MAP

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የወንጌል ደስታን መመስከር ሰላምን እና ተስፋን እንደሚሰጥ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ኅዳር 18/2017 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የወንጌል ደስታ ምስክርነት ሰላምን እና ተስፋን እንደሚያመጣ ገልጸዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባቀርቡት የዕለቱ አስተምህሮአቸው ስለ መንፈስ ቅዱስ የጀመሩትን አስተምህሮ በመቀጥል ከመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች አንዱ በሆነው በመንፈሳዊ ደስታ ስጦታ ላይ ትኩረት አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ባቀረቡት አስተምህሮአቸው፥ ከዓለማዊ ደስታዎች በተለየ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መገናኘት በልባችን ውስጥ ጥልቅ እና ዘላቂ ደስታን እንደሚፈጥር እና ይህን ደስታ ከሌሎች ጋር እንድንካፈል ያነሳሳናል ሲሉ ተናግረዋል።

ጸጋ እና ነፃነት
የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በጸጋ እና በነፃነት መካከል ያለ አንድነት ውጤቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስረድተው፥ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ በልዩ እና አስደሳች በሆነ መንገድ እምነት እውን ሊሆን የሚችልበትን መንገድ አስረድተዋል።

ያለ ልዩነት ሁላችንም ድንቅ ስጦታዎች እንዳሉን ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህ ስጦታዎች ዘወትር በጎ አድራጎትን እና ታጋሽነት ከማሳደግ በተጨማሪ ትሑት የሰላም መልዕክተኞች እንድንሆን የሚያግዙን ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

“ደስታ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው!”
የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በደስታ የመሞላትን ስሜት እንደሚሰጠን እና “ይህም አንድ ሰው ሁል ጊዜ በውስጣችን የሚኖር ደስታን እንድንመኝ ያደርገናል” ሲሉ አስረድተዋል። ቅዱስ አውግስጢኖስ ለእግዚአብሔር ሲናገር፥ “አንተ እኛን ለራስህ ፈጠርከን፥ ልባችንም በአንተ ዘንድ እስኪያርፍ ድረስ ዕረፍት የለውም” ማለቱን አስታውሰዋል።

ከሌሎች ጋር የሚጋሩት ደስታ የበዛ ይሆናል
"የወንጌል ደስታ እንደ ሌሎች ደስታዎች በየዕለቱ ሊታደስ እና ወደ ሌሎች ሊተላለፍ ይችላል" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከእግዚአብሔር ፍቅር ጋር ቀጣይነት ላለው ግንኙት ምስጋና ይግባውና፥ "የወንጌል ደስታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደሚያብብ ወዳጅነት የሚደርስ፣ ከጠባብነት እና ራስ ወዳድነት ነፃ የሚያወጣን መሆኑን አስረድተዋል።

“ይህንን ደስታ ከሌሎች ጋር መካፈል ተፈጥሯዊ በመሆኑ ወንጌልን ለሌሎች የመመስከር ጥረታችን ሁሉ ምንጭ እና ተነሳሽነትንም የምናገኘው ከዚሁ ደስታ ነው” ብለው፥ “የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነውን ደስታ ከሌሎች ጋር ሲጋሩት ከቀን ወደ ቀን ይጨምራል እንጂ ፈጽሞ አይጠፋም” ሲሉ አስረድተዋል።

ደስተኛው ቅዱስ ፊሊጶስ ኔሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአስተህሮአቸው ማጠቃለያ ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት በሮም ይኖር የነበረውን የቅዱስ ፊሊፕ ኔሪ ምስክርነትን አስታውሰው፥ “የደስታ ቅዱስ” በመባል ይታወቅ እንደ ነበር ገልጸዋል።

ይህ ቅዱስ ለድሆች እና ለተናቁት ልጆች ይናገራቸው የነበረውን ቃላት ሲያስታውሱ፥ “ልጆቼ ሆይ አይዞአችሁ! ብስጭትን ወይም ትካዜን አልፈልግም፤ ኃጢአትን የማትሠሩ ከሆነ ይህ ለእኔ ይበቃኛል” ማለቱን ጠቅሰዋል። “የቅዱስ ፊሊጶስ ደስታ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነበር” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዚህ ደስታው እውነተኛ ወንጌላዊ ለመሆን እንደበቃ ተናግረዋል።

ወንጌል የሚሰጠው ደስታ
“ወንጌል” የሚለው ቃል የምስራች ማለትን ይገልጻል ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ምዕመናን በላከው መልዕክቱ በምዕ. 4፡4-5 ላይ፥ “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” ያለውን ምክር ልብ እንዲሉት አሳስበዋል።

 

27 Nov 2024, 17:11