ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሃይማኖታዊ እሴቶችን አለማክበር ወደ አለመቻቻል ደረጃ ሊያደርስ እንደሚችል ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በልዩነት ላይ የተመሠረተ አድልዎን መቃወም ለብዙዎቹ የዕለት ተዕለት ልምድ እንደሆነ ገልጸው፥ መንፈሳዊ እውነታዎችን እና እሴቶችን በተለያዩ እምነቶች መካከል መጋራት ያለውን ጠቀሜታ ጠቁመዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ለተከበሩ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ክብር አለመስጠት ዛሬ ዓለማችን ከሚገኝበት የችግር መንስኤዎች መካከል አንዱ ነው” ሲሉ “በስሪ ናራያና ዳርማ ሳንጎም” አስተባባሪነት የተዘጋጀን የመላው ኃይማኖቶች መቶኛ ዓመት ለማክበር በቫቲካን ለተሰበሰቡት የእምነት መሪዎች እና ተወካዮች ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።
የስሪ ናራያና ዳርማ ሳንጎም ማኅበራዊ ተሃድሶ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የስሪ ናራያና ዳርማ ሳንጎም ውርስ በመደገፍ ባደረጉት ንግግር፥ የሂንዱ መንፈሳዊ መመሪያ እና ማኅበራዊ ተሐድሶ የሕይወትን ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ መሻሻልን ለማስተዋወቅ ወስኗል” ሲሉ ተናግረው፥ የዘውድ ሥርዓቱን በመቃወም፥ በማንኛውም ደረጃ ወይም መልክ የሰው ልጅ ዘር እና ሃይማኖታዊ ባህል ሳይለይ የአንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ አባላት ናቸው” በማለት መልዕክት ማስተላለፉን አስታውሰዋል።
“ሃይማኖቶች በአንድነት ለተሻለ የሰው ልጅ ሕይወት”
ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላ “ሃይማኖቶች በአንድነት ለተሻለ ሰብአዊነት” በሚል መሪ ርዕሥ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ድጋፍ የተዘጋጀው የሁሉም ሃይማኖቶች ጉባኤ ለዘመናችን ጠቃሚ እና ዋጋ ያለው ነው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ላይ ገልጸውታል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው፥ “ዛሬ በዓለማችን ውስጥ በተለያዩ አገራት ሕዝቦች መካከል ያለው አለመቻቻል እና ጥላቻ እየጨመረ ነው” ብለው፥ በጎሳ ወይም በማኅበራዊ አደረጃጀት፣ በዘር፣ በቀለም፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት ልዩነት ላይ የተመሠረተ መድልዎ፣ ውጥረት እና ሁከት ያሉባቸው አጋጣሚዎች የብዙ ግለሰቦች እና ማኅበረሰቦች የዕለት ተዕለት ልምድ እየሆኑ መምጣታቸው በድሆች፣ ራስን መከላከል በማይችሉ እና ድምጽ በሌላቸው ላይ ጉዳት እያስከተሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
እኩልነት እና ወንድማማችነት ያለበት ሰብዓዊነት
ቅዱስነታቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየካቲት 2010 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ከአል-አዝሃር ታላቅ ኢማም አህመድ አል ጣይብ ጋር የተፈራረሙትን የሰው ልጆች ወንድማማችነት የዓለም ሰላም እና አብሮ የመኖር ሠነድን አስታውሰዋል። ሠነዱ “እግዚአብሔር ሁሉንም የሰው ልጆች በመብት፣ በግዴታ እና በክብር እኩል አድርጎ እንደ ወንድም እና እህት አብረው እንዲኖሩ ጠርቷቸዋል” የሚል እንደሆነ ይታወሳል።
“መዋደድ እና መከባበር በሃይማኖቶች መካከል ያለ የጋራ እውነት ነው”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው፥ “የአንድ አምላክ ልጆች እንደመሆናችን መጠን እርስ በርሳችን መዋደድ እና መከባበር፣ ብዝሃነትን እና ልዩነቶችን በወንድማማችነት እና በመደመር መንፈስ ማክበር እና መተሳሰብ ሁሉም ሃይማኖቶች የሚካፈሉት መሠረታዊ እውነት፣ ለእርስ በርሳችን እንዲሁም ለጋራ መኖሪያ ምድራችንም አስፈላጊ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው፥ እንደነዚህ ያሉ ትምህርቶችን ችላ ማለት በዓለም ላይ የሁከት መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህን ትምህርቶችን እንደገና ማግኘት የሚቻለው በተጨባች ለመኖር የምንጥር ከሆነ እና ከሁሉም ሰው ጋር ወንድማማችነትን እና ወዳጃዊ ግንኙነቶችን ከፈጠርን ብቻ እንደሆነ አስገንዝበው፥ ዓላማው በብዝሃነት ውስጥ ያለውን አንድነት ማጠናከር፣ በልዩነቶች መካከል ተስማምቶ አብሮ መኖርን በማረጋገጥ፣ ችግሮች ቢኖሩም ፈተናዎችን ማሸነፍ የሚቻለው የሰላም ፈጣሪዎች በመሆን እንደሆነ አስረድተዋል።
ግለኝነት በጋራ መቃወም
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እርስ በእርስ የመከባበር፣ የመተሳሰብ፣ የእርቅ እና የወንድማማችነት ባህል እንዲጎለብት በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ እንደሚተባበሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ይህ መልዕክት ባለፈው መስከረም ወር በኢስቲቅላል የጋራ መግለጫ ላይ የተገለጸ መሆኑ ሲታወስ፥ ግለኝነትን፣ መገለልን፣ ግዴለሽነትን እና ሁከትን ለመከላከል እንደሚያገለግል ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጋራ መለያ ባህሪያት በመጥቀስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ተወካዮች በእምነታቸው እና ሥር በሰደዱ ጽናታቸው የተሻለ ሰብዓዊነትን ለመገንባት አብረው መጓዝ እና መሥራት ይችላሉ” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።