MAP

ወጣቶች በ6ኛው የካቶሊክ ወጣት ሠራተኞች ብሔራዊ ኮንግረስ መክፈቻ ላይ በተደረገ መስዋእተ ቅዳሴ ወቅት ቅዱስ ቁርባን ሲቀበሉ ወጣቶች በ6ኛው የካቶሊክ ወጣት ሠራተኞች ብሔራዊ ኮንግረስ መክፈቻ ላይ በተደረገ መስዋእተ ቅዳሴ ወቅት ቅዱስ ቁርባን ሲቀበሉ  

በታንዛኒያ ካቶሊክ ወጣቶች ኮንግረስ ላይ ከ4,200 በላይ ተሳታፊዎች በምቤያ ከተማ መገኘታቸው ተነገረ

ከመላው ታንዛኒያ የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ካቶሊኮች እምነታቸውን ለማካፈል እና የሀገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመገንባት ላይ ያላቸውን ሚና ለመፈተሽ በምቤያ ከተማ መሰብሰባቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በታንዛኒያ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ የወጣቶች ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት (TEC) የተዘጋጀው 6ኛው የካቶሊክ ወጣት ሠራተኞች ብሔራዊ ኮንግረስ (VIWAWA) በምቤያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ (CUoM) ውስጥ ከነሃሴ 13-17 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ መካሄዱ ተነግሯል።

ዝግጅቱ የተካሄደው በምቤያ ካቶሊካዊት ሃገረ ስብከት አስተናጋጅነት ሲሆን፥ በዚህ ዝግጅት ላይ በመላ አገሪቱ ከሚገኙ 37 የካቶሊክ ሃገረ ስብከቶች የተውጣጡ ከ4,200 በላይ ወጣቶች መገኘታቸው ተገልጿል።

በመክፈቻ መርሃግብሩ ወቅት በተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የምቤያ ሃገረ ስብከት ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ጌርቫስ ኒያሶንጋ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ወጣቶች ከማንኛውም ዓይነት ግጭቶች እና ሥርዓት አልበኝነት እንዲርቁ ያሳሰቡ ሲሆን፥ ግድያ፣ አፈና፣ ማሰቃየት እና ሌሎች ማህበራዊ ኢፍትሃዊ ድርጊቶችን በማውገዝ፥ እነዚህ ወንጀሎች ብዙውን ጊዜ የሚፈጸሙት በሌሎች ተጽዕኖ ወይም በሌሎች በሚመሩ ወጣቶች እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳሱ አክለውም ወጣቶቹ ሕገወጥ የሆኑ ትዕዛዞችን በጭፍን ከመከተል እንዲቆጠቡ በማስጠንቀቅ፥ ወጣት ካቶሊኮች ምንም አይነት የውጭ ጫናዎች ቢኖሩም የሞራል ታማኝነትን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

“የነፍስ ግድያ ወይም የጠለፋ አካል አትሁኑ፥ ምክንያቱም ማንም ሰው የሌላውን ሰው ህይወት የማጥፋት መብት የለውም” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ኒያሶንጋ፥ ‘ንጹሃን ሲገደሉ ማየት በጣም ተስፋ አስቆራጭ ተግባር’ መሆኑን ገልጸው ፤ ከእነዚህ ድርጊቶች ውስጥ አብዛኞቹ በአረጋውያን ሳይሆን በወጣቶች የተፈጸሙ እንደሆኑ፤ ወጣቶቹ ይህን ተግባር እንዲፈጽሙ ቢታዘዙ እንኳን በወንጀሉ ተጠያቂው እነሱ እንደሆኑ እና በጭፍን መታዘዝ ጥበብ ያልተሞላበት ተግባር እንደሆነ አብራርተዋል።

ጥቅምት ወር ውስጥ ከሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ በፊት ሙስናን ለመታገል ጥሪ ማቅረባቸው
ሊቀ ጳጳስ ኒያሶንጋ ጥቅምት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. ላይ ለማካሄድ የታሰበውን የታንዛኒያ አጠቃላይ ምርጫ አስመልክተው እንደተናገሩት ወጣቶች ጉቦ፣ ማጭበርበር፣ ስርቆት እና አድልዎ እንዳይፈጽሙ ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ ወጣቶች ፍትሃዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፥ ለፖለቲካዊ ሙስና መሳሪያ እንዳይሆኑ አሳስበዋል።

ይህ ዓመት በተለይም ምርጫዎችን ጨምሮ ወሳኝ የሆኑ ተግባራት የሚፈጸሙበት ዓመት በመሆኑ የሙስና እድሎች ሰፊ መሆናቸውን የጠቆሙት ብጹእነታቸው፥ ወጣቶች የጉቦ መልዕክተኞች እንዳይሆኑ ወይም በመራጮች የማጭበርበር ተግባር ውስጥ እንዳይሳተፉ፣ ብሎም የሥራም ሆነ የማሰብ ስንፍናን እንዲያስወግዱ መክረዋል።

የህይወት ዋጋ እና የሞራል ሃላፊነት ላይ ትኩረት መስጠት ይገባል
ሊቀ ጳጳስ ኒያሶንጋ ወጣቶች በመንፈሳዊ ግንዛቤ እንዲኖሩ እና በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ጥበብ የተሞላበት የሞራል ምርጫ እንዲያደርጉ መክረው፥ ከዚህም በተጨማሪ የሕይወትን ክብር እንዲያስከብሩ ብሎም የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ሞራላዊ ሕሊና እንዲያስቡ አበረታተዋል።

“ሁልጊዜ እራስህን የት እንዳለህ፣ ምን እየሰራህ እንደሆነ እና ከማን ጋር እንደሆንክ ጠይቅ” ያሉት ብጹእነታቸው፥ እነዚህ ምልክቶች በጥበብ መንገድ እየተጓዝክ እንዳለህ ያሳያል ካሉ በኋላ፥ የራስን ህሊና መግራት እንደሚገባ፥ በዚህም ብቻ ሳይቆም ሌሎች የራሳቸውን ባህሪ መግራት እንዲችሉ መርዳት እንደሚገባ መክረዋል።

አደንዛዥ ዕፅን አላግባብ መጠቀምን፣ ዝሙት አዳሪነትን እና የሞራል ውድቀትን ማውገዝ
የወጣቶች በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪነት፣ ዝሙት አዳሪነት እና ሌሎች ሥነ ምግባር የጎደላቸው ተግባራት ውስጥ የመሳተፍ አዝማሚያ እየተባባሰ መምጣቱን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ኒያሶንጋ፥ ወጣቱ ከእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንዲርቅና በኅብረተሰቡ ውስጥ እየተስተዋለ ያለውን የሞራል ውድቀት እንዳይደግፍ አሳስበዋል።

“አምላክ ለሰው ልጆች ካለው ዕቅድ ጋር የሚጋጭ የግብረ ሰዶም፣ ወይም ማንኛውንም ዓይነት የብልግና ተግባራት መፈጸም ወይም ማስተዋወቅ የለብንም” ያሉት ብጹእነታቸው፥ ወላጆች ልጆቻቸው በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ውስጥ እንደሚሳተፍ ሲገነዘቡ ልባቸው እንደሚሰበር እና በአንድ ወቅት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ የነበረው አሁን የሐዘን ምንጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ብጹእነታቸው ከዚህም በተጨማሪ በሃገሪቷ ‘ቦዳ ቦዳ’ ተብለው የሚጠሩት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች በቸልተኝነት ምክንያት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ደንቦችን ስለሚጥሱ ለአላስፈላጊ አደጋ እና ሞት የሚዳርጉ ሲሆን በተደጋጋሚ በወጣቶች ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱም ጠቁመዋል።

ጥበብ፣ ጸሎት እና ዓላማ ያለው ኑሮ
ሊቀ ጳጳስ ኒያሶንጋ ወጣት የታንዛኒያ ካቶሊኮች በጸሎት፣ በማሰላሰል እና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመከተል እውነተኛ ጥበብን እንዲፈልጉ አሳስበው፥ ጥበብን የሚፈልጉ ሰዎች ብዙ እንደሚያገኙ ለማስረዳት የንጉሥ ሰሎሞንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ በማስታወስ፥ ስለ ከንቱ ነገር መጸለይ እንደማይገባ፣ ንጉስ ሰሎሞን ስለ ጥበብ ጸልዮ ሌላውን ሁሉ እንደተቀበለ እና የማዳን ኃይል ያለውን የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት እና ለመከተል መትጋት እንደሚገባ መክረዋል።

ወጣቶቹ በእውቀት እና በመንፈሳዊ ህይወት ንቁ እንዲሆኑ ጥሪ ያቀረቡት ሊቀ ጳጳሱ፥ ወጣቶቹ ችሎታቸውን ተጠቅመው ሌሎችን በማስተማር እንዲሁም ስለ እግዚአብሔር ፍቅር እና ከህዝቡ የሚጠብቀውን ግንዛቤ እንዲያዳብሩ ማገዝ እንደሚገባቸው መክረዋል።

“አላዋቂነት ብዙ ክፋትን ያስከትላል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ኒያሶንጋ፥ በመጨረሻም አንዳንድ ወጣቶች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመማር ወይም ለመረዳት እድል ስላላገኙ ብቻ በደል እንደሚፈጽሙ እና መታመን ያለብን በዓለማዊ ጥበብ ሳይሆን በመለኮታዊ ጥበብ በሆነው እና በሚያድነው ኃይል እንደሆነ በመግለጽ አጠቃለዋል።

ስለ VIWAWA ብሔራዊ ኮንግረስ
የካቶሊክ ወጣት ሠራተኞች ብሔራዊ ኮንግረስ (VIWAWA) ታንዛኒያ ከሚገኙ ሀገረ ስብከቶች የተውጣጡ ካቶሊካዊ ወጣት ሰራተኞችን ለመንፈሳዊ እድገት፣ ለትምህርት እና ለማህበረሰብ ግንባታ የሚሰበስብ ዓመታዊ ዝግጅት ሲሆን፥ ዝግጅቱ ወጣቶች በሥነ ምግባር የታነጹ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች እንዲሆኑ በማብቃት ላይ ያተኮሩ አውደ ጥናቶችን፣ ንግግሮችን እና የባህል ልውውጦችን እና የአምልኮ ሥርዓቶችን ያካተቱ እንደሆነ ተገልጿል።

25 Aug 2025, 13:36