ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጤና ባለሞያዎች ተግባር ሕመምን ከማዳን በላይ መሆኑን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የምሥረታውን 800ኛ ዓመት የሚያከብረውን የኔፕልስ ዩኒቨርስቲ የጥርስ ሐኪሞች ቡድንን ዓርብ ዕለት በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። በዓለም ውስጥ በመንግሥት የሚደገፍ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በጣሊያን ኔፕልስ ከተማ የሚገኝ የፌዴሪኮ 2ኛ ዩኒቨርስቲ የመሥራቹን ራዕይ የተሸከመ እና ሁለንተናዊ እውቀትን በማስተዋወቅ የጋራ ጥቅምን በማገልገል ላይ የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ነው” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በሕክምናው መስክ ለሚሠሩ ሰዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ “መጀመሪያ ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረስ፥ ሁለተኛ መንከባከብ፣ ሦስተኛ መፈወስ” በሚል የሕክምና ባለሙያዎችን ለመምራት የተቀመጠው ይህ መሪ ሃሳብ ጊዜ የማይሽረው እና አግባብነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ ሦስት መመሪያዎች በሕክምናው ዘርፍ መሪ ምክር ሆነው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፥ እያንዳንዱ እርምጃ ጥልቅ ጥበብን የያዘ መርህ እንደሆነ አብራርተዋል።
ታካሚውን አለመጉዳት
የመጀመሪያው መርህ “በታካሚው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረስ!” የሚል እንደሆነ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በተግባር ላይ ያለውን ጠቀሜታ አጽንኦት ሰጥተው፥ ይህም አንድ በሽተኛ ቀድሞውኑ የደረሰበትን ሕመም እና ስቃይ የመገንዘብ እውነታን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
ዶክተሮች ዋና ግዴታቸው ሕመምን ማባባስ ሳይሆን ማስታገስ መሆኑን በማስታወስ ሁል ጊዜ እርምጃ መውሰድ እንዳባቸው አሳስበው፥ ከዚያም በሁለተኛው መርህ ላይ በማሰላሰል መንከባከብ የእግዚአብሔር ጥሪ መሆኑን ገልጸዋል።
“እግዚአብሔር ቅርብ፣ ሩህሩህ እና ለጋስ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቫቲካን በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ሁሉ ለታካሚዎቻቸው ይህንን መለኮታዊ ዘይቤ እንዲያስተላልፉ አሳስበው፥ በሃያዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ደረጃ ላይ እያሉ የሳንባቸው ክፍል የተወገደበትን የግል ታሪክ አስታውሰዋል።
ታካሚውን መንከባከብ
ከሕመሙ ለመፈወስ መርፌ ቢሰጣቸውም ነገር ግን ከሁሉ የበለጠ ጥንካሬን የሰጣቸው የነርሶች እጅ መሆኑን በመግለጽ ፥ ይህ የሰው ልጅ ርኅራኄ ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝ ተናግረዋል። “ይህ መርህ የሕመም ምልክቶችን ከማከም ባለፈ ጠቅላላውን ሰውነት ማለትም አካልን፣ አዕምሮን እና መንፈስን መንከባከብ ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ታካሚውን መፈውስ
የሕክምና ባለሙያዎች ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እና ምልክት የፈወሰውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲመስሉ ጥሪ አቅርበው፥ ሕሙማንን መፈወስ ከሙያው በላይ የሆነ የተቀደሰ ተግባር መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስን በመጥቀስ “የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ የቆሰሉትን ሁሉ መፈወስ እና የሰው ልጆችን ማስታረቅ” መሆኑን በመናገር፥ የሕክምና ዶክተሮች ለሚሰቃዩ ሰዎች በሚያመጡት መልካም ነገር እንዲደሰቱ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ በቫቲካን የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ተወካዮች ላሳዩት ትጋት እና ጽናት ምስጋናቸውን ገልጸው፥ የአስተማሪነት እና የፈውስ ሚና እንዳላቸው አስታውሰዋል።
“የሕክምና ዶክተር ሕሙማንን ከበሽታቸው ለመፈወስ፣ ለመንከባከብ እና ሕይወትን ወደ ጎን እንዳይል የተጠራ መሆኑን ተናግረው፥ ነገር ግን ይህን ማድረግ የማይችል መስሎ ከታየው ቢያንስ “እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ አብረዋቸው ሊሆን ይገባል” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።