MAP

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሃኪም እገዛ ህይወትን ማቋረጥ እና ፅንስ ማቋረጥን ትቃወማለች  የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሃኪም እገዛ ህይወትን ማቋረጥ እና ፅንስ ማቋረጥን ትቃወማለች   (©Natalya Lys - stock.adobe.com)

የኮሪያ ብጹአን ጳጳሳት ፅንስ ማቋረጥ እና በእገዛ ህይወት ማቋረጥን በመቃወም ‘ፕሮ-ላይፍ’ የተሰኘ ንቅናቄ ማስጀመራቸው ተነገረ

የደቡብ ኮሪያ ብጹአን ጳጳሳት እና ድርጅቶች በፅንስ ማቋረጥ እና በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣው በሃኪም እርዳታ ህይወት ማቋረጥ ጥሪዎችን በተመለከተ በቀረቡት የህግ ለውጦች ላይ ተቃውሞዋቸውን አጠናክረው በቀጠሉበት በአሁኑ ወቅት፥ በደቡብ ኮሪያ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተቃውሞውን በማጠናከር ‘ፕሮ ላይፍ ሙቭመንት’ ተብሎ የተሰየመ ንቅናቄ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደገና ልታስጀምር እንደሆነ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኮሪያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ የቤተሰብ እና ሕይወት ነክ ጉዳዮች ኮሚቴ ፕሬዚዳንት የሆኑት የጄጁ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሙን ቻንግ-ዎ ይህ ንቅናቄ “ሕይወትን ከመጀመሪያው እስከ ተፈጥሮአዊ ፍጻሜው ድረስ ለመጠበቅ የተልዕኮውን ስሜት እና ጥሪን እንደገና ለማነቃቃት” እና “ትንቢታዊ ጩኸት ለማሰማት” ዓልሞ ዘመቻውን ለማስፋፋት ማቀዱን ያስታወቁ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው ይሄንን አስመልክተው የቫቲካን የዜና ወኪል ለሆነው ፊደስ ኒውስ እንደተናገሩት ይህ ተነሳሽነት “የሰው ልጅን ህይወት የማይገሰስ ክብር” ወደ ህዝባዊ ውይይት እና ፖለቲካዊ እርምጃ ለመመለስ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተጠነሰሰው ይህ ንቅናቄ የተለያዩ ክልላዊ ውጥኖችን ለማስተባበር እንዳለመ የተነገረ ሲሆን፥ ከእነዚም መካከል ለተቸገሩ እናቶች እንክብካቤ እና ድጋፍ የሚሰጥ “ያልተወለዱ ሕይወቶች ፕሮጀክት” የተሰኘ እንዲሁም በባህላዊ እንቅስቃሴዎች እና ቅስቀሳዎች “የሕይወት ባህልን” የሚያበረታታውን “ሕይወት 31” የመሳሰሉ መርሃ ግብሮች እንደሚኖሩት ተገልጿል።

ነሃሴ 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ብጹእ አቡነ ሙን የጳጳሳት ጉባኤ የሥነ መድሃኒቶች ጥናት ኮሚቴ እና የካቶሊክ ሥነ መድሃኒቶች ምርምር ኢንስቲትዩትን ጨምሮ የካቶሊክ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በመሆን የእናቶች እና የህፃናት ጤና ህግ ማሻሻያዎችን በተመለከተ ከብሄራዊ ምክር ቤት የጤና ኮሚቴ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ተገልጿል።

በ 11 የኮሪያ ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት የተደገፈው ይህ ረቂቅ ህግ እ.አ.አ. በ 2019 ዓ.ም. የወጣውን እና የሕገ መንግስታዊው ፍርድ ቤት ፅንስ ማቋረጥ ፀረ ሕገ መንግሥታዊ ነው ብሎ ያወጀውን የሕግ ክፍተቶችን ለመፍታት እንደሚፈልግ ተነግሯል።

ብጹአን ጳጳሳቱ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ ከዋለ ፅንስ ከማህፀን ውጭ ሊኖር የሚችል ቢሆንም እንኳን ፅንስ ማቋረጥን እንደሚፈቅድ እና በፈቃደኝነት እርግዝናን የማቋረጥ ገደቦችን እንደሚያስወግድ ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ ቤተክርስቲያን እንደዚህ አይነት እርምጃዎች ፅንሱን በህይወት የመኖር መብቱን የሚነፍገውን “ያልተገደበ ፅንስ ማቋረጥን” ሊፈቅድ እንደሚችል አሳስባለች።

የሴኡል ሃገረ ስብከት የፕሮ ላይፍ ንቅናቄ ኮሚቴ ዋና ጸሃፊ የሆኑት አባ ሊዮ ሴክ-ጁን ጉዳዩ ህዝባዊ ግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን እንደሚፈልግ ገልጸው፥ ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ውይይቶች እንደተካሄዱ በማስታወስ፥ “የጽንሱ ዕድሜ ምንም ይሁን ምን ፅንስ ማቋረጥን እንቃወማለን” ብለዋል።

ካህኑ በማከልም ‘አማኞች እና ሁሉም መልካም ሰዎች የህይወት ማዕከላዊ እሴት የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ክብር እንዳይነኩ ጉዳዩን በግልፅ እና በስፋት ማስረዳት’ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ነሃሴ 22 በብሄራዊ ምክር ቤት በተካሄደው መድረክ ላይ የሴኡል ረዳት ጳጳስ እንዲሁም የሥነ መድሃኒት እና ህክምና ኮሚቴ ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹእ አቡነ ኩ ዮ-ቢ የታገዘ ህይወትን የማቋረጥ ተግባር እና የታገዘ ራስን ማጥፋት ድርጊትን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ክርክሩ እስከ ህይወት ፍጻሜ ጉዳዮች ድረስ እንደሚሄድ ጠቅሰው፥ በአሁኑ ወቅት እየጨመረ የመጣው ህይወት የማቋረጥ እና በእገዛ ራስን የማጥፋት ፍላጎት የመዳን ተስፋ በመጥፋቱ እንደሆነ አስረድተው፥ ህብረተሰባችን ለብቃት እና ለምርታማነት ብቻ አፅንዖት ሲሰጥ ታማሚዎችን መንከባከብ እንደ ብክነት እና ከንቱ ተግባር አድርጎ እንደሚወሰደው እና ይህም ታማሚዎችን ወደ ሞት የሚያደርስ ድርጊት ነው ብለዋል።

ብጹእነታቸው የህብረተሰቡ ሰብአዊነት የሚለካው ለታመሙ እና ለደካሞች በሚያደርገው የእንክብካቤ መንገድ እንደሆነ በመግለጽ፥ ተጋላጭ ህሙማንን ችላ ማለት ወይም ወደ ሞት ጎዳና እንዲጓዙ ጫና ማድረግ ማህበረሰቡን ከሥነ ምግባራዊ መሰረቱ እንደሚያጠፋ አስጠንቅቀዋል።

በእገዛ ራስን የማጥፋት ድርጊትን እንደ የርህራሄ ተግባር አድርጎ ማሰብ የእውነተኛ እንክብካቤን ትርጉም ማዛባት መሆኑንም በማስጠንቀቅ፥ ለእርሳቸው በራስ መወሰን በሕያዋን ላይ ብቻ ሊተገበር የሚችል እንደሆነ እና ሞት እንደ መብት ሊቆጠር ስለማይችል ከመሠረታዊ የህይወት መብት መብለጥ እንደማይችል አስረድተዋል።

01 Sep 2025, 14:21