመላክታል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጸሎታዊ መንገድ የቅዱስ በሩን መሻገራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በጭብጨባ ተሞልቶ ነበር፣ ይህም የአዲሱን ሺህ ዓመት ተስፋ ያመለክታል።
የ2015 ቅዱስ ዓመት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ባንጉዊ የሚገኘውን የኖትርዳም ካቴድራል ቅዱስ በርን በመክፈት አስደናቂው የምሕረት ኢዮቤልዩ እንዲጀመር ማድረጋቸው ይታወሳል። እ.አ.አ በታኅሣሥ 8/2015 ዓ.ም፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የቅዱስ በርን ከፈቱ፣ ከእርሳቸው በፊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከነበሩት ቤኔዲክት 16ኛ ጋር በመሆን ቀጣይነት ባለው ምሳሌያዊ ምልክት ይህንን ልዩ የምሕረት አመት ኢዩቤሊዩ አስጀመሩ።
መጪው የ2025 ቅዱስ ዓመት ይህንን ባህል ለመቀጠል ይፈልጋል፣ ይህም የእግዚአብሔርን ፍቅር እና በክርስቶስ የመዳን ተስፋ ላይ አፅንዖት ይሰጣል።