MAP

ብጽዕ ገብረሚካኤል ዘ ኢትዮጲያ ብጽዕ ገብረሚካኤል ዘ ኢትዮጲያ 

ብፁዕ ገብረሚካኤል

በነሐሴ 23/2017 ዓ.ም ቤተክርስቲያን የአባታችን የብፅዕ ገብርሚካኤልን ሰማዕትነት እንድናከብር ታሳስበናለች።ከቤተክርስቲያን ጋር በቅድሚያ ይህንን የሃይማኖት ትልቅ ፍሬና ታላቅ ሰማዕት የሰጠንን እግዚአብሔርን እናመስግነው። ቀጥለን ደግሞ የተቀደሰውን ገድላቸውን አጥብቀን በማስተዋል እናስተንትን። በመንፈሳዊ ጀግንነታቸው በመደነቅ በመንፈሳችን እናክብራቸው፤ በመጨረሻም እንደ እርሳቸው የጸናና የከበረ ሃይማኖት ጠባቂዎች ለመሆን ወስነን አብነታቸውን እንከተል፡፡

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን 

«ተሰአሎ ንጉሥ ለብፁዕ ገብረሚካኤል ወይቤሎ ንግር ሃይማኖትከ፣ አውሥኦ ብፁዕ አአምን በኢየሱስ አምላክ ወሰብእ ወበአሐቲ መንበረ ጴጥሮስ፣ ሰማዕተ ኮነ በሃይማኖት ወወረሰ መንግሥተ ሰማያት ንጉሥ አፄ ቴዎድሮስ ብፁዕ ገብረ ሚካኤልን «ሃይማኖትህን ንገረኝ አሉአቸው፣ ብፁዑም (አባ ገ/ሚካኤል) «አምላክና ሰው በሆነ በኢየሱስ ክርስቶስና በአንዲት የጴጥሮስ መንበረ አምናለሁ ሲሉ መለሱላቸው፣ ስለ ሃይማኖትም ሰማዕትነትን ተቀበሉ፣ መንግሥተ ሰማያትንም ወረሱ (ዋዜማ ዘብፁዕ ገብረሚካኤል)።

ብፁዕ አባ ገብረሚከኤል በ1788 ዓ.ም. በጐጃም ልዩ ስሙ ዲቦ በተባለ መንገደር ተወለዱ። ከልጅነታቸው ጀምረው የአገራችንን ትምህርት ማለት ዜማ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ቅኔ ወዘተ … ለመማር ተሰማሩ። በትምህርት ትጋታቸውና በውጤታቸው መምህሮቻቸው በጣም ያደንቋቸው ነበር። ይህንን ሁሉ መንፈሳዊ እውቀት ከአካበቱ በኋላ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር በሙሉ ልባቸው ሊሰጡ ፍላጐትና ዕቅድ ስለነበራቸው በ25 ዓመት ዕድሜያቸው በመርጡለ ማርያም ገዳም ሊመነኩሱ ገዳም ገብተው ሳሉ የዕውቀትና የምርምር ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው ዕውቀትን፣ ትምህርትና እውነትን ለማግኘት ብለው ከገዳም ወደ ገዳም ይዘዋወሩ ጀመር።እንደዚህም እያሉ ሲታገሉ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሕሊናቸውን ያስጨንቅ የነበረው የሃይማኖት ልዩነትና ጭቅጭቅ ገጠማቸው።

በዚህም ዕረፍት አጥተውና ተጨንቀው እያሉ «ጌታዬና መድኃኒቴ ጽድቅ የት እንደምትገኝ ግለጥልኝ፤ አንተ ጻድቀ እንደሆንክ አምናለሁ። ጻድቅ እኔ ነኝ፣ ትክክለኛ የኔ ነው ወዘተ…  የሚሉኝ ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ግን ጽድቅን ሳትበላሽ ከምንጭዋ ላገኛት እፈልጋለሁ እያሉ ጸለዩ። እግዚብሔርም ጸሎታቸውንና የልባቸውን ምኞች ሰምቶ ከቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ዩስጢኖስ  ጋር አገናኛቸው። ብፅዕ ገብረሚካል በቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ሕይወት ዘመን በብዙ የሃይማኖት ትምህርት ታነጹ። ከእርሳቸውም ጋር በመሆን ግብፅን፤ ኢየሩሳሌምንና የሮም መንበር ጴጥሮስን ጐበኙ።

የመንበረ ጴጥሮስ ሃይማኖት በጣም ደስ አላቸው፣ እጅግም ወደዱት፤ በዚህ ጽድቅና እውነት እንደሚገኝ ተረዱ፤ አበክረውም ተገነዘቡ። ግብፅን፣ ሮምንና እየሩሳለምን ጐብኝተው ወደ አገራቸው በተመለሱ ጊዜ ሁሉን መርምርውና በሚገባ ተረድተው ስለነበረ የሰውን ዓይንና ይሉኝታ ሳይፈሩ የመንበረ ጴጥሮስን ሃይማኖት ተቀበሉ። ተቀብለው ሲያበቁ ደግሞ ዝም አላሉም፣ ሌሎችን ለማስተማርና ለማስረዳት ቆርጠውና ታጥቀው ተነሡ። ጠላቶቻቸው ወደ ቀድሞው ሃይማኖታቸው ሊመልሱአቸው ታገሉ፤ ያላደረጉት ጥረናት ያላደረሱባቸው ፈተና አልነበረም። ነገር ግን አልሆነላቸላቸውም ፣ መጥፎ ሐሳባቸውንና ምኞታቸው ሊሳካላቸው አልቻለም።ብፁዕ ገብረሚካኤል በእምነታቸው ጸንተው ቀጠሉ እንጂ ወደኋላ አላፈገፈጉም፣ በደረሳቸው መከራና ሥቃይ አልተበገሩም፡፡

የብፁዕ ገብረሚካኤል ጽናትና ብርታት ጠላቶቻቸውን እጅግ አስቆጣቸው፤ በኃይልም ሃማኖታቸውን ሊያስክዷቸው ሞከሩ። በብዙ የፈተና ዓይነቶች ተፈታተኗቸው፣ በብርቱ ግርፋት ሰውነታቸውን አቆሰሏቸው፤ በጽኑ አሥራትም አሰቃዩአቸው። የብፁዕ አባታችን አንገርጋሪ «በአውደ ንጉሥ ቀስፈው በጥብጣቤ ሐብል ለብፁዕ ገብረሚካኤል አርአየ ተአምረ ውስተ ጉባኤሁ ለልፁል፤ አማን ተላዌ ጊዮርጊስ ገባሬ ኃይል ( በንጉሥ ፊት ብፁዕ ገብረሚካኤልን በጅራፍ ገረፉአቸው፤ በልዑል ፈጣሪ ዙፋን ተአምራትን አሳዩ በእውነት የጊዮርጊስ ተከታይ በመሆናቸው ድንቅ ነገርን ሠሩ)"።

በእስር ቤት ለሁለት ዓማታት ያህል በብርቱ ከተሰቃዩ በኋላ ነሐሴ 23 ቀን 1847 ዓ.ም. የሰማዕትነትን አክሊል ለመጫን ወደ መንግሥተ ሰማያተ በረሩ። እ.አ.አ መስከረም 23 ቀን 1919 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን በሮም ለዓለም ሕዝበ ክርስቲያን አባ ገብረሚካአል የክርስቶስ ሰማዕት መሆናቸውን ከገለጡ በኋላ ብፅዕናቸውን አወጁላቸው። ቀጥሎም ሕዝበ ክርስቲያኑ በሙሉ ለብፁዕነት የሚሰጠውን ክብር እንዲሰጣቸው አዘዙ። የብፁዕ አባታችን ሰማዕት መልክዕም «ሰላም ለሞትከ ዕረፍተ ጻድቃን ዘኮነ፣ አምሳለሊሁ ለኢየሱስ ዘሞተ በአንቲአነ፣ ለነኒ ሃበነ ገብረሚካኤል አቡነ፣ ለነፍስነ ሞገስ ወለልብነ ዛህነ ወኀሎ ቀንብርክብ ዘነፍስነ ድኂነ። (የጻድቃንን እረፍት ለሚመስለው ሞትህ ሰላም ይሁን፣ አባታችን ገብረሚካኤል ሆይ! ሞትህ ስለ እኛ የሞተውን የክርስቶስን ሞት ይመስላል፤ አባታችን ሆይ ለነፍሳችን ደኀንነት እንድናገኝ ለልባችን ጸጋና ዕረፍት ስጠን ይላል።

ብፁዕ አባ ገብረሚካኤል በብዙ ትግልና ጥረት ያገኙትን ሃይማኖት ጠንክረውና በርትተው ያዙት፣ ስለእርሱም ውርደትና ስቃይን ተቀበሉ፣ ሃይማኖታቸውን ከመክዳት ይልቅ ደማቸውን ማፍሰስ መረጡ። በዚህ ምክንያት በንግሥተ ሰማያት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጁ። ስለዚህ  ብፁዕ አባታችንን በአድናቆትና በተመስጦ እንመልከታቸው። ሃይማኖታችን ከሃይማኖታቸው ጽናት በብዙ መንገዶችን ይለያያል፤ የእኛ እምነት ደካማና ቀዝቃዛ ሲሆን የእርሳቸው ግን ብርቱና የጋለ፣ ሙሉና ጥልቅ ነው። በደካማነታችንና በስንፍናችን አፍረን ተጸጽተን ብርቱና የጋለ ሃይማኖተቸውን ለመከተል እንወስን። ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ደግሞ «አባ ጸሊ በአንቲአነ         (አባ ስለ እኛ አማልዱን) እያልን እንለምናቸው።

 

29 Aug 2025, 09:11